1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ጉዞ» የኢትዮጵያ ሙዚቃ ጥናት

ሐሙስ፣ መጋቢት 8 2008

«ጉዞ» የሙዚቃ ጥናት ምርምር ቡድን ከታዋቂዉ ኢትዮጵያዊ ጃዝ ፒያኖ ተጫዋች ከሳሙኤል ይርጋ ጋር በመሆን በተለያዩ የሙዚቃ ቅላጼዎች ላይ ምርምሩን ያደርጋል፤ የሙዚቃ አመጣጥ ፈለግንም ይፈትሻል ይላል፤

https://p.dw.com/p/1IEkH
«ሳሚ ልስልሱ በፒያኖው አንጀት እርሱ» ይሉታል አድናቂዎቹ
ሙዚቀኛ ሳሙኤል ይርጋምስል York Tillyer

ጀርመን ቫይመር ከተማ በታዋቂዉ የሙዚቃ ቀማሪና፤ የፒያኖ ተጫዋች በፍራንዝ ሊስት በተሰየመዉ ከፍተኛ የሙዚቃ ትምህርት ተቋም ድረ-ገጽ ላይ የሚነበበዉ መረጃ።

ኢትዮጵያዊ የፒያኖ ተጫዋች ሳሙኤል ይርጋና ኢትዮጵያዉያን ብሎም ሌሎች የሙዚቃ ምሑራንን ያካተተዉ በጀርመን መንግሥት የሚደገፈዉ «ጉዞ» የተሰኘዉ የሙዚቃ ጥናት የዕለቱ መሰናዶአችን ትኩረት ነዉ።

Team GUZO
ሳሙኤል ይርጋ እና ዶ/ር ጌቲ ገላዬምስል Dr. Getie Gelaye


በጀርመን መንግሥት የሚደገፈዉ «ጎዞ» የተሰኘዉ የሙዚቃ ጥናት ፕሮጀክት ዋና ኃሳብን የጠነሰሰዉ ታዋቂዉ የሙዚቃ ባለሙያ ሳሙኤል ይርጋ ነዉ። ሳሙኤል ጉዞ የሚልና በዓለም ሙዚቃ አፍቃሪዎች ተደናቂነትን ያገኘ የሙዚቃ ሲዲም ማሳተሙ ይታወቃል። ይህ ሲዲ በተለይ ከፊልም ባለሙያዎች አድናቆትን ማትረፉ ይነገርለታል። የሳሙኤል ሙዚቃዎች የኢትዮጵያን የሙዚቃ ባህል ሳይለቁ ቅኝቶቹን ሁሉ አካቶ በዓለም ደረጃ ሊደመጥ የሚችል ኢትዮ ጃዝ የሚለዉ ሙዚቃ ቅላጼ በዓለም ደረጃ ከፍተኛ እዉቅናን ያስገኘ መሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሳሙኤልን ኃሳብ በመቀበል ድጋፍ ሰጥቶታል። ወጣቱ ሙዚቀኛ ሳሙኤል ይርጋ በተለያዩ ጊዜያት ወደ ጀርመን መጥቶም ሥራዎቹን አቅርቧል፤ ስለጀመረዉ ጥናትም ከባለሙያዎች ጋር ተወያይቶአል።


«ከጀርመን መንግሥት ጋር ያለኝ ፕሮጀግት የሙዚቃ ጥናት ፕሮጀክት ነዉ። ለረጅም ጊዜ ሳስበዉ የነበረ የጥናት ሃሳብ ነበር። የኢትዮጵያ ሙዚቃ መፍለቅያዉ የት ነዉ። የኢትዮጵያ ሙዚቃ ስንል በሰሜን በኩል የሚገኘዉ አዝማሪ ብቻ ሳይሆን ፤ ደቡብም ሊሆን ይችላል ምስራቅም፤ ምዕራብም ሊሆን ይችላል። የኢትዮጵያን ሙዚቃ የሚገልጽ ከየት መጣ፤ ከዉጭ ነዉ ወይስ እዝያዉ ነዉ የተወለደዉ፤ ምናልባት ከተለያዩ ሃገራት ጋር ተያያዥነት ያለዉ ታሪክ ካለዉ ወይም መነሻ ካለዉ ያንን ማጥናት ህልም ነበረኝ። ኢትዮጵያ ዉስጥ በሙሉ ከሰሜን ጀምሮ እስከ ደቡብ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ያለዉን ቦታ ተጉዤ እንደ ማኅበረሰቡ እየበላሁ እየጠጣሁ ሙዚቃዉን ለማጥናት ነዉ ፍላጎቴ። ምናልባትም የዋሽንት፤ የክራር፤ የመሰንቆ የሙዚቃ መሳርያ መነሻዉ ከየት እንደሆነ ማግኘት ከተቻለ ፤ የአዝማሪ ሙዚቃ ከየት ተገኘ የደቡብ ማኅበረሰብ ሙዚቃ መነሻዉ ከየት ነዉ የሚለዉን ለማጥናት ህልሜን እዉን ለማድረግ ለጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያቀረብኩት ሃሳብ ነበር። እነሱም በሃሳቡ በጣም ስለተደሰቱ ይህንን ሃሳብ በገንዘብ በመደገፍ ፤ በቫይማር ጀርመን ከሚገኘዉ የሙዚቃ ተቋም ጋር አጋር ተመራማሪ ሆኜ ለመስራት አማካሩኝ እኔም ፈቃዴን ገለጽኩላቸዉ። ከዚህ ሌላ በርካታ ፕሮፊሰሮች የሙዚቃ ምሁራን የማኅበረሰብ አጥኝዎች፤ ሙዚቀኞች በዚሁ የጥናት ቡድን ይሳተፋሉ፤ ጥናቱ ተጀምሮአል። እስከ አሁን እንደ ዶክተር ትምክህት ተፈራ ፤ እንደ ዶክተር ጌቲ ገላይ የተካፈሉበት ትልቅ ጥናት ተጀምሮአል።»

Team GUZO
የጉዞ ጥናት ምሑራንምስል Dr. Getie Gelaye


ሳሙኤል ይርጋ ቫይመር በሚገኘዉ ከፍተኛ የሙዚቃ ተቋም በተጋበዘት ወቅት፤ ተቋሙ በተሰየመበትና በክብር በተቀመጠዉ በፍራንዝ ሊስት ፒያኖም ሙዚቃ ተጫዉቷል ያሉን በሃንቡርግ ዩንቨርስቲ የአፍሪቃ እና የኢትዮጵያ ጥናቶች የትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጌቲ ገላዬ፤ በሦስት ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረዉ «ጉዞ» የተሰኘዉ ይህ ፕሮጀክት በርካታ ምሁራንን ያካተተ ነዉ ሲሉ ይገልጻሉ።

Team GUZO
ዶ/ር ትምክህት ተፈራ እና ሙዚቀኛ ሳሙኤል ይርጋምስል Dr. Getie Gelaye


« ይህ ፕሮጀክት ብዜ ምሁራንን ያካተተ ነዉ። ከአሜሪካ ፕሮፊሰር ዴቪድ ኤቫንስ፤ ከጃፓን ዶክተር ካዋሲ አለ። ከፈረንሳይ የኢትዮጵያን ሙዚቃ የሚያሳትመዉ ፍራንሲ ፋልሴቶም ይገኛል፤ ከጀርመን ዶክተር ትምክህት ተፈራ፤ እኔ እንዲሁም ከቫይመር ዩንቨርስቲ ፕሮፊሰር ቲያጎ ፒንቶም ተካፋይ ናቸዉ። ሌሎችም በአጋጣሚ መገኘት ያልቻሉ የኢትዮጵያን ሙዚቃ የሚያጠኑ ምሁራን አሉ። እና ይህ «ጉዞ » የሚለዉ የሙዚቃ ጥናት ፕሮጀክት ተጀመረ እንጂ ገና አላለቀም። ጥናቱ በሦስት ዋና ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ነዉ። የኢትዮጵያን ሙዚቃ ጥንት መሰረት መሳርያዎች ጨምሮ የሚያጠና የሚሰበስብ በሳይንሳዊ ዘዴ ምርምር የሚያደርግ ነዉ። ሁለተኛዉ ይህንን ምርምር በፊልም የሚደግፍ ሳይንሳዊ የዘጋቢ ፊልም ይሰራበታል። ሦስተኛዉ የጥናትና የምርምር ተግባር ማካሄድ ነዉ፤ ማስተማር ነዉ። የቫይማር ዩንቨርስቲ ከባህርዳር ዩንቨርስቲ ጋር የሚሰበሰቡትን ማስረጃዎችና በአጠቃላይ ስራዎች በሙሉ ለባህርዳር ዩንቨርስቲ ለፎክሎርና ለባህል ጥናት እንሰጣለን። ከነሱም ጋር አብረን የጥናትና የምርምር ስራዎችን እንሰራለን፤ እናስተምራለን፤ ጉባዔዎችንና አዉደ ጥናቶችን በጋራ እናዘጋጃለን።

Team GUZO
ሙዚቀኛ ሳሙኤል ይርጋምስል York Tillyer


ከዩንቨርስቲ ጋር የተያያዘ የጥናትና የምርምር ሥራ ነዉ ያሉት ዶክተር ጌቲ ገላዬ የሳሙኤልን ሃሳብ በመደገፍ በጎርጎረሳዊዉ 2014 ዓ,ም የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሙዚቀኛ ሳሙኤል ይርጋን ቫይማር በሚገኘዉ የሙዚቃ ከፍተኛ ተቋም ተጋብዞ የአንድ ሳምንት ሲንፖዚየም ተካሂዶአል።
የጃዝ ሙዚቃ ቅላጼን በፒያኖ የሚቀምረዉ ታዋቂዉ ሙዚቀኛ ሳሙኤል ይርጋ ከያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ተመርቆ ከወጣ 11 ዓመት እንደሆነዉ ይናገራል።


ሳሙኤል እንግዲህ በመጨረሻ በኢትዮጵያ የሙዚቃ መሠረት የት ነዉ በሚል የተለያዩ ባህላዊ ሙዚቃና የሙዚቃ መሳርያን ለማጥናት በጀርመን መንግሥት የሚደገፈዉ «ጉዞ» የተሰኘዉ ጥናት ድጋፍ በማግኘቱ ህልሜ እዉን ሆንዋል ሲል ተናግሮአል። ቃለ ምልልስ የሰጡንን እያመሰገንን፤ ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።


አዜብ ታደሰ


ሸዋዬ ለገሠ