1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጅምላ ጨራሹ የጦር መሣሪያ መርሐ ግብር እና ሊብያ

ቅዳሜ፣ ጥር 29 1996

የሊቢያ መሪ ሞአመር ኤል ጋዳፊ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከለከሉ አውዳሚ የጦር መሣሪያ ለማምረት ሀገራቸው የጀመረችውን ሙከራ በጠቅላላ እንደምታቆም፡ እንዲሁም ይህንኑ የጦር መሣሪያ ዓይነት ለማምረት ያቋቋመቻቸውን ቤተ ሙከራዎች መንበሩ ቪየና ኦስትርያ ለሚገኘው የዓለም አቀፉ የአቶም ኃይል ተቆጣጣሪ ድርጅት ጠበብት ፍተሻ ክፍት እንደሚያደርጉ ስምምነታቸውን የሰጡት ባለፈው ታኅሳስ ወር በኅቡዕ ከዩኤስ አሜሪካና ከብሪታንያ ጋር ዘጠኝ ወራት ሙሉ የፈጀ ድርድር

https://p.dw.com/p/E0l9

ካካሄዱ በኋላ ነበር።

በዚሁ ስምምነታቸውም ሊቢያ በርግጥ ጅምላ ጨራሹን የጦር መሣሪያ ለማምረት ሙከራ ማድረጓን፡ ግን ሙከራዋን ከግብ አለማድረስዋን ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ አምነዋል። ጋዳፊ የአቶም የጦር መሣሪያ ምርት መርሐ ግብርን ለማቆም በተስማማችበት ድርጊትዋም፡ ዩኤስ አሜሪካ ሽብርተኝነትን ይደግፋሉ፡ ያበረታታሉ ከምትላቸው ሀገሮች መደዳ የተቆጠረችበት፡ እንዲሁም፡ እአአ በ 1988 ዓም በሎከርቢ ስኮትላንድ ላይ ሲበር በተከሰከሰው የፓናም መንገደኞች ማመላለሻ አይሮፕላን ላይ ለተጣለው የቦምብ ጥቃት ተጠያቂዎቹ የሊብያ ዜጎች መሆናቸውን በይፋ ካመነች ወዲህ፡ በዚሁ ሰበብ በዓለም አቀፍ ደረጃ የደረሰባት የመገለል ዕጣ እንዲያበቃላትና ወደ ዓለም አቀፉ ኅብረተ ሰብ መድረክ እንደገና እንድትመለስ ተስፋ አድርገዋል። ከሁለት መቶ የሚበልጡት የፓናም አይሮፕላን ተሣፋሪዎች በጠቅላላ ሕይወታቸውን ባጡበት ጥቃት የተነሣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሊብያ ላይ የኤኮኖሚውን ማዕቀብ አሳርፎ ነበር፤ ሊብያም ለጥቃቱ ኃላፊነቱን ባለፈው መስከረም ወር በይፋ ከወሰደችና ለሟቾቹ ቤተ ዘመዶችም ካሁለት ነጥብ ሰባት ቢልዮን ዶላር ካሣ ለመክፈል ከተስማማች በኋላ ነበር ይኸው የዓለሙ መንግሥታት ድርጅት ማዕቀብ የተነሣላት። ዩኤስ አሜሪካም ሊብያ ጅምላ ጨራሹን ዮር መሣሪያ ዓይነት ለማምረት ሙከራ ይዛለች በሚል በተደጋጋሚ በመውቀስ፡ እአአ በ 1986 ዓም በዚችው ሰሜን አፍሪቃዊቱ ሀገር ላይ የኤኮኖሚውን ዕገዳ ማሳረፍዋ አይዘነጋም። በአሜሪካውያኑ ስለላ መረጃዎች መሠረት፡ ሊብያ በዘጠናኛዎቹ ዓመታት ውስጥ ቢያንስ ሁለት የመርዘኛ ንጥረ ነገር ጦር መሣሪያ ማምረቻ ተቋማት እንደነበሩዋት ተመልክቶዋል። የተመድና ዩኤስ ያሳረፉባት ይኸው ማዕቀብም ሊብያን እውድቀት አፋፍ ላይ አድርሶ ነበር። በማዕቀቡ መሠረት፡ እያንዳንዱ የሊብያ ኩባንያ ባያመቱ ከሀያ ሚልዮን ዶላር የበለጠ ንግድ ማካሄድ አይፈቀድለትም ነበር። ዕገዳውን የማያከብሩ መንግሥታትን ተቋማት ዕገዳ እንደሚያርፍባቸው ያስጠነቀቀችው ዩኤስ አሜሪካ፡ በሊብያ ላይ ያረፈውን ማዕቀብ ተግባራዊነት በጥብቅ ነበር የተከታተለችው። የአሜሪካውያኑ ማዕቀብ አሁንም ቢቀጥልም፡ ጋዳፊ ሀገራቸውን የኑክልየር ጦር መሣሪያ ባለቤት ለማድረግ የጀመሩትን ሙከራ ለማቆም ከጥቂት ጊዜ በፊት በገቡት ቃል የተነሣ የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት ሊሻሻል እንደሚችል አሜሪካውያን ባለሥልጣናት ጠቁመዋል። በአሜሪካዊው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እንደራሴ ቶም ላንቶስ የተመራ አንድ የአሜሪካውያኑ የእንደራሴዎች ቡድን ከሠላሣ አምስት ዓመታት በኋላ ከጥቂት ጊዜ በፊት ወደ ሊብያ በመጓዝ በዚያ ከሀገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ሀሳብ ተለዋውጦዋል። ላንቶስ ከውይይቱ በኋላ እንዳስረዱትም፡ ዩኤስ አሜሪካና ሊብያ ያለፈውን ልዩነታቸውን ለመርሣትና ግንኙነታቸውን እንዳዲስ ለማደስ፡ የኋላ ኋላም በመዲናዎቻቸው ዋሽንግተንና ትሪፖሊ ውስጥ ኤምባሲዎችን ለመክፈት የሚችሉበት አመቺው ሁኔታ ጋዳፊ የሀገራቸውን የጅምላ ጨራሹን ጦር መሣሪያ መርሐ ግብርዋን ለማቆም በተስማሙበት ድርጊት ተፈጥሮዋል። ይህ የጋዳፊ ርምጃ ለሰሜን አፍሪቃና ለመካከለኛው ምሥራቅ መረጋጋት ሰፊ ድርሻ እንደሚያበረክት ነው የተገመተው። ጋዳፊም በበኩላቸው ርምጃቸው በመካከለኛው ምሥራቅ የአቶም ጦር መሣሪያ ባለቤት ሳትሆን አትቀርም የምትባለዋን እሥራኤልን፡ ምንም እንኳን እሥራኤል የተባለው የጦር መሣሪያ ይኑራት አይኑራት ከመናገር ብትቆጠብም፡ ተመሳሳዩን ርምጃ እንድትወስድ የሚያበረታታ እንዲሆን ተስፋቸውን ገልፀዋል።
ሊብያ የጅምላ ጨራሹን ጦር መሣሪያ መርሐ ግብር የምትነቃቅልበትን ሥራ በተመለከተ ባጭር ማስታወቂያ በሀገርዋ ሰፊ የፍተሻ ሂደት የሚፈቅደውን የአቶም ጦር መሣሪያ ምርትና ሽያጭን የሚከለክለው ውል ተቀጥላ ሰነድንም ፈርማለች። የዓለም አቀፉ የአቶም ኃይል ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት ጠበብትም የሊብያ የጅምላ ጨራሹ ጦር መሣሪያ መርሐ ግብር የሚፈራርስበትን ሥራ ክንውን ለመከታተል በዚችው ሀገር ይቆያሉ። በዚሁ ሊብያ ከዓለም አቀፉ የአቶም ኃይል ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት ጋር በጀመረችው ትብብር መሠረትም፡ ከጥቂት ሣምንታት በፊት ሀምሳ አምስት ሺህ ፓውንድ የጅምላ ጨራሹ ጦር መሣሪያ መርሐ ግብር ሰነዶችና ለምርቱ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች የያዘ ትልቅ ፓኬት ወደ ቴኔሲ፡ ዩኤስ አሜሪካ በአይሮፕላን ተልኮዋል። ሰበበኛውን ዕቃ የያዘው ትልቁ ፓኬት እአአ በ 1943 ዓም ዩኤስ አሜሪካ የአቶሙን ቦምብ ለማምረት እንዲያስችላት በተዘጋጀውና የማንሃተን ፕሮዤ በተሰኘው ዕቅድ አማካይነት በኅቡዕ ባሠራችው ሕንፃ ውስጥ ተቀምጦዋል።