1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጋዛ፤ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተቋረጠ

እሑድ፣ ሐምሌ 13 2006

የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰርጥ ሟቾችን እና ቁስለኞችን ለማንሳት ለ2 ሰዓታት የተኩስ አቁም ተስማምቷል ተብሎ ነበር። ይሁንና የሀማስ ቡድን ቃሉን እንዳልጠበቀ ነው የሚነገረው። ሁለቱ ቡድኖች ባደረጉት የተኩስ አቁም ስምምነት የተነሳ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ወደ ስፍራው ሰርጎ ገብቶ ነበር።

https://p.dw.com/p/1Cfoa
Gaza Bodenoffensive Israel Soldaten 20.07.2014
ምስል Reuters

ለ2 ሰዓታት የታቀደው የተኩስ አቁም ከተጀመረ ከአንድ ሰዓት በኃላ በሀማስ ቡድን እንደተቋረጠ ነው የእስራኤል የመንግስት ቃል አቀባይ የተናገሩት። ዛሬም የእስራኤል እግረኛ ጦር በጋዛ ሰርጥ የጀመረዉን ጥቃት አጠናክሮ ቀጥሎአል። ጋዛ ሳዱሺጃ በተባለዉ ከተማ አካባቢ ዛሬ በደረሰ ጥቃት ቢያንስ 40 ሰዎች ተገድለዋል 400 የሚሆኑ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በጋዛ ምሥራቃዊ የከተማዉ ክፍል ከፍተኛ ጥቃት ከደረሰ በኃላ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መኖርያ ቀያቸዉን ለቀዉ እየወጡ መሆኑም ተመልክቶአል። ሟቾችን ለማንሳት እና ቁስለኞችን ለመርዳት እንዲያስችል በዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ አነሳሽነት እስራኤልና ሃማስ የጀመሩትን ጦርነት ለሰዓታት እንዲገቱ መስማማታቸዉም ተገልፆአል።እስራኤል የእግረኛ ጦርዋን በጋዛ ሰርጥ ካስገባች ወዲህ ፤ ከፍልስጤም ወገን ከ 350 በላይ ሰዎች መገደላቸዉ ነዉ የተነገረዉ። እስራኤል በበኩልዋ ሰባት ወታደሮችዋ እንደተገደሉባት ገልፃለች።

Zivilisten leiden in Gaza
ምስል DW/Shawgy el Farra

ሃማዝ ከርሰ ምድር ዉስጥ የገነባዉን መሿለክያ መንገድ እና፤ የመሣርያ ማጠራቀሚያ ዴፖ እንዳይፈርስ በመታገል ላይ እንደሆነ የገለፁት የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል ቃል አቀባይ ፒተር ልርነር፤ ጦሩ በሃማስ የተገነባዉን ምድር ለምድር መሿለኪያ መንገድና የመሣርያ ማከማቻ ለመያዝ በሚደረገዉ ጥረት፤ ከሃማስ ወገን ከፍተኛ ትግል ገጥሞታል።

Zivilisten leiden in Gaza
ምስል DW/Shawgy el Farra

እንደ ፒተር ለርነር እስካሁን በፈንጂ መዉደም ያለባቸዉ 36 መገናኛ ያላቸዉ 14 የከርሰ ምድር ዉስጥ ለዉስጥ መሿለክያ ረጅም መንገዶች ተገኝተዋል። ከነዚህ መሿለክያዎች መካከል አንዳንዶቹ የመሳርያ ማከማቻዎች ናቸዉ። በሌላ በኩል የፍልስጤሙ ፕሬዚዳንት ሞሃሙድ አባስ እና የተመድ ዋና ፀሃፊ ባን ኪሙን፤ ሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች ለተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ዛሬ ካታር ላይ ለመገናኘት እቅድ ይዘዋል። በዉይይቱ መጠናቀቅያ አባስና የሃማስ ቡድን መሪ ቻሊድ ሚሻል ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ