1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም» HRW

ሐሙስ፣ ጥር 14 2007

የኢትዮጵያ መንግሥት በመጪዉ ግንቦት ለሚካሄደዉ ምርጫ ነፃ ሃሳብን ለማገድ ሆኖ ብሎ የግል መገናኛ ብዙሃንን እየተጫነ ነዉ ሲል ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋቹ ድርጅት ሂዉማን ራይትስ ዎች አመለከተ።

https://p.dw.com/p/1EPEG
Pakistanische Journalisten protestieren gegen Behinderung der Arbeit
ምስል picture-alliance/dpa

የሂዉማን ራይትስ ዎች ዘገባ የኢትዮጵያ መንግሥት ለመረጃ ምንጭነት እና ትንታኔያቸዉ ዋጋ ከመስጠት ይልቅ እንደስጋት ስለሚያያቸዉ የግል መገናኛ ብዙሃንንና ገለልተኛ ድምፆችን ሆን ብሎ እያጠቃ መሆኑን ያመለክታል። ድርጅቱ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2010 ወዲህ ብቻ ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብታቸዉን እየተቀሙ 19 ጋዜጠኞች ወህኒ እንደተወረወሩ፤ ሌሎች 60 የሚሆኑት ደግሞ ከሀገር እንደተሰደዱ እንደ ማሳያ ይጠቅሳል።«ጋዜጠኝነት ወንጀል» አይደለም በሚል ርዕስ የተዘጋጀዉን ባለ 76 ገፅ ዘገባ ሲቀናበርም ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2013 መጋቢት እስከ ታሕሳስ 2014 ባሉት ጊዜያት ኢትዮጵያ ዉስጥ በሥራ ላይ ያሉት እና በስደት የሚገኙ 70 ኢትዮጵያዉያን ጋዜጠኞችን ማነጋገራቸዉን የገለፁት በሂዉማን ራይትስ ዎች የአፍሪቃ ጉዳይ ዘርፍ ተመራማሪ ፊሊክስ ሆም ጥቃቱ በጋዜጠኞቹ ላይ ብቻ እንደማያበቃ ዘገባዉ ለማሳየት መሞከሩን ይገልፃሉ።

Menschenrechte Logo human rights watch

«ዘገባዉ ከ2002ቱ ምርጫ ወዲህ በግልና ገለልተኛ መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚደርሰዉን ማዋከብ ያሳያል፤ በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ በመሥራታቸዉ ወደ60 የሚሆኑ ከሀገር መሰደዳቸዉን፣ 19 የሚሆኑት መታሠራቸዉን ፤ በተጨማሪም ገለልተኛ ድምፆችንና ጋዜጠኞችን ፀጥ ለማሰኘት መንግስት የሚጠቀምባቸዉን እንደማስፈራራትና ማዋከብ እንዲሁም የወንጀል ክሶችን የመሰሉ ስልቶችና ዘዴዎች መዝግቧል። ከዚህም ሌላ ጥቃቱ አሳተሚ ድርጅቶችና የግል ኅትመት ዉጤት አከፋፋዮችን እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃኑን የመረጃ ምንጮችም ሁሉ ማካተቱን ዘገባዉ ይዘረዝራል።»

በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ የሀገሪቱ የኅትመት፣ የቴሌቪዥንና የራዲዮ መገናኝ ብዙሃን በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መሆናቸዉን የገለፀዉ የሂዉማን ራይትስ ዎች ዘገባ ቀሪዎቹ ጥቂት የግል መገናኝ ብዙሃን እንዳይዘጉ ሲሉ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በሚዘግቡበት ጊዜ ራሳቸዉን እንዲመረምሩ (ሠልፍ ሴንሰርሺፕ) እንደሚያካሂዱም ዘገባዉ ይገልጻል። ኢትዮጵያ ዉስጥ መገናኛ ብዙሃኑ ላይ የሚደረገዉ ጫናም በመጪዉ የግንቦት ምርጫ ወቅት ሊኖራቸዉ በሚችለዉ ሚና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያስከትልም ከወዲሁ ያሳስባል። ይህን ከወዲሁ መገመት እንደማይከብድም ፊሊክስ ሆም በእርግጠኝነት ይናገራሉ፤

Temesgen Desalegne
እስር ላይ ከሚገኙት ጋዜጠኞች አንዱ ተመስገን ደሳለኝምስል DW

«ባለፈዉ ምርጫ ገዢዉ ፓርቲ በ99,6 በመቶ ማሸነፉ ከተነገረበት ከ2002,ም ወዲህ የምንመለከተዉ በይፋ የሚደረጉ ዉይይቶችና ክርክሮች ይባስ ተመናምነዋል። ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ የሚደረገዉ ማዋከብ፤ ሃሳባቸዉን የሚገልፁ የሲቪል ማኅበረሰቦች መቀነስ በዚያም ላይ የግል መገናኛ ብዙሃን ቁጥር እያነሰ ሄዷል። የግል መገናኛ ብዙሃን የወቅቱን ፖለቲካዊ ጉዳዮች በማጋራት ከምርጫዉ በፊት ይፋዊ ክርክሮችን በማነቃቃት ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ኢትዮጵያ ዉስጥ ባለዉ የግል ፕረሱን የመጫን ርምጃ አንገጋቢ ፖለቲካዊ ጉዳዮች በዚህ ወቅት ብዙም ሽፋን ሲያገኙ አይታዩም።»

ዘገባዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ የግል ፕሬሱ ላይ የተደቀኑትን ችግሮች በመዘርዘር ብቻ ያላበቃዉ የሂዉማን ራይትስ ዎች ዘገባ መንግሥት የሀገሪቱን የመገናኛ ብዙሃን ይዞታ በበጎ መልኩ ለማስተካከል ጊዜዉ አልረፈደበትም ሲልም ያበረታትል። ፊሊክስ ሆም ምንም እንኳን ይህን የሚያመለክቱ አዎንታዊ ርምጃዎች እስካሁን ሲወሰዱ ባይታይም ድርጅታቸዉ ተስፋ የሚያደርገዉን ዘርዝረዋል።

«መንግሥት ከምርጫዉ በፊት ነገሮችን ክፍት ሊያደርግ እንደሚችል የሚያሳዩ አዎንታዊ ነገሮች ያን ያህል አይታዩም። የምርጫዉ ጊዜ ፈጥኖ እየደረሰ ነዉ። ምንም እንኳን የሚታይ ምንም አዎንታዊ ነገር ባይሆንርም መንግሥት በሀገሪቱ የዲሞክራሲ ሂደት ንቁ ፕሬስ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ይገነዘባል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤ በዚህ ምክንያትም ጋዜጠኞችና የድረገፅ ፀሐፍቱ ከእስር ይፈታሉ ብለንም ተስፋ እናደርጋለን። በተጨማሪም ኢትዮጵያ በሕገ መንግሥቷ ላይ ሃሳብን በነፃነት በመግለፅ ረገድ ካሰፈረችዉ ጠንካራ አንቀፅ ጋ በሚጣጣም መልኩ እነዚያን ችግር ፈጣሪ ሕጎች ታሻሽላለች ብለን ተስፋ እናደርጋለን።»

Karte Äthiopien Afar-Region
ምስል DW

ፊሊክስ ሆም ዘገባዉን ለማጠናቀር የተለያዩ ኢትዮጵያዉያንን ማነጋገሩ ቀላል እንዳልነበር ያመለከቱ ሲሆን ብዙዎችም ከግል እና ገለልተኛ መገናኛ ብዙሃን ጋም ሆነ ከመብት ተሟጋች ተቋማት ጋ ቃለምልልስ ያካሄዱ ዜጎች የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ክትትል እንደሚያደርጉባቸዉ እንደገለፁላቸዉም ጠቅሰዋል።

«ለማንኛዉም የመብት ተሟጋች ድርጅት እንዲህ ያለዉን ምርምር ማካሄድ በጣም ፈታኝ። ሲቪል ማኅበረሰቡና በርካታ ድርጅቶች ገደብ ተጥሎባቸዋል። በተጨማሪም ከመገናኛ ብዙሃን ወይም ከመብት ተሟጋች ድርጅቶች ጋ የተነጋገሩ ግለሰቦች የደህንነት ወኪሎች ተፅዕኖ እንደሚያርፍባቸዉ ለማወቅ ችለናል። የፀጥታ ኃይሎች ስለሚመጡባቸዉ ዉይይታችን ከጨረስን በኋላ ይህ ስጋትና የዘፈቀደ እስር በመኖሩ ሰዎች ለመናገር በጣም ይፈራሉ።»

Zeitungen Äthiopien

መንግሥት የሂዉማን ራይትስ ዎችንም ሆነ የሌሎች ለጋዜጠኞችና ለሰብዓዊ መብት የሚሟገቱ ድርጅቶች የሚያቀርቧቸዉን ዘገባዎች ከመጣጣል አልፎ ድርጅቶቹን በአፀፋዉ ሲከስ ይስተዋላል። አንዳንድ ጋዜጠኞችም ይህንኑ ፈለግ በመከተል እነዚህ ድርጅቶች ሌላ ዓላማ እንዳላቸዉ መናገር ጀምረዋል። እርስዎ ምን ምላሽ አልዎት ብያቸዉ ነበር።

«እኛ ያለን አጀንዳ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመመዝገብ መንግሥታት ያንን ድርጊት እንዲያወግዙት ማድረግ ነዉ። ይህን በኢትዮጵያም፣ በኤርትራም በመላዉ ዓለም በሌሎች ሃገራትም እናደርገዋለን። ያለን አጀንዳ ያ ነዉ። እንደኛ ያሉ ድርጅቶች ለሚያነሱትን ርዕሰ ጉዳይ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ማዉገዙ ብዙም ትርጉም አይሰጥም።»

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ