1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዳርፉር፤ የምድር ላይ ሲኦል

ዓርብ፣ መጋቢት 9 1997
https://p.dw.com/p/E0kA

ወደ ቀውሱ አካባቢ ሰላም አስከባሪ ሃይልና ዕርዳታ በመላኩ በኩል ብዙ መወራቱ ባይቀርም ፍርድ ያላየው ርሸና፣ የሴቶች ክብር ደፈራ፣ ማሰቃየት፣ መንደሮችን ማቃጠልና ሲቪሎችን ማፈናቀል በዳርፉር ዕለታዊ ድርጊቶች ሆነው ቀጥለዋል። ይህ የመግለጫው አንድ ይዘት ነው። ሆኖም በጸጥታው ም/ቤት ውስጥ የጥቅም ቅራኔ መከሰቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወደፊት በሱዳን ሊኖረው ስለሚገባው ፖሊሲ ከአንድነት መድረሱን የሚቻል ነገር አላደረገውም። ዲፕሎማቶች እንደሚናገሩት አሜሪካ በሱዳን ላይ እንዲጣል የጠየቀችውን ማዕቀብ ሩሢያ፣ ቻይናና አልጄሪያ እስካሁን አልተቀበሉትም።

የዳርፉር ቀውስ ለይቶለታል፤ የሚያሳዝነው የዓለም ሕብረተሰብ ከተመልካችነት ያለፈ አንዳች የረባ ዕርምጃ አለመውሰዱ ነው። ምክንያቱም በወቅቱ አንድ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ሃይል ወደ ደቡብ ሱዳን በመላኩና በዳርፉር ላይ ግልጽ ውሣኔ በማስተላለፉ ጉዳይ በጸጥታው ም/ቤት ውስጥ ውዥምብር መፈጠሩ እንጂ ሌላ ነገር አይደለም።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዳርፉር አስከፊ ሰብዓዊ ቀውስ ሰፍኖ መቀጠሉን ጠንቅቆ ያውቀዋል። ሆኖም ከሁለት ዓመታት ወዲህ በዳርፉር ምድረ-በዳ ግፍ የሚፈጽመው ጃንጃዊድ የተሰኘ አረብ ሚሊሺያ የሚያካሂደውን ፍጅት ለማቆም አልቻለም። ድርጅቱ ያወጣው የቅርብ መረጃ የሚያመለክተው እንዲያውም ቀውሱ ከተገመተው በላይ የከፋ መሆኑን ነው። በመረጃው መሠረት በጦርነቱ ሳቢያ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 180 ሺህ ገደማ ይጠጋል። በየወሩ አሥር ሺህ ሰዎች ይሞታሉ ማለት ነው። ስድሥት ሚሊዮን ሕዝብ ደግሞ በሽሽት ላይ ነው የሚገኘው።

በወቅቱ በቦታው ሰፍረው የሚገኙት ሁለት ሺህ የአፍሪቃ ሕብረት ወታደሮች ደግሞ የታዛቢነት ሚና ብቻ ስላላቸው በሕዝቡ ላይ የሚደርሰውን ግድያ፣ ዝርፊያና መፈናቀል ሊገቱት የሚችሉ ሆነው አይገኙም። የዓለም ሕብረተሰብ እንግዲህ ሰላማዊ ሕዝብን የመጠበቅ ግዴታውን ሊወጣ አልቻለም። ይህ የእያንዳንዱ መንግሥታት በራስ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ ነጸብራቅ ነው። ቻይናና ሩሢያ በዚህ ጉዳይ የጸጥታው ም/ቤት ግልጽ ውሣኔ እንዳይወስድ አግደው ይዘዋል። ሁለቱ ሃያላን መንግሥታት ይህን የሚያደርጉት በመጀመሪያ ደረጃ በአካባቢው ሰፊ የጦር መሣሪያ ንግድ ስለሚያካሂዱና በሱዳን የነዳጅ ዘይት ጥቅምም ስለሚታያቸው ነው። በራስ ጥቅም ላይ ያመዘነው የአቋም ዝንባሌ እርግጥ በምዕራባውያኑ መንግሥታት አኳያም ጎልቶ የሚንጸባረቅ ጉዳይ ነው። የጦርነቱ ሰለቦች እንደሚሉት የምድር ላይ ሲኦል በሀነችው ዳርፉር ታዲያ ይህ ስብዕና የጎደለው ዝንባሌ ሃቅ መሆኑ እጅግ ያሳፍራል።

የዓለም ሕብረተሰብ በዳርፉር ውዝግብ እንደሚታየው ጠቃሚና ቀደምት የሆኑ ዓለምአቀፍ ሕግጋትን የማስከበርና የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ግዴታውን አልተወጣም። ከሰው ሕይወት ጥበቃ ይልቅ በተለይ በአፍሪቃ የልዕልና ፖለቲካ ሲቀድም ይህ የመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ አይደለም። ከዚህ አንጻር ዓለምአቀፉ ሕብረተሰብ በኮንጎና በሶማሊያ ከተቀጣጠለው ዓመጽ ትምሕርት አለመቅሰሙ በግልጽ የሚታይ ነገር ነው። የዳርፉር ሁኔታ በተባበሩት መንግሥታት ጸጥታ ም/ቤት ላይ አፋጣን አፍሪቃውያን መንግሥታትን ጭምር በቋሚ ዓባልነት እንዲጠቀልል የሚያደርግ የተሃድሶ ለውጥ መካሄዱንም ይበልጥ አጣዳፊ ያደርገዋል።

የዓለም ሕብረተሰብ ለነገሩ በካርቱም መንግሥት ላይ ተጽዕኖ የሚያደርግበት ፍቱን ዘዴ አጥቶ አይደለም። ሃሣቡ ጠረጴዛ ላይ ከቀረበ ውሎ ያደረ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ፤ በመላው የውዝግቡ ታሳታፊዎች ላይ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ መጫን፣ በባለሥልጣናት ላይ የጉዞ እገዳ ማስፈንና በውጭ የሚገኝ የባንክ ሂሣባቸውን መዝጋት፤ እንዲሁም የጦርነቱን አራማጆችን ለፍርድ ማቅረብና የሰላም ጥበቃ ሃይል በተግባር ማሰማራት፤ እነዚህ ሁሉ በያጋጣሚው ተዘርዝረዋል። ግን ገቢር ካልሆኑ በጎ ቃል መደርደሩ ብቻውን ለሰለቦቹ አንዳች ፍሬ አይኖረውም።