1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰሞኑ የግብር እሰጥአገባ

ነጋሽ መሐመድ
እሑድ፣ ሐምሌ 23 2009

ባንድ በኩል ሱቆች እንዲዘጉ ሲያሳድሙ የነበሩ ሰዎችን አሳሰርን ይላሉ።እዚያዉ ላይ ደግሞ ግብር ከተጣለበት ነጋዴ አብዛኛዉ 68 በመቶዉ ግብሩን እየከፈለ ነዉ ይላሉ።32 በመቶዉ ለመንግሥት ቅሬታ ማቅረባቸዉን እና 99 በመቶዉ ተገቢ መልስ ማግኘታቸዉን አስታዉቀዋል።ቅሬታ አቅራቢዎች «ተገቢ» መልስ ካገኙ የሚያድመዉ ወይም አድማ የሚያነሳሰዉ ማነዉ?

https://p.dw.com/p/2hKWQ
Äthiopien Lebensmittel-Markt in Addis Ababa
ምስል DW/Y. Gebre-Egziabher

ውይይት፦ ግብርና መዘዙ

የኢትዮጵያ መንግስት «ሐ» የሚል ደረጃ በሰጣቸዉ አነሰተኛ ነጋዴዎች ላይ የጣለዉን የግምት ግብር በመቃወም የሚደረገዉ አድማ፤የሚሰማዉ ቅሬታና እና ትችት አሁንም እንደቀጠለ ነዉ።

የተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች እና የአዲስ አበባ ነጋዴ መደብሮቹን እየዘጋ አድማ ለመምታት ሞክሯልም።አንቦን በመሳሰሉ ከተሞች ደግሞ  የመንግሥትንና የባለሥልጣናትን ተሽከርካሪዎችን እስከመሰባበር ደርሷል።

ግብር የየትኛዉም ዜጋ ግዴታ መሆኑ አላነጋገረም።የኢትዮጵያ መንግሥት ግን በዚሕ ወቅት በአነስተኛ ነጋዴዎች ላይ  ግብር መጣሉን አንዳዶች፤ በኃይልና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከገደበዉ ሕዝባዊ አመፅ  «የትኩረት አቅጣጫን ለማሳት ያለመ» በማለት ይተቹታል።ሌሎች ደግሞ በየአመቱ ባለሁለት አሐዝ የምጣኔ ሐብት ዕድገት ማስመዝገቡን የሚያዉጅ መንግሥት፤ ፀጉር ቆርጠዉ፤ሻሂ ቸርችረዉ የዕለት ጉርስ ለማግኘት በሚባትሉ ዜጎች ላይ ተጨማሪ ግብር መጣል ለምን አስፈለገዉ እያሉ ይጠይቃሉ።

ግብሩ፤ በጥናት ሳይሆን «ገማች» በሚባሉ ሰዎች በጎ ፈቃድና ስሜት የሚጣል መሆኑ ታዛቢዎችን ግራ አጋብቷል።የኢትዮጵያ የገቢዎችና የጉምሩክ መስሪያ ቤት ባለሥልጣናት በመንግሥት ለሚደገፉ መገናኛ ዘዴዎች ሰጡት የተባለዉ መግለጫ  አንዱ ከሌላዉ የሚቃረን ነዉ።

ባንድ በኩል ሱቆች እንዲዘጉ ሲያሳድሙ የነበሩ ሰዎችን አሳሰርን ይላሉ።እዚያዉ ላይ ደግሞ ግብር ከተጣለበት ነጋዴ አብዛኛዉ 68 በመቶዉ ግብሩን እየከፈለ ነዉ ይላሉ።32 በመቶዉ ለመንግሥት ቅሬታ ማቅረባቸዉን እና 99 በመቶዉ ተገቢ መልስ ማግኘታቸዉን አስታዉቀዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎች «ተገቢ» መልስ ካገኙ የሚያድመዉ ወይም አድማ የሚያነሳሳዉ ማነዉ? የሚለዉ ጥያቄ ግን መልስ አላገኘም።ባለሥልጣናቱ ዝቅተኛ ነጋዴዎች ያመኑበትን ግብር ይክፈሉ ማለታቸዉም ተዘግቦ ነበር።ወዲያዉ ግን ባለሥልጣናቱ አላልንም አሉ። መግለጫዉም እንደ ግብሩ የግምት ይሆን? ለዚሕና ለመሠል ጥያቄዎቹ መልስ እንዲሰጡን የሚመለከታቸዉ ባለሥልጣናት ጋ በተደጋጋሚ ደዉለን ነበር።ገሚሶቹ ሥልካቸዉን እያነሱም።የተቀሩት ሥልክ ዝግ ነዉ።ሌሎቻችን እንቀጥላለን።ሰወስት እንግዶች አሉን።

ነጋሽ መሐመድ

ልደት አበበ