1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን እና የቀጠር ቀውስ 

ሐሙስ፣ ሰኔ 8 2009

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እንዳሉት ሀገሪቱ የሽምግልና ሚና አይኖራትም። የምትችለውን ማድረጓ ግን አይቀርም። ወደ አንዳቸው ላለማዘንበል ግን መጠንቀቅ እንዳለባት ግልፅ ነው። ሌላው አሳሳቢው ጉዳይ በጀርመን ኩባንያዎች የሚገኘው የቀጠር ገንዘብ ነው።

https://p.dw.com/p/2ekts
Wolfenbüttel Bundesaußenminister Sigmar Gabriel trifft den katarischen Außenminister Scheich Mohammed Al Thani
ምስል Imago/photothek/T. Koehler

Deutschland und die Katar-Krise - MP3-Stereo

የአረብ ባህረ ሰላጤ ሐገራት ከቀጠር ጋር ግንኙነታቸውን ማቋረጣቸው ለጀርመን ብዙ አስቸጋሪ ጥያቄዎችን እያስነሳ ነው። ጥያቄዎቹ ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ናቸው። ሀገራቱ ቀጠርን ማግለላቸው በጀርመን ጥቅሞች ላይ ሊያስድር የሚችለው ጫና እያነጋገረ ነው። በጀርመን ኩባንያዎች ላይ  ተጽእኖዎችን ሊያሳድር ይችላል የሚባለው የቀጠር ቀውስ ለጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስቸጋሪ የፖለቲካ ፈተና ሆኖባቸዋል። 
የአረብ ባህረ ሰላጤ ሐገራት ትንሽቷ ግን በነዳጅ ዘይት የበለፀገችውን ቀጠርን ማግለላቸው ጀርመንን አሳስቧል። ችግሩ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ ሃሳብ ያቀረበችው ጀርመን ሳውዲ አረብያ እና ሌሎችም የአረብ ሀገራት በቀጠር ላይ የጣሉትን የምድር የባህር እና የአየር መስመሮች እገዳ እንዲያነሱ ጠይቃለች። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዚግማር ጋብርየል የቀጠሩን አቻቸውን ሼህ ሞሀመድ አብዱራህማን አል ታኒን  በርሊን ውስጥ ባስተናገዱበት ወቅት ይህንኑ የመንግሥታቸውን አቋም ግልጽ አድርገዋል።
« አሁን  የዲፕሎማሲ ሰዓት መሆኑን በጥብቅ እናምናለን። እናም ርስ በርስ መነጋገር አለብን፣ከአሜሪካን አቻዎቻችን ጋር ከዚያም በላይ በአካባቢው ካሉ ባለስልጣናት ጋር በመነጋገር በተለይ የባህር እና የአየር እገዳው እንዲነሳ መፍትሄዎችን ለመፈለግ መጣር አለብን» 
የጋብርየል ተማጽኖ በአካባቢው የሰፈነው ውጥረት እንዲረግብ የተሰነዘረ መፍትሄ ነው። ሆኖም ጀርመን ለቀጠር ይህን መሰሉን ድጋፍ ማድረጓን ጀርመን ውስጥ የሚቃወሙ ወገኖች አሉ ። የዘመናዊው የመካከለኛው ምሥራቅ ጥናት ማዕከል ሃላፊ ኡልሪከ ፍራይታግ ተቃውሞ ቢኖርም ጋብርየል ይህን ያሉበት ሌላ ምክንያትም አለ ይላሉ።
«በአንድ በኩል የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአንዳንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከበሪታ ካላቸው ድርጅቶች ጋር በመሆን ንግግሮችን የማካሄድ የቆየ ልምድ አለው። ሌላው ደግሞ ጀርመን በሁለቱ ሀገራት( በቀጠር እና በሳውዲ አረብያ) ከፍተኛ የውጭ ንግድ ጥቅሞች አሏት። ይህ ብቻ አይደለም ጀርመን ውስጥ ሰፊ የኳታር መዋዕለ ንዋይ ፍሰት አለ፣ ከቀተር ጋር ሲነፃጸር የሳውዲ አረብያ ውረታ አነስተኛ ነው»
የአልታኒም ሆነ የግብጹ ፕሬዝዳንት የአል ሲሲ እና የሳውዲ አረብያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአዴል አል ጁቤር የቅርብ ጊዜያት የበርሊን ጉብኝቶች ጀርመን የምትፈለግ የንግግር አጋር መሆንዋን ያሳያል።  የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እንዳሉት ግን ሀገሪቱ የሽምግልና ሚና አይኖራትም ።  የምትችለውን ማድረጓ ግን አይቀርም። ወደ አንዳቸው ላለማዘንበል ግን መጠንቀቅ እንዳለባት ግልፅ ነው። ሌላው አሳሳቢው ጉዳይ በጀርመን ኩባንያዎች የሚገኘው የቀጠር ገንዘብ ነው። ቀጠሮች ከወረቱባቸው የጀርመን ኩባንያዎች መካከል ዶቼ ባንክ ሲመንስ እና ፎልክስ ቫገን ይገኙበታል።  ምናልባት ሲመንስ ገንዘቡን ሳውዲ አረብያ ውስጥ የኢንጅነሪንግ ኩባንያ ለመትከል ሊጠቀምበት ይችላል? በዶቼ ባንክ ውስጥ ያላቸው የአክስዮን ድርሻስ ምን ያህል ነው? በፎልክስ ቫገን ኩባንያ ተቆጣጣሪ ቦርድ ውስጥ ሁለት ቀጠሮች መቀመጫ አላቸው። ቀጠሮች ገንዘብ ቢያስፈልጋቸው እና ድንገት ቢያወጡት ምን ይፈጠራል? ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ቀጠር አሸባሪዎችን ትደግፋለች የሚል አቋም ከያዘ ጀርመን ውስጥ ያለው የቀጠር መዋዕለ ንዋይ ላይ ምን ተጽእኖ ይኖረዋል ? ጉዳዩ የሚመለከታቸው የጀርመን ድርጅቶች ብዙውን ጊዜ የአረብ ባለወረቶችን በሚመለከት ምንም አይናገሩም። ዶቼ ባንክ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት አንሰጥም ነው ያለው። ቀጠር በዶቼ ባንክ 9 በመቶ  በፎክስ ቫገን ደግሞ 17 በመቶ ፣ በሲመንስ ደግሞ 3.3 በመቶ ድርሻ ድርሻ አላት። ያም ሆኖ በሀለ ዩኒቨርስቲ የዓለም ዓቀፍ የንግድ ግንኙነቶች መምህር ማርቲን ክላይን እንደሚሉት የቀጠር ቀውስ ለጀርመን ኩባንያዎች አሳሳቢ አይደለም ። 
«እንደሚመስለኝ ኩባንያዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ምንም ዓይነት ለውጥ ይኖራቸዋል ተብሎ አይጠበቅም። ቀጠርም ከቀውሱ ጋር በተያያዘ በኤኮኖሚያዊም ሆነ በፖለቲካዊ ምክንያት ውረታዋን ታቆማለች ተብሎም አይጠበቅም። ከዚህ በመነሳት የቀጠር ቀውስ በጀርመን ኩባንያዎች ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ አነስተኛ ነው ብዮ ነው የማምነው።»

Symbolbild Volkswagen Investitionen
ምስል picture-alliance/dpa/Jochen Lübke
Symbolbild Das Logo der Deutschen Bank
ምስል picture-alliance/dpa/F. Rumpenhorst
Wolfenbüttel Bundesaußenminister Sigmar Gabriel trifft den katarischen Außenminister Scheich Mohammed Al Thani
ምስል Imago/photothek/T. Koehler

ሃይነር ኪዝል/ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ