1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከታገቱት የጋምቤላ ህጻናት መካከል 68ቱ አሁንም አልተገኙም

ሰኞ፣ ጥቅምት 14 2009

ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ከጋምቤላ ታፍነው ወደ ደቡብ ሱዳን ከተወሰዱ ህጻናት መካከል ስድሳ ስምንቱ አሁንም ድረስ ያሉበት እንደማይታወቅ ጉዳዩን የሚከታተለው የተባበሩት መንግስታት ቡድን አስታወቀ፡፡ ህጻናቱ ለባርነት ይዳረጋሉ የሚል ስጋቱንም ገልጿል፡፡

https://p.dw.com/p/2ReXn
UNHCR Flüchtlingslage in Gambella Äthiopien
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

 

 

ከመንፈቅ በፊት በጋምቤላ ጂካዎ እና ላሬ ወረዳዎች ባሉ 13 መንደሮች ውስጥ ከደቡብ ሱዳን በመጡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት 208 ሰዎች መገደላቸውን 80 ሰዎች መቁሰላቸው ተገልጾ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በወቅቱ ባወጣው መግለጫ ጥቃቱን ያደረሱት ታጣቂዎች 125 ህጻናትን አግተው ወደ ደቡብ ሱዳን እንደወሰዷቸው አስታውቋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ቡድን በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ግን የታጋቾቹን ህጻናት ቁጥር 159 አድርሶታል፡፡ 

የቡድኑ አባል የሆኑት እና በተባበሩት መንግስታት የህጻናት ሽያጭ ልዩ አጥኚ የሆኑት ሙውድ ደቡር ቡኪቺዮ ለዶቸ ቨይለ እንደገለጹት ቁጥሩ ሊጨምር የቻለው ቡድኑ ከአከባቢው በሰበሰበው እና ከታማኝ ምንጮች ባገኘው ተጨማሪ መረጃ መሰረት ነው፡፡

 “የተባበሩት መንግስታት በአካባቢው ላይ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ ግልጽ ነው፡፡ ከዚያ በተጨማሪም ዩኒሴፍ የተሰኘ [ህጻናት ላይ] ትኩረት የሚያደርግ ድርጅት አለን፡፡ ግኝታችን የተመሰረተባቸው በርካታ ምንጮች አሉን፡፡ ታፍነው ስለተወሰዱ ወንድ እና ሴት ህጻናት መጀመሪያ ላይ የነበረን ቁጥር አነስተኛ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ቁጥራቸው ከተነገረው በላይ እንደሆነ መረጃ አግኝተናል፡፡ ከታማኝ ምንጮች ባገኘነው መረጃ መሰረት በአሁኑ ወቅት ስድሳ ስምንት ያህሉ እስካሁንም ያሉበት አይታወቅም፡፡

ከጋምቤላ ታግተው ከተወሰዱ ህጻናት መካከል ለሁለት ወር በተደረገ የማስመለስ ዘመቻ 91 ያህሉ ብቻ ወደ ጋምቤላ መመለሳቸውን እና ቀሪዎቹን ህጻናት “የማዳን እንቅስቃሴ መቋረጡ”ን የተባበሩት መንግስታት ቡድን በመግለጫው ጠቅሷል፡፡ ቡኪቺዮ ጉዳዩ ቸል መባሉ “እንደሚያሳሰባቸው” ይናገራሉ፡፡

 “እኔን በተለይ ያሳሳበኝ የ86ቱ ቀሪ ህጻናት ዕጣ ፈንታ ነው፡፡ እነዚህ ህጻናት የት እንዳሉ ማንም አያውቅም፡፡ ከእገታው በኋላ ህጻናቱ ለሽያጭ የመቅረባቸው ስጋት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ እንኳንስ እነዚህን ህጻናት አስለቅቆ ከቤተሰባቸው እና ከማህበረሰባቸው ጋር መቀላቀል ይቅርና ያሉበትን ቦታ ለማወቅ የሚደረግ ጥረት ሲደረግ አይሰተዋልም፡፡ በዚህ በጣሙኑ ቅሬታ ገብቶኛል፡፡

ቡድኑ ይህን መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን መንግስታት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ለማድረግ መሆኑን ቡኪቺዮ  ያስረዳሉ፡፡ “ሁለቱም መንግስታት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ወሎችን ፈራሚ እንደመሆናቸው የህጻናቱን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው” ሲሉ ልዩ አጥኚዋ ይገልጻሉ፡፡ “ህጻናቱ በቶሎ ወደቤተሰባቸው ወይም ወደቀያቸው ካልተመለሱ በታገቱበት ቦታ ለባርነት የመሸጥ አሊያም ለሌሎች ጥቃቶች የተጋለጡ ይሆናሉ” ሲሉ ስጋታቸውን ያጋራሉ፡፡  

 “እንደ እድሜያቸው እና ጾታቸው የሚወሰን ቢሆንም ባሪያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሴት ህጻናት ብዙውን ጊዜ ለግዳጅ ጋብቻ የተጋለጡ ናቸው፡፡ ወሲባዊ ብዝበዛም ሊደርስባቸው ይችላል፡፡ ይህ በወንድ ልጆች ላይም ሊተገበር የሚችል ነው፡፡ የቤት ውስጥ አገልጋይ እንዲሆኑ ሊገዱዱ ይችላሉ፡፡ ህጻናቱ ደግሞ ያለውዴታቸው ማደጎ ይሆናሉ፡፡

Südsudanesische Flüchtlinge in Gambella
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

የሚያዝያውን ጥቃት ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት ባወጣው መግለጫ ድርጊቱን ከፈጸሙት ታጣቂዎች ጀርባ ፖለቲካዊ ምክንያት አንደሌለ አስታውቆ ነበር፡፡ እንደዚህ አይነት ተመሳሳይ ድርጊቶቹ ከዚህ ቀደምም እንደሚፈጸሙ የገለጸው መንግስት ምክንያቱ ደግሞ ተራ የከብት ዘረፋ እና የጎሳ ግጭት እንደሆነ ማስረዳቱ አይዘነጋም፡፡ ልዩ አጥኚዋ ለጥቃቱ በመንግስት የተጠቀሱ ምክንያቶችን ይቀበላሉ፡፡

 “እኛ እንደተረዳነው የጎሳዎች ግጭት እንደነበር ነው፡፡ በዚህም ብዙ መንደሮች ተጠቅተዋል፡፡ ይህ ደግሞ በአካባቢው ካለው የከፋ ድህነት ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡ ብዙውን ጊዜ የእንደዚህ አይነት ጥቃቶች የመጀመሪያ አላማ የቀንድ ከብቶችን መዝረፍ ነው፡፡ ነገር ግን አንደዚህ አይነት ግጭቶች ሲባባሱ ግድያን ያስከትላሉ፡፡ የህጻናቱ እገታም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

የሙርሌ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት 662 ህጻናትን ከወላጆቻቸው አንዳቸውን አሊያም ሁለቱንም እንዳጡ የተባበሩት መንግስታት መግለጫ አስታውሷል፡፡ ከእገታ ነጻ ወጥተው ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ 91 ህጻናት መካከል አስራ ሰባቱ ወላጆቻቸውን በዚህ መልክ ማጣታቸውን መግለጫው ይጠቁማል፡፡ ከሚያዚያው እገታ ቀደም ብሎ ከአኙዋ ጎሳ በተመሳሳይ ጥቃት የተወሰዱ 26 ህጻናት እስካሁንም አድራሻቸው አለመታወቁን መግለጫው አትቷል ።

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ