1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጋምቢያውያን ከጃሜሕ በኋላ ለውጥ ይኖራል የሚል ተሥፋ ቢያደርጉም ሥጋትም ገብቷቸዋል

ሰኞ፣ ኅዳር 26 2009

ለ22 አመታት ጋምቢያን እንደ ብረት ቀጥቅጠው የገዙት ያሕያ ጃሜህ በስተመጨረሻ ሽንፈታቸውን ተቀበሉ። የምርጫው ውጤት ጋምቢያውያንን አዲስ ተስፋ ቢሰጣቸውም ያለፈውን ጊዜ በቀላሉ የሚዘነጉት አይመስልም። 

https://p.dw.com/p/2Tm0h
Gambia Musiker Jaliba Kuyateh
ምስል DW/A. Kriesch

Gambia – Blick nach vorn oder zurück? - MP3-Stereo

Gambia neuer Präsident Adama Barrow
ምስል Getty Images/AFP/M. Longari

ጃሊባ ኩያቴህ በሕይወቱ ብዙ ውጣውረዶችን አሳልፏል። ሙዚቀኛው ከክራር መሰሉ ኮራ የሙዚቃ መሳሪያ ጋር በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሥራዎቹን አቅርቧል። እንዲህ አይነት ቀን ግን ፈፅሞ ገጥሞት አያውቅም። በተለይም በትውልድ አገሩ ጋምቢያ። የጋምቢያ የምርጫ ውጤት በታወቀበት ዕለት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ጃሊባ ኩያቴህ የሙዚቃ ዝግጅት ተመሙ። እርሱም ተቃዋሚዎችን እና በአገሪቱ የታየውን ለውጥ የሚያወድስበትን ሙዚቃ አቀነቀነ። 

«ታዳሚዎቼ በጥሩ ሥሜት በታላቅ ደስታ ውስጥ እንደነበሩ አውቂያለሁ። ይኸን ሙዚቃ ብጫወት  አስደናቂ  እንደሚሆን ሁሉንም እንደሚያስደስት አውቂያለሁ።» በሙዚቃ ድግሱ ደስታ እና ግፊያ በዛ። ሙዚቀኛውም ለደህንነቱ ሲል የሙዚቃ መሳሪያውን (ኮራ) ይዞ ከመድረኩ ገሸሽ አለ። የሙዚቃ ድግሱም ተበተነ። 

የጠፉት ተቺዎች

ጃሊባ ኩያቴህ ባለፉት አመታት ለሕይወቱ የሚሰጋ ሙዚቀኛ ነው። ኩያቴህ ባይስማማም «ተቃዋሚው ሙዚቀኛ» የሚል ስም ተለጥፎበታል። «ስሜ በእነሱ መዝገብ ላይ በጥሩ ጎን ስላልሰፈረ ለእኔ አስቸጋሪ ነበር። በጊዜው የምፈልገው መስራት አልችልም ነበር። ተቃዋሚው ሙዚቀኛ የሚል ሥም ተሰጥቶኝ ነበር። ነገር ግን አንድም ቀን ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ጊዜ አሳልፌ አላውቅም።»ፕሬዝዳንት ያሕያ ጃሜሕ በስልጣን በቆዩባቸው አመታት በርካታ የመንግሥት ተቺዎች «አደገኛ» እየተባለ በሚወቀሰው ፖሊስ እየታፈኑ በተደጋጋሚ ይጠፋሉ። 
የምርጫው ውጤት የፈጠረው ሐሴት ቀኑን ሙሉ ቢዘልቅም በ22 አመታት የጃሜሕ የሥልጣን ዘመን የተፈጠረው መሰላቸት* ግን ሥር የሰደደ ነው። በአደባባዮች የተሰቀሉ የጃሜሕ የምረጡኝ ዘመቻ ማስታወቂያዎች ለመቀደድ ውጤቱ ከታወቀ በኋላ ጥቂት ደቂቃዎች ነበር የወሰደባቸው። 

የአዲሱ ፕሬዝዳንት ጥሪ 

ተመራጩ ፕሬዝዳንት አዳማ ባሮው ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ የደቡብ አፍሪቃን ሥልት በመከተል እውነት እና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን እንደሚመሰርቱ ተናግረዋል። አዳማ ባሮው አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት የፖለቲካ እስረኞችን እንዲፈታም ጥሪ አቅርበዋል። ጃሜሕ በስልጣን በቆዩባቸው አመታት ጋምቢያ እስላማዊ ሪፐብሊክ መሆኗን አውጀዋል፤ከጋራ መገበያያ አገራት እና ከዓለም አጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት አባልነት አስወጥተዋታል። አዳማ ባሮው አንዴ የፕሬዝዳንትነት መንበረ-ስልጣኑን ሲረከቡ እነዚህን ሁሉ ውሳኔዎች እንደሚቀለብሱ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚታሙትን ያሕያ ጃሜሕ ከችሎት ያቆሟቸው ይሆን? 
«ይኸን ምርጫ የተወዳደርነው ለውጥ እንፈልጋለን በሚል መርሕ ነው። የምንፈልገው ለውጥ መጥቷል። ከማንም ጋር ግለሰባዊ ጠብ የለንም። ሥልጣን እንደተረከብን በዚች አገር የተፈጠሩ አብዛኞቹን ነገሮች እንመረምራለን። የምናገኘውን የመጨረሻ ውጤት መሰረት አድርገን እንወስናለን።  ፍትኅ ለሁሉም ይሆናል። ሕጋዊውን የአሰራር ሥርዓት እንከተላለን። ማንም ምንም ሊፈራ አይገባም። ለሁሉም ጥሩ የሆኑ ሕግጋት ሥራ ላይ እናውላለን።» 

Gambia Wahlen Yahya Jammeh
ምስል Getty Image/AFP/M. Longar

አንቶኒ ታባል አገር ጎብኚዎች ከሚያዘወትሩት ኮሎሊ ከሚገኘው የግሪን ማምባ ምግብ ቤት ውስጥ ተቀምጧል። በጥሩ ስሜት ላይ የነበረው የምግብ ቤቱ ባለቤት ቅንጡ የእጅ ስልኩን ተመልክቶ ተበሳጨ። አንቶኒ ታባል በማሕበራዊ ድረ-ገፆች ላይ ፕሬዝዳንቱን የሚዘልፉ ግድያ እንዲፈጸምባቸው ጥሪ የሚያቀርቡ ጽሁፎችን ነበር ያነበበው። 


«ይኽ ፕሬዝዳንቱን ፤ ሚኒስትሮቻቸውን እና በጦሩ ውስጥ የሚገኙ አዛዦቻቸውን የሚያስፈራራ ነው።  ነገር ግን አሁንም የጦር መሳሪያ ታጥቀዋል። አሁንም ፕሬዝዳንት ናቸው።» ሲሉ አንቶኒ ታባል ሥጋታቸውን ይገልጣሉ። የሥጋት ደመናው ገሸሽ ባይልም ጊዜው ጋምቢያ ወደ ፊት የምትመለከትበትም ጭምር ነው። 
የ46 አመቱ አንቶኒ ታባል የሥልጣን ሽግግሩ ከዩናይትድ ስቴትስ እንኳ በተሻለ ሁኔታ እየተካሔደ ነው ብለው ያምናሉ። ለ22 አመታት ጃሜሕ እንደ ብረት ቀጥቅጠው የገዟት ትንሺቱ አገር ጋምቢያ ኤኮኖሚያ እድገት እንደምታዝመዘግብም ተስፋ አድርገዋል። በእሳቸው እምነት አንዴ ጃሜሕ ከስልጣን ገለል ካሉ የውጭ ባለወረቶች እና የልማት እርዳታዎች ወደ ጋምቢያ ይጎርፋሉ። 
ሙዚቀኛው ጃሊባ ኩያቴህም ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር አገሪቱን ወደ በጎ ምዕራፍ እየወሰዳት እንደሆነ ያምናል። ኩያቴሕ ከዚህ ቀደም በሌሎች አገሮች ሲጓዝ የአገሩ ጋምቢያ ሥም በተደጋጋሚ ከአምባገነንነት ጋር ሲያያዝ አስተውሏል። «ይኽ ለእኔ አሳፋሪ ነው» የሚለው ኩያቴሕ ጋምቢያ ለተያያዘችው ለውጥ አሁን የተሻለ ማበረታቻ እና ክብር እናገኛለን የሚል እምነት አለው። 


አድሪያን ክሪኸ/እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ