1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግድያና ሁከት በፈርግሰን

ረቡዕ፣ ነሐሴ 14 2006

በዩናይትድ ስቴትስዋ የሚዙሪ ግዛትበምትገኘው በፈርግሰን ከተማ አንድ ጥቁር ወጣት በነጭ ፖሊስ ከተገደለ በኋላ የተነሳው ተቃውሞ አሁንም አልቆመም ። ትናንት ማታም ተቃዋሚዎች በፖሊስ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸው ተሰምቷል ። ትናንት ማታ ተቃዋሚዎች ውሃና ሽንት የያዙ ፕላስቲኮች ወደ ፖሊስ መወርወራቸውን ፓሊስ አስታውቋል ።

https://p.dw.com/p/1CyLp
USA Proteste in Ferguson 19.08.2014
ምስል Getty Images

ፖሊስ ለተቃውሞ ከተሰበሰቡት መካከል 47 ቱን አስሯል።በፈርግሰን አካባቢ ፖሊስ ለማስፈራራት ሞክሯል የተባለ ሌላ ሰው ተተኩሶበት ተገድሏል ።18 ዓመቱ ጥቁር አሜሪካዊ ማይክል ብራውን ፈርግሰን ከተማ በነጭ ፖሊስ መገደል የአሜሪካን ፣ ፖሊስ በጥቁሮች ላይ ይፈጽማል የሚባለው በደልና በከተማይቱም የጥቁሮች ይዞታ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አጉልቶ አውጥቷል ። በዩናይትድ ስቴትስዋ የሚዙሪ ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ውስጥ የምትገኘው ፈርግሰን 21 ሺህ ነዋሪዎች አሏት። ከመካከላቸው 2/3 ተኛው ጥቁር አሜሪካውያን ናቸው ።የከተማይቱ ከንቲባ፣ ከከተማይቱ 6 የምክርቤት አባላት 5ቱ እንዲሁም ከከተማዋ 53 ፖሊሶች 50ው ነጮች ናቸው ። በታዛቢዎች እምነት ፣ጥቁሩ ወጣት በፖሊስ ከተገደለ በኋላ በፈርግስን የተነሳው ሁከት በነጮችና በጥቁሮች መካከል በገሃድ የሚታየው ሰፊ ልዩነት ውጤት ነው ። በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የአፍሪቃ አሜሪካውያን ጥናት ማዕከል ሃላፊና የማህበራዊ ሳይንስ ምሁር ዳርኔል ሃንት በፈርግሰን አፍሪቃውያን አሜሪካውያን በማናቸውም ማህበራዊ ኑሮ አብሮ የመወሰን መብታቸው አይጠበቅላቸውም ይላሉ ።

Michael Brown
ምስል Getty Images

« በአጠቃላይ ልል የምችለው በሁሉም ደረጃ ፈርግሰን መጥፎ ነበር ። የከተማይቱ ምክር ቤት አባላት በሙሉ ማለት ይቻላል ነጮች ናቸው ። የትምሕርት ቤት ቦርድ አባላት በአብዛኛው ነጭ ሲሆኑ ከፖሊስም ሁሉም ማለት ይቻላል ነጭ ነው እጎአ በ1940ዎቹ በአሜሪካን የሲቪል መብት ንቅናቄ ከመጀመሩ በፊት በነበረው ሁኔታ ውስጥ ያለች ነው የምትመስለው ።»

ይህ ችግር በፈርግሰን ብቻ ነው ወይ የሚንፀባረቅ ተብለው ከተጠየቁት አፍሪቃ አሜሪካውያን 80 በመቶው ችግሩ በዛ ብቻ አይደለም የብራውን ግድያ በዩናይትድ ስቴትስ ያለውን ዘረኝነት የሚያንፀባርቅ ነው ሲሉ ፣ከነጮች ደግሞ 37 በመቶው ግድያው ዘረኛነት አለበት ብለው እንደሚያስቡ ጠቁመዋል ። የሲቪልና የሰብዓዊ መብቶች አመራር ጉባኤ በመባል የሚጠራው የመብት ተሟጋች ድርጅት ቃል አቀባይ ሌክሰር ክዋሚ እንደሚሉት አሁን በፈርግሰን የሆነው አዲስ ነገር አይደለም ።

«እንደሚመስለኝ ፈርግሰን የሆነው በዚህ ሃገር ባለፉት ዓመታት ና አሥርት ዓመታት በተደጋጋሚ ሲፈፀሙ ያየናቸው ድርጊቶች ምሳሌ ነው ። »

Ferguson Polizeigewalt 17.08.2014
ምስል Getty Images

ክዋሚ ከዚህ ቀደም ያልታጠቁ ጥቁር አሜሪካውያንን የገደሉ ፖሊሶች ለፍርድ ሳይቀርቡ መታለፋቸውን ያስታውሳሉ ። ፍሎሪዳ ውስጥ የአካባቢው ሰላም አስጠባቂ አባል በነበረ ሰው የ17 ዓመቱ ወጣት ትሬቨን ማርቲን መገደሉና በተለይ ደግሞ የገደለው ሰው በነፃ መለቀቁ በዓለም ዙሪያ ትልቅ ዜና ነበር ። በወቅቱ የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ባራክ ኦቦማ እኔም የትሬቬን ማርቲን እጣ ሊገጥመኝ ይችል ነበር ብለዋል ። በአሜሪካን ፖሊሶች ምን ያህል ተጣድፈው መሣሪያ እንደሚተኩሱ የተካሄደ ስታስቲክሳዊ ጥናት ባይኖርም በቅርብ ዓመታት ግን መሰል ሁኔታዎች ተደጋግመው ተከስተዋል ። Mother Jones የተባለው የግራ ለዘብተኛው መፅሄት ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በአንድ ወር ውስጥ 4 ያልታጠቁ ጥቁሮች በፖሊሶች መገደላቸውን ዘግቧል ። የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ ሃንት እንደሚሉት በነጮች ላይ ግን ይህ ሲደርስ አልታየም ።

«ይህን መሰል እርምጃ ስለተወሰደባቸው መሣሪያ ያልያዙ ነጭ ወጣቶች ጉዳይ ግን አንሰማም ። »

USA Proteste in Ferguson 19.08.2014
ምስል Reuters

በርሳቸው አስተያየት ጥቁሮች ላይ ተደጋጋሚ ግድያ የሚፈጸመው አሁንም ባልተቀየረው መጥፎ አመለካከት ምክንያት ነው ።

«ይህ ጥቁሮች አስጊዎች ናቸው ፣ በተለይ ደግሞ ጥቁር ወንዶች የሚያስፈሩ በመሆናቸው በጥብቅ ቁጥጥርና በፖሊስ ክትትል ስር መዋል አለባቸው ካስፈለገም በእንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ፖሊስ እስከ መግደል የሚደርስና ከተጠያቂነት ነጻ የሚያደርግ እርምጃ መውሰድ ይችላል የሚለውን አመለካከት የሚወክለው ነው ። »

የወጣቱ ጥቁር አሜሪካዊ ግድያ በፈርግሰን ያስነሳው ተቃውሞ አልቆመም ።ተቃውሞው የወጣቱን ህይወት ባይመልስም በሃገሪቱ ለዓመታት ተሸፋፍኖ የቆየው የዘረኝነት ጉዳይ ዳግም የመነጋገሪያ ርዕስ እንዲሆን ግን አድርጓል ።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ