1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ዲያስፖራዉ» እና የኢትዮጵያ መንግሥት

እሑድ፣ ነሐሴ 3 2007

ዉጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን አላማዉን ደግፈዉ ወይም ጥቅሙን አይተዉ ወደ ሐገር ቤት የሚጓዙ እንዳሉ ሁሉ ዓላማዉንም ጥቅሙንም የሚቃወሙ፤ ተጓዦችንም የሚተቹ አሉ።የተቃዋሚዎቹ ምክንያት በርግጥ የተለያየ ነዉ።ዲያስፖራዉን ወደ ሐገር ቤት የመጋበዙ ፋይዳ እስከየትነት፤ የተቃዉሞዉ ምክንያት ዋና ዋና መሠረት የዛሬ ዉይይታችን ትኩረት ነዉ።

https://p.dw.com/p/1GBqf
ምስል Solomon Mengist

በስደት፤ በሥራ፤ በትምሕርት፤ በጋብቻና በመሳሰሉ ምክንያቶች ከሐገሩ ዉጪ የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ በያለበት ከተማ፤ ሐገር፤ አልፎ ተርፎም አሐጉር በየአጋጣሚዉ እየተሰባሰበ እርስ በርሱ መተዋወቅ፤ልጅና ዉላጆቹን ማስተዋወቅ፤ የስፖርትና የባሕል ትርዒቶችን መጋራትና ሥለ ሐገሩ መምከር በርግጥ እንግዳ አይደለም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲሕ የኢትዮጵያ የፌደራዊና አካባቢያዊ መንግሥታት፤ ለረጅም ጊዜ ዉጪ የሚታወቀዉን ከማሻሻያ ጋር ሐገር ዉስጥ ማሳናዳት ጀምረዋል።እንደተከታተልነዉ ኢትዮጵያዉያንና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን (ዲስፖራ-በአንድ የዉጪ ቃል) የሚሳተፉበት ዝግጅት ልዩ ቀን ወይም ሳምንት ተቆርጦ፤ ድግስና ገለፃ ታክሎበት ሞቅ ባለ የአቀባበልና የሽኝት ሥርዓት የታጀበ ነዉ።

ባለፈዉ ዓመት የትግራይ መስተዳድር «የትግራይ ዲያስፖራ» ያለዉን ድግስ አዘጋጅቶ የአካባቢዉን ተወላጆች ጋብዞ ነበር።ዘንድሮ ኦሮሚያ ነዉ።የኦሮሞ ዲያስፖራ ፌስቲቫል የተሰኘዉ ዝግጅት ካለፈዉ ሐምሌ 25 ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ዘልቋል።ከመጪዉ ነሐሴ 6 ጀምሮ ደግሞ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ቀንን ለማክበር ታቅዷል።

ዉጪ የሚኖሩ ኢትዮያዉን በየዘር ሐረጋቸዉ፤ በትዉልድ አካባቢያቸዉ ይሆን በመላዉ ኢትዮጵያ በሚከበረዉ በዓል፤ ፌስቲቫል ወይም ድግስ ላይ እንዲገኙ ለማማለል የኢትዮያ አየር መንግድ ከመደበኛዉ የአዉሮፕላን ቲኬት ዋጋ አርባ በመቶ ያክል ቅናሽ ያደርጋል።ከሆቴል ቤት እስከ መገናኛ (ትራንስፖርት) ያሉ የፌደራልና የአካባቢ መንግሥታትት ተቋማትም ለዲያስፖራዉ ተመሳሳይ ቅናሽ ወይም ማበረታቻ ማድረጋቸዉም እየተዘገበ ነዉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከዲፕሎማሲዉ ዘመቻ እስከ አየር መንገድ ትኬት ያሉ ጥቅማ ጥቅሞችን እየሰጠ ዲያስፖራዉን ወደ ሐገር ቤት የሚጋብዘዉ፤ ዲያስፖራዉ ሥለ ኢትዮጵያ ልማትና እድገት እንዲረዳ፤ ለሌሎች እንዲያስረዳ፤ ሐገር በማልማቱ ጥረት እንዲሳተፍና እንዲያሳትፍ ለማድረግ ነዉ-ተብሏል።ዉጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን አላማዉን ደግፈዉ ወይም ጥቅሙን አይተዉ ወደ ሐገር ቤት የሚጓዙ እንዳሉ ሁሉ ዓላማዉንም ጥቅሙንም የሚቃወሙ፤ ተጓዦችንም የሚተቹ አሉ።የተቃዋሚዎቹ ምክንያት በርግጥ የተለያየ ነዉ።ዲያስፖራዉን ወደ ሐገር ቤት የመጋበዙ ፋይዳ እስከየትነት፤ የተቃዉሞዉ ምክንያት ዋና ዋና መሠረት የዛሬ ዉይይታችን ትኩረት ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ልደት አበበ