1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጽእኖ እስከመፍጠር ደርሰዋል”

ሰኞ፣ ግንቦት 21 2009

የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚዎችን ሲያወዛግብ የሰነበተው የዶ/ር ቴድሮስ አድሓኖም የምርጫ ጉዳይ መቋጫ አግኝቷል፡፡ የዓለም የጤና ድርጅትን ለመምራት “የምረጡኝ ዘመቻ” ሲያደርጉ የቆዩት የቀድሞው ሚኒስትር ያለሙትን አሳክተዋል፡፡ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የነበረው ስሜት ምን ይመስላል? ድጋፍ እና ተቃውሞው የነበረው አንደምታስ?፡፡ 

https://p.dw.com/p/2da7a
Tedros Adhanom Ghebreyesus
ምስል Picture alliance/Keystone/V. Flauraud

ዶ/ር ቴድሮስ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ዓይን

ማክሰኞ ግንቦት 15 ቀን 2009 ዓ.ም፡፡ የዓለም ትኩረት በብሪታንያ ማንቸስተር ላይ ሆኗል፡፡ በከተማይቱ በተካሄደ የሙዚቃ ዝግጅት ማጠናቀቂያ ላይ በፈነዳ ቦምብ ስለሞቱት፣ ስለቆሰሉት እና ስለአደጋው መረጃ በመቀባበል ተጠምዷል፡፡ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ቀልብ የነበረው ግን ከማንችስተር በሁለት ሰዓት በረራ ከሚደረስባት ዤኔቭ ከተማ ላይ ነበር፡፡ የስዊትዘርላንዷ ዤኔቭ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) መቀመጫ ናት፡፡ በዚያ ደግሞ ኢትዮጵያዊው የቀድሞ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሓኖም የድርጅቱን የኃላፊነት ቦታ ለመጨበጥ ለመጨረሻው ፉክክር ቀርበዋል፡፡ 

ከደጅ ደጋፊዎቻቸው ባንዲራዎችንና ፎቶዎችን ይዘው ተሰልፈዋል፡፡ የተወሰኑ ኢትዮጵያውያን የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ከአንድ ቀን በፊት በዚያው ድርጅት ደጃፍ ስለተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ በማንሳት በዶ/ር ቴድሮስ ላይ ትችቶችን ማዝነብ ቀጥለዋል፡፡ በድርጅቱ ሰባኛ መደበኛ ስብሰባ መክፈቻ ላይ በኃይለ ቃል ተቃውሟቸውን ስላሰሙት ኢትዮጵያዊ አክቲቪስት ዘለላም ተሰማ በሁለት ጎራ የተከፈሉ አስተያየቶች እየተዥጎደጎዱ ነው፡፡ የስብሰባው ስነ-ስርዓት በድረ-ገጽ በቪዲዮ በቀጥታ የሚተላለፍ ነበርና እርሱን በፌስቡክ ገጻቸው በማጋራት ሂደቱን በትኩረት የሚከታተሉም ነበሩ፡፡ 

Schweiz Exil-Äthiopier protestieren gegen neuen WHO-Generaldirektor
ምስል Reuters/P. Albouy

ንግግሮች እና ሌሎች ስነ-ስርዓቶች ተጠናቅቀው ወደ ድምጽ መስጠት ስነ-ስርዓት ሲገባ ቀጥታ የቪዲዮው ስርጭት በመቆሙ በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ እና ውጭ የነበሩ ታዳሚዎች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚያስተላልፏቸውን መረጃዎች ላይ መመርኮዝ ግድ ሆነ፡፡ በዚህ የመረጃ ቅብብሎሽ ውስጥ ባልተለመደ መልኩ መንግስት የሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙሃን እና አጋሮቻቸው ከፍተኛ ተሳትፎ ሲያደርጉ ታይተዋል፡፡ በሶስት ዙር ከተካሄደ ምርጫ በኋላ የዶ/ር ቴድሮስ ማሸነፍ ይፋ ሲደረግ ፌስ ቡክ እና ትዊተር በ“እንኳን ደስ ያላችሁ” መልዕክትና መረጃውን በሚያጋሩ ሰዎች ተጥለቅልቆ ታይቷል፡፡

ሁሉም ነገር ሰከን ሲል ግን የዶ/ር ቴድሮስን ማሸነፍ እና አንደምታውን ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመለከቱ አስተያየቶች ለንባብ በቅተዋል፡፡ የዶ/ር ቴድሮስን መመረጥ ሲደግፍ የቆየው ዘውዳለም ታደሰ ከምርጫው በኋላ በፌስ ቡክ ገጹ ተከታዩን አስፍሯል፡፡ “ዶክተሩን ስመርጥ የኔ አንድ ድምጽ በጆንያ ውስጥ እንዳለች የጤፍ ቅንጣት እንኳ ዋጋ እንደማታወጣ ባውቅም አንድን ሰው ከዘርና ከፖለቲካ አመለካከቱ በላይ አሻግሬ ማየት እንደምችል አረጋግጣልኛለች፡፡ ኢህአዴግ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ በሞኖፖል የተቆጣጠረውን ስልጣን ለህዝብ እንዲያስረክብ እፈልጋለሁ፡፡ በዚያው ልክ ጥላቻና ዘር ተኮር ተቃውሞውን እጸየፋለሁ፡፡ ቴዎድሮስ ካሳሁንንም ቴድሮስ አድሓኖንምንም እኩል መውደድ ይቻላል” ሲል ጽፏል፡፡ 

አንድ ኢትዮጵያዊ ለዓለም አቀፍ ኃላፊነት በመመረጡ ደስታውን በመግለጽ የጀመረው የፊልም አዘጋጅ እና አርታኢው ያሬድ ሹመቴ በበኩሉ “ከስሜት ወረድ ብለን እናውራ” ባለበት የፌስ ቡክ ጽሁፉ ይህንን ብሏል፡፡ “ሰሞኑን ያልተነበበ ስድብ፣ ያልታየ ብሽሽቅ፣ ያልተደረገ ክርክር የለም። በሁለቱም ወገን ከአመክንዮ በታችም ከአመክንዮም በላይ የሆኑ እሰጣ ገባዎችን አይተናል። አልገባንም እንጂ፣ ይህ የዴሞክራሲ አንዱ ባህል ነው። የሚያሳዝነው በሀገራችን ውስጥ ይህ አይነት የጋለ ስሜት የሚፈጥር የዴሞክራሲ ባህል ለማየት አልታደልንም። በድል መንፈስም፣  በንዴት መንፈስም ውስጥ ሆኖ ትምህርት መውሰድ ተገቢ ይመስለኛል። ምኞትም ብንመኝ ጥሩ ነው። ሀገሬ ኢትዮጵያ ውጤቱ የማያከራክር ምርጫ ይስጥሽ!” 

Tedros Adhanom Ghebreyesus Außenminister Äthiopien
ምስል Getty Images/AFP/F. Coffrini

ዶ/ር ቴድሮስ የተመረጡት በምስጢር በተሰጠ ድምጽ ይሁን እንጂ ከ185 አባል ሀገራት መካከል በእያንዳንዱ ዙር ምን ያህል ድምጽ እንዳገኙ በይፋ ይገለጽ ነበር፡፡ እንደ ያሬድ ሁሉ ይህ ግልጽ የምርጫ አካሄድ ሌሎች ኢትዮጵያውያንንም የማረካቸው ይመስላል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ወሰንሰገድ ገብረኪዳን ነው፡፡ “የWHO ምርጫ ምንድን ነው የሚያስተምረን?” ሲል ይጠይቅና ምላሹን ራሱ ይሰጣል፡፡ “መልሱ ቀላል ነው። መቶ በመቶ ማሸነፍ ብሎ ነገር እንደሌለ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላው ትርጉም የለውም!” ይላል፡፡  

አለማየሁ ገመዳ በበኩሉ “ጎበዝ በተጭበረበረ ምርጫም በነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫም ተሸንፈህ ትችለዋለህ እንዴ? መፍትሔ ፈልግ እንጂ!” ሲል ዶ/ር ቴድሮስን ለተቃወሙ ወገኖች ማክሰኞ ዕለት የቤት ስራ ለመስጠት ሞክሯል፡፡ በዚያው ቀን በፌስ ቡክ ባወጣው ሌላ ጽሁፍ “ ʻቴድሮስ ለዓለም ጤና ድርጅት አይሆንምʼ ከሚለው ዘመቻ ሽንፈት መወሰድ ያለበት ትልቁ ትምህርት የምንታገለልለትን ነገር መምረጥ እንዳለብን ነው፡፡ ሁሉም ትግሎች ለእኛ ዋጋ አላቸው ማለት አይደለም፡፡ ቅድሚያ መስጠት ያለብንን ማወቅ አለብን፡፡ አብዛኛውን ሃይላችንን ማዋል ያለብን አንድን ነገር ለመቃወም ሳይሆን ለቆምንለት ነገር በመታገል መሆን አለበት። ይህንን ዘመቻ ያልደገፍኩበት ምክንያት ለተወሰኑ እሴቶች ማቀንቀን እና በእነርሱ ዙሪያ መሰለፍን በማመኔ ነው፡፡ በእኔ አስተያየት ይህ ይበልጥ የተከበረ እና ለእኛ ዓላማ ጠቃሚ ነው” ሲል ተቃውሞ ለሚያሰሙ ሰዎች ምክር ለግሷል፡፡  

ኢትዮጵያውያን በሁለት ወገን ሆነው መቆራቆዛቸው ያሳሰባቸው ቢኒያም ሂሩት ደግሞ መንግስት ዶ/ር ቴድሮስ ላይ ከታየው ተቃውሞ መማር የሚገባውን ጠቁመዋል፡፡ “የዶ/ር ቴድሮስ የአለም ጤና ድርጅት ውድድር ለኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ለህዝቦቿ አስደንጋጭ መልእክት አስተላልፏል፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ለእንደዚህ አይነት ትልቅ ቦታ ሲወዳደር የመንግስት የቁጥጥር ቀጣና እና ፌዴራል ፖሊስ በሌለባቸው ቦታዎች ሁሉ (በውጪ ሀገር) እጅግ ተቃውሞ ሲሰማ ነበር፡፡ ዶ/ሩ እንዳይመረጡ የተሰራው ስራ እንደ ኢትዮጵያዊ ቢያሳዝነኝም በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየመረረና እየከረረ የመጣውን ተቃውሞ ብቻ ሳይሆን ጥላቻንም ያሳየ ነው፡፡ ወንድሞቼን ለምን ተቃወሙ ብዬ መናገር አልችልም፡፡ መንግስት ግን ለምን ራሱ የማይቆጣጠራቸው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እንደዚህ አምርረው እንደሚጠሉት ራሱን መጠየቅ ያለበት ይመስለኛል፡፡ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ቆም ብሎ ማሰብም ይፈልጋል፡፡ ውጪ ያሉት እንደዛ ከጠሉት ሀገር ውስጥ ያሉት እንዴት ይሆን ብሎ መጠየቅ ይገባል፡፡ የዳያስፖራው በጣም በመደራጀት መንግስት ላይ የሚያሳርፈው በትር ወደ ህመም ከመለወጡ በፊት መንግስት ህዝቡን ይስማ፣ ማስተካከል ያለበትን ነገር ያስተካክል፡፡”

Tedros Adhanom Ghebreyesus ehem. Außenminister Äthiopien
ምስል DW/T. Woldeyes

 የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃኖች ንቁ ተሳታፊ የሆነውና ዶ/ር ቴድሮስን በግልጽ ሲደግፍ የቆየው መርከብ ነጋሽ ኢትዮጵያውያን በቀድሞው ሚኒስትር ዙሪያ ባላቸው አቋም በሁለት ወገን ቆመዋል በሚለው አይስማማም፡፡  

“ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ የነበረውም ቢሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ለሁለት ተከፍሎ ነበር የሚለው ግምገማ የማይዋጥልኝ ነው፡፡ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ ያለው እንኳ ከመንግስት ፖሊሲ ጋር ተስማማም አልተስማማም ዶ/ር ቴድሮስን እየደገፈ የነበረ ነው፡፡ በአብዛኛው እኔ ያየሁት የህዝቡን ጨዋነት እና ብሔራዊ ጥቅም ላይ ከሞላ ጎደል የማይደራደር መሆኑን ነው፡፡ ከማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ውጭ እኔ ብዙ ሰዎች አገኛለሁ፡፡ ይህንን ሂደት በጣም ሲከታተሉ የነበረው አብዛኞቹ እንደውም የመንግስት ደጋፊ ያልሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡ ብዙ ሰዎች ይወዷቸዋል፡፡ በጣም ብዙ ሰዎች እንዲያሸንፉ ይፈልጉ ነበር፡፡ የድሉ ቀን ማታም አዲስ አበባ ውስጥ የነበረው ስሜት እንደዚያ ነው” ይላል መርከብ፡፡  

ልዩነቶች እንደነበሩ የማይሸሽገው መርከብ በተለይ በሳይበሩ ዓለም “ጽንፈኝነት” ታይቷል ባይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እርሱን መሰል ተስፈኞችን ተስፋ የማስቆረጥ ስሜት ውስጥ እንደከተታቸው ይናገራል፡፡ የዩኒቨርስቲ መምህሩ እና ጦማሪው ስዩም ተሾመ በዶ/ር ቴድሮስ ላይ በማህበራዊ ድረ-ገጾች የታየው ተቃውሞ ለኃላፊነት ከተፎካከሯቸው ዕጩዎች የውድድር ስልት በላይ “ትልቁ ፈተና” እንደነበር ጽፏል፡፡ “ዶ/ር ቴድሮስ ያሸነፈባቸው አራት ምክንያቶች እና ማህበራዊ ሚዲያዎች” በሚል ርዕስ ያወጣውን ይህን ጽሁፍ ብዙዎች ተቀባብለውታል፡፡ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሚና እየጎላ መምጣቱን በተመለከተ ስላነሳው ነጥብ እንዲህ ያብራራል፡፡ 

“እነዚህ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዜጎች ሀሳባቸውን፣ አቤቱታቸውን፣ ድጋፋቸውን ጭምር የሚገልጹባቸው መድረኮች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች፣ ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ላይም የመወያያ መድረክ ከመሆንም አልፈው ተጽእኖ እስከመፍጠር ደርሰዋል፡፡ ከዚያም አልፎ ለዋና ዋና የኤሌክትሮኒክስ እና የህትመት መገናኛ ብዙሃንም እንደግብዓት እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ከዶ/ር ቴድሮስ ጋርም በተያያዘ የፖለቲካ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖር የተደረገበት ነው፡፡ በእዚህም የተለያዩ ወገኖች የእርሳቸውን በእጩነት መቅረብ ደግፈው የቀረቡ አሉ፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የተካሄደበት አለ፡፡ ግን ማህበራዊ መገናኛ ሰዎች በዋናነት በትክክል ሀሳባቸውን የሚገልጹበት መድረክ እየሆነ መምጣቱን ግልጽ አድርጓል ብዬ አስባለሁ” ይላል ስዩም፡፡ 

Tedros Adhanom Ghebreyesus Außenminister Äthiopien
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

ዶ/ር ቴድሮስ የብዙዎች ዓይን እንዲያርፍባቸው ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ ለማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ያላቸው ቅርበት ነው፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ከነበሩ ጊዜ ጀምሮ በፌስቡክና ትዊተር በመደበኛነት ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡ በኢትዮጵያውያን ባለስልጣናት ዘንድ ባልተለመደ ሁኔታ አመለካከቶቻቸው እና የግል ድርጊቶቻቸውን ያጋራሉ፡፡ ሁነቶችን አስታክከው መልዕክቶቻቸውን ያስተላልፋሉ፡፡ ስለዶ/ር ቴድሮስ የማህበራዊ መገናኛዎች ተሳትፎ በአንድ ወቅት አብሯቸው የሰራውን መርከብ ነጋሽን ጠይቄዋለሁ፡፡   

“[ከባለስልጣናት መካከል] እርሳቸው ብቻ ናቸው ማህበራዊ መገናኛዎችን በንቃት የሚጠቀሙት፡፡ እንደምታውቀው የሁሉም ሰው ስድብ እርሳቸው ጋር ነው የሚሄደው፡፡ ጭራሽ ማህበራዊ መገናኛዎች ላይ ‘ሰውየው ስራ የላቸውም እንዴ?’ የሚሉ አሉ፡፡ የሚገርምህ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ሆነው አንድ እንግዳ አግኝተው ሌላ እንግዳ እስኪመጣ ድረስ ባሉት ደቂቃዎች ውስጥ ሌላ ሰው ማኪያቶ እና ቡና በሚጠጣበት ሰዓት ነው ስላለው ሂደት አዲሱን ነገር የሚያሳውቁት፡፡ ከህዝቡ እና ከማህበረሰቡ ጋር በቅርብ ለመገናኘት መሞከሩን በጣም አተኩረው ይሰሩበት ነበር፡፡ ያው ሁሌም ራሳቸው ናቸው ትዊት የሚያደርጉት ማለት አይቻልም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ግን ራሳቸው ናቸው ለመጻፍ እና ለመመለስ የሚሞክሩት፡፡ ይህ በመጨረሻ ክሷቸዋል ብዬ አስባለሁ” ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ በእርግጥም በማህበራዊ መገናኛዎች ከመንግስት ባለስልጣናት ከፍተኛ ተከታይ በማግኘት ቀዳሚነቱን ይዘዋል፡፡ በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጻቸው 922 ሺህ ገደማ፣ በትዊተር ደግሞ 232 ሺህ ገደማ ተከታታይ አላቸው፡፡ ነሸጥ ሲያደርጋቸው ለተከታዮቻቸው ዘፈን ሁሉ የሚጋብዙት ዶ/ር ቴድሮስ በቅርቡ ሻኪራ በደቡብ አፍሪካ ለተካሄደው የዓለም ዋንጫ ያቀነቀነችውን “Waka Waka” መርጠው ነበር፡፡ የዘፈኑ ተለዋጭ መጠሪያ የሆነውን “This is time for Africa” በምርጫ ዘመቻቸው ማብቂያ ሲደጋግሙት ተስተውለዋል፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ