1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን ለአፍሪቃ ያሰበችው ውረታ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 1 2009

አፍሪቃን ለማገዝ የተነደፉት የሦስቱ የጀርመን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ሀሳቦች የግል ባለሀብቶችን ተሳትፎ ማሰደግ እና ሁለቱንም ወገኖች አትራፊ ማድረግ ነው እቅዳቸው። ይሁን እና ይህ ብቻውን የአፍሪቃን የልማት ችግሮች ለማቃለል በቂ ነው ብለው አያስቡም።

https://p.dw.com/p/2ceeS
Deutschland Brenda Otieno
ምስል DW/H. Shuen Lee

ጀርመን ለአፍሪቃ ያሰበችው ውረታ እና ትችቱ

 የአውሮጳ ሀገራት ህገ ወጥ የሚሉትን ከአፍሪቃ ወደ አውሮጳ የሚደረግ ስደት ለማስቆም የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ናቸው። የአፍሪቃ ስደተኞች በሜዴትራንያን ባህር በኩል በብዛት ወደ አውሮጳ መሰደድ ከጀመሩበት ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ጀርመንን የመሳሰሉ ሀገራት ጥብቅ የድንበር ቁጥጥር ተግባራዊ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ ብዙ ገንዘብ እየተቀበሉ ሰዎች በአደገኛ ጉዞ እንዲሰደዱ የሚያደርጉ ሰው አሻጋሪዎችን በማደን ለፍርድ እያቀረቡም ነው። ከዚህ ሌላ ችግሩን ከምንጩ በዘላቂነት ሊከላከሉ ይችላሉ ያሏቸውን ሃሳቦችም እያቀረቡ ነው። በዚህ ረገድ የስደተኞች መነሻ እና መተላለፊያ በሆኑ የአፍሪቃ ሀገራት ሊያካሂዱ ያቀዷቸው ውጥኖች ተጠቃሽ ናቸው።ጎሮጎሮሳዊውን 2017 ለአፍሪቃ ትኩረት የሰጠችበት ዓመት ያደረገችው ጀርመን በሦስት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቿ አማካይነት በአፍሪቃ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትን ያበረታታሉ ሥራም መፍጠር ያስችላሉ ያለቻቸውን ንድፈ ሀሳቦች አቅርባለች። በጀርመን የኤኮኖሚ ሚኒስቴር የቀረበው «ፕሮ አፍሪቃ» የተባለው ንድፈ ሀሳብ አንዱ ሲሆን፣ የጀርመን የገንዘብ ሚኒስቴር ያሰናዳው «ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ» እንዲሁም የጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ማርሻል ፕላን ከአፍሪቃ ጋር የተሰኙትም ሁለተኛ እና ሦስተኛዎቹ ንድፈ ሀሳቦች ናቸው። የዶቼቬለ የበርሊን ዘጋቢ ይልማ ኃይለ ሚካኤል እንደሚለው የተለያዩ የጀርመን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ያዘጋጇቸው የእነዚህ ውጥኖች ዓላማዎች ተመሳሳይ እና ተደጋጋፊም ናቸው። በርሱ አገላለጽ ለአንደኛው ሀሳብ አፈጻጸም ሌላኛው ንድፈ ሀሳብ አስፈላጊ ነው።  
የጀርመን የኤኮኖሚ ሚኒስትር የብሪጊተ ትሲፕሪስ  መሥሪያ ቤት ያቀረበው «ፕሮ አፍሪቃ» የተባለው ንድፈ ሀሳብ ዓላማ በጀርመን እና በአፍሪቃ መካከል እኩል የኤኮኖሚ አጋርነት መፍጠር ነው። አፍሪቃ የጀርመን እኩል አጋር ተደርጋ እንደምትቆጠር ያሳወቀው መሥሪያ ቤቱ ያቀረበው ሀሳብ፣በአፍሪቃ የግሉን ዘርፍ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ማበረታት እና ሥራ የመፍጠር ዓላማ እንዳለው ተገልጿል። የጀርመን የገንዘብ ሚኒስትር ቮልፍጋንግ ሾይብለ መሥሪያ ቤት ያሰናዳው ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ የሚል ስያሜ የተሰጠው ንድፈ ሀሳብም ዓላማ በጥቅሉ በአፍሪቃ ለአስተማማኝ የግል ውረታ የሚያስፈልጉ መሠረታዊ  ሁኔታዎችን ማሻሻል ነው። ከዚሁ ጋር በክፍለ ዓለሙ በመሠረተ ልማት ዘርፍ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትን ማጠናከር እና የሥራ እድል መፍጠር ከዓላማዎቹ ውስጥ ይካተታሉ። በዚህ ሥራም ፍላጎቱ ያላቸውን የአፍሪቃ ሀገራት ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች እና ሌሎች አጋር ሀገራትን ለማሳተፍ ታስቧል። በአሁኑ ጊዜ ሦስት የጀርመን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አፍሪቃን የተመለከቱ ጉዳዮችን አጀንዳቸው አድርገው ለማቅረብ ፉክክር ላይ ያሉ ይመስላል። ይህም ለአፍሪቃ እገዛ ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉትን ወገኖችን ሲያስደስት በሌላ በኩል ደግሞ ሦስቱ ንድፈ ሀሳቦች በአንድ ላይ አለመቀናጀታቸው ወይም በአንድ መሥሪያ ቤት መሪነት አለመያዛቸው መተቸቱ አልቀረም። ሀሳቦቹ የታሰበላቸውን ዓላማ ማሳካት መቻላቸው ያሳሰባቸው አፍሪቃውያን አልጠፉም። ናሻሊላ ኑኩምቦ ONE ዋን የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ናቸው። በርሳቸው አስተያየት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ በአፍሪቃ ጉዳይ ላይ ማተኮራቸው እሰየው የሚያሰኝ ነው። ሆኖም ንድፈ ሀሳቦቹ ግባቸውን መምታት አለመምታታቸው ያሳስባቸዋል።
«ሦስቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በአፍሪቃ ታሪክ አስፈላጊ በሆነው ጉዳይ ላይ ፍላጎት ማሳየታቸው በጣም ትልቅ ነገር ነው። ሆኖም ይህ በሚቀጥሉት ዓመታት አፍሪቃ ውስጥ እውን ሊሆን ለሚገባው ለትልቁ የልማት ዓላማ በቂ መሆን አለመሆኑ ያሳስበናል።»
ከዚሁ ጋር የንድፈ ሃሳቦቹ አለመቀናጀት እንደ አንድ ድክመት ይነሳል።  ባለፈው ሳምንት ደርባን ደቡብ አፍሪቃ በተካሄደው የአፍሪቃ የኤኮኖሚ  ጉባኤ ላይ የተገኙት  የጀርመን የገንዘብ ሚኒስትር ቮልፍጋንግ ሾይብለ ግን ሥራዎች በቅንጅት ነው የሚካሄዱት ብለዋል።
«እርግጥ ነው ሦስት የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው ። ሆኖም በተገቢው ሁኔታ የተቀናጁ ናቸው ።»
የጀርመን የኤኮኖሚ ሚኒስትር ቢርጊተ ትሲፕሪስ እንዳሉት ደግሞ የሦስቱን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ሃሳቦች ወደ አንድ የጋራ ስልት የማጠቃለል ሥራ እየተካሄደ ነው።
«ይህን የጋራ ስልት የማዳበር ሂደት ላይ ነው ያለነው። ሥራውን የማቀናጀቱን ሃላፊነት የመራሄ መንግሥት ጽህፈት ቤት ወስዷል ። የመራሄ መንግሥቱ ጽህፈት ቤት አመራር፣ በቅርቡ ከነዚህ ሦስት ንድፈ ሀሳቦች ውስጥ ፣ ውጤታማ የሚሆን አንድ ስልት ያወጣል የሚል ተስፋ አለኝ።»
አፍሪቃን ለማገዝ የተነደፉት የሦስቱ የጀርመን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ሀሳቦች የግል ባለሀብቶችን ተሳትፎ ማሰደግ እና ሁለቱንም ወገኖች አትራፊ ማድረግ ነው እቅዳቸው። ይሁን እና ዋን የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ናሻሊላ ኑኩምቦ እንደሚሉት ይህ ብቻውን የአፍሪቃን የልማት ችግር ለማቃለል በቂ ነው ብለው አያስቡም።
«ተጨማሪ የጀርመን መዋዕለ ንዋይ ፍሰት መኖሩ ጥሩ ነው ። ሆኖም ይህ በቂ አይደለም ። ድህነት በሚያጠቃቸው የአፍሪቃ ክፍሎች የሚኖሩ በርካታ ሰዎች አሉ። እነዚህ አካባቢዎች ሌሎች ከተሞች የደረሱበት የእድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ አሁንም ከእርዳታ ጋር ግንኙነት ያላቸው መንግሥት እራሱ መዋዕለ ንዋይ የሚያፈስባቸው ውረታዎች ያስፈልጓቸዋል። የጀርመን የግል ባለሀብቶች ሰሜን ናይጀሪያ ውስጥ ያለ ኤሌክትሪክ ወይም መንገድ አለያም ሌሎች መሠረተ ልማቶች የሌሉበት አካባቢ ይገባሉ ብለን አንጠብቅም። ስለዚህ እኛ የምንለው የግል ባለሀብቶች መምጣታቸው ተቀባይነት አለው። ሆኖም ይህ እርዳታ እና የአፍሪቃ መንግሥታት ተሳትፎ ካልታከለበት ብቻውን ውጤታማ አይሆንም። »
እነዚህን የመሳሰሉ ትችቶች የቀረቡባቸው የሦስት የጀርመን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ሀሳቦች ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ የአፍሪቃ ሀገራትም ተለይተዋል። መስፈርቶቹም እንዲሁ። ይሁን እና  ይልማ እንደሚለው እነዚህ በጥድፍያ የቀረቡ የሚመስሉት ንድፈ ሃሳቦች በመጪው መስከረም ከሚካሄደው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ውጤት በኋላ እጣ ፈንታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ማሳሰቡ አልቀረም። ግን ደግሞ ወደፊት ወደ አውሮጳ ሊመጣ ይችላል ተብሎ የሚያሰጋው ስደተኛ ጉዳይ እረፍት የሚነሳ በመሆኑ ጥረቱ ይቀጥላል እንጂ አይቋረጥም የሚል ግምት ነው ያለው። 

re:publica 2017
ምስል picture alliance/dpa/B.Pedersen
Entwicklungshilfe Gerd Müller
ምስል picture-alliance/dpa/K. Nietfeld
Südafrika Weltwirtschaftsforum in Durban Wofgang Schäuble
ምስል Reuters/R. Ward

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ