1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደብዛቸው የጠፋ ሰዎች አፅምና DNA ፣

ረቡዕ፣ ሐምሌ 7 2002

በዓለም ዙሪያ ፤ በተለያዩ ሀገራትም ሆኑ አካባቢዎች፤ በውዝግብ ፣ የእርስ በርስ ጦርነትም ሆነ ጉልበተኞች በደካሞች ላይ በሚወስዱት የግፍ እርምጃ ፣ ሥፍር-ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ስለመገደላቸው፣ ከፊሉም ደብዛቸው እንደጠፋ ስለመቅረቱ፣ በየጊዜው በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ሲገለጥ ይሰማል ።

https://p.dw.com/p/OJGo
ምስል Qiagen 2010

ይህ በሰው ልጆች ታሪክ በተደጋጋሚ የታየና፣ እስከዛሬ ድረስ ሊገታ ያልቻለ ሁኔታ መሆኑም የታወቀ ነው። ደብዛቸው የጠፋ ሰዎችንም ሆነ የተገደሉ ሰዎችን ፤ ጊዜው እየረዘመ ሲሄድ ፤ እንዲሁ በአጽማቸውን ማንነታቸውን ለመለየት ፤ በጊዜ ሂደት አስቸጋሪ እንደነበረ ቢታወቅም፣ በአዲስ ሥነ ቴክኒክ ለችግሩ መፍትኄ ማስገኘት አዳጋች አልሆነም። በሩዋንዳ፤ በሱዳን በኮንጎ፤ በሲሪላንካ፣ በቦስኒያና በተለያዩ አገሮች፣ የተጠቀሰው ችግር መከሠቱ እሙን ነው። አዲሱ ሥነ ቴክኒክ ፤ የሺ ዓመታት ዘመን ያስቆጠሩ አጽሞችንም በመመርመር የግለሰቦችን ማንነት ለመለየት ያስችላል። -----

በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን፤ ከ 15 ዓመታ በፊት በደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ፣ በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ፣ በቦስኒያ ግዛት በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ተጨፍጭፈው በተለያዩ ቦታዎች በጅምላ የተቀበሩ ሰዎችን ማንነት ለይቶ ለማወቅ ሥነ-ቴክኒክ ያበረከተውን ድርሻ እንዳስሳለን።

እ ጎ አ ሐምሌ 11 ቀን 1995 ዓ ም፤ ቦስኒያ ውስጥ ስረብረ ኒትሣ በተሰኘችው ከተማ አቅራቢያ በጥቂት ቀናት ውስጥ 8,500 ያህል ቦስኒያውያን ተገድለው በየቦታው በጅምላ መቀበራቸው ይታወቃል። የብዙዎቹን ሰለባዎች ማንነት ለመለየት አዳጋች ሆኖ መቆየቱ ቢታወቅም፤ ደብዛቸው የጠፋ ሰዎች አፈላላጊው ዓለም አቀፍ ኮሚቴ፤ አዲሱን ሥነ ቴክኒክ በመጠቀም አብነቱን ማግኘች ችሏል። መሣሪያው፤ ከዘር የሚወረሱ ፈሳሽ ኅዋሳትን አጽድቶና መርምሮ ውጤት የሚያሳውቅ ሲሆን፤ ለቦስኒያ በእርዳታ መልክ የቀረበው፤ ጀርመን ውስጥ ዱዑሰልዶርፍ እተሰኘችው ከተማ አቅራቢያ ከሚገኝ አንድ ሥነ ህይወታዊ የሥነ-ቴክኒክ ተቋም ነው። ስለመሣሪያው በትክክል ምንነትና አጠቃቀም Michael Lange የተባሉት የተቋሙ ባልረባ፣ እንዲሁም፤ የሳይንስ ምሁር ማሪዮ ሸረር አስረድተዋል። በቤተ-ሙከራ፣ የሚቀመጥ አንድ 60 ሴንቲሜትር ያህል ርዝመት ያለው ሰማያዊ ንዑስ ሣጥን- መሰል «ኩብ» አለ። ሣጥኑ ከመደበኛ የምግብ ማሞቂያ መሣሪያ ትንሽ ከፍ የሚል ነው። Qiagen የተሰኘው ተቋም ባልደረባ ፣ ሸረር፣ሰማያዊውን ኩብ ሣጥን በመክፈት በፕላስቲክ ሣጥን ያሽጉና በልዩ አቀማመጥ ከሚሠራበት ቋሚ መሣሪያ ይሠኩታል። ሸረር በይበልጥ ሲያብራሩ---

«አሁን እዚህ ውስጥ መልስ የሚገኝበትን የአካል ቁስ አስቀምጫለሁ። መሣሪያው ውስጥ ዝግጁ ይሆን ዘንድ አስገባዋለሁ። ይህም ማለት፤ በውስጡ ከተቀመጠው የኅዋሳት ፈሳሽ ከፊል፤ የዘር ውርሱ ተለይቶ ይቀርባል። »

በሰመማያዊው ኩብ ውስጥ አንድ ንዑስ የሚሠብቅ ተሽከርካሪ መሣሪያ ይገኛል። ሥነ-ህይወታዊው ኢምንት ቁስ አካል፤ መሣሪያው ውስጥ በፍጥነት እንዲሽከረከር ከተደረገ በኋላ፤ የዘር ውርሱ ይለያል። ማሪዮ ሸረር፤ ኩቡን ይዘጉና አንዳንድ አውቶማቲክ ጉጦችን በመነካካት መሣሪያው በቀጥታ በመሽከርከር የማጣራቱን ተግባር፤ ደረጃ በደረጃ እንዲያካሂድ ያደርጋሉ።

የዘር ውርስ የሆነውን የኅዋሳት ርጥበት ለማጣራት፣ ሰማያዊው ኩብ አዕማዳት አሉት እነርሱም የፕላስቲክ ዘንጎች ሲሆኑ ፣ እነርሱም፣ የዘር ውርስ ፈሳሽ ኅዋሳትን አጣብቆ በሚይዝና ከሚበታትን ቅመም በሚለይ ንጥረ ነገር የተሞሉ ናቸው። አሁንም ማሪዮ ሸረር----

«በፓላስቲክ ዘንጎቹ፤ ማጣሪያ የመሰለ መሣሪያ አለ። የዘር ውርስ የሆነው የኅዋሳት ፈሳሽ ነገር፣ በአንድ አካባቢ ተጣብቆ ይገኛል። ሌሎች ምርምር የሚካሄድባቸው በቀጥታ ይፈሳሉ ወይም በመጨረሻ ደረጃ በደረጃ እየታጠቡ እንዲወገዱ ይደረጋል። ስለዚህም በመጨረሻ፤ ሙከራ የሚደረግበትን መያዣ አነሣና የራሴን የተጣራ የዘር ውርስ መለያ ምልክቴን DNA አገኛለሁ ማለት ነው።»

ሰማያዊው ኩብ መሳሪያ በምርምር ጣቢያዎች የሚቀመጥ ሲሆን፣ በፍርድ ቤቶችም ከባድ የሆነ ማመሣከሪያም ሆነ መረጃ በሚያስፈልግበት ጊዜ ይቀርባል። እንደ ምሥጢር መፍቻ የደም ዓይነት መለያ ማለት ነው። የዘር ውርስ ፈሳሽ ኅዋሳትን ፣ እስከዚህም እምብዛም ያልቆሸሸ Deoxyribonucleic Acid (DNA )ካለው አጥንትም ማግኘት ይሻላል።

በዘመናዊው ሥነ ቴክኒክ በመታገዝ፤ እ ጎ አ በ 1922 ዓ ም፤ የመቃብሩ ቦታ እንደተጠበቀ አጽሙ ታሽጎ የተገኘው፣ ከ 3,300 ዓመት በፊት በ 19 ዓመቱ መሞቱ የሚነገርለት ወጣቱ ፈርዖን ቱትአንካሙን፤ ከባድ የአጥንት ህመምና ወባ እንደነበረበት ለማረጋገጥ መቻሉ የሚታወስ ነው። ወላጆቹ፣ እህትና ወንድም እንደነበሩ ነው የሚገመተው።

አሁንም ማሪዮ ሸረር----

«እጅግ ብዙ ዘመን ካሳለፉ አጽሞች፤ በተለይ አፈር ውስጥ በጊዜ ብዛት ሳቢያ ከደቀቁትም ሆነ ከበሰበሱት የሚፈለገውን የዘር ውርስ ኅዋስ ለማግኘት በተደጋጋሚ ችግሮች አጋጥመዋል። ችግሩ የሚያጋጥመውም በተፈጥሮም ሆነ በንጥረ ነገሮች ተጽእኖ በባክቴሪያም ጥቃት አጽሙ ክፉኛ ሲጎዳ ነው። ከአጽም፤ ያንድን ሰውም ሆነ እንስሳ የዘር ውርስ ለይቶ ለማወቅ፤ በተቻለ መጠን ፣ በተጣራ ሁኔታ በጥንቃቄ የሚፈለገውን በመቅረፍ ማግኘት የግድ ይላል። »

ደብዛቸው የጠፋ ሰዎች አፈላላጊው ዓለም አቀፍ ኮሚቴ ያሠማራቸው ሳይንቲስቶች ቀደም ሲል በተገለጠው የ Qiagen ተቋም አዲስ ሥነ ቴክኒክ ይገለገላሉ። ደብዛቸው የጠፋ ሰዎች አፈላላጊው ዓለም አቀፍ ኮሚቴ በሳራየቮ ባቋቋመው የ DNA ቤተ-ሙከራ የሚሠሩት ተመራማሪ Rene Huel እንዲህ ይላሉ----

«DNA በእርግጥ በዘር ተወራራሽነት ረገድ ብቸኛው የማንነት መለያ ዘዴ ነው። ይህ ለብዙኀኑ የሚሠራ ነው። ዲ ኤን ኤ፤ ደብዛቸው የጠፋውን ሰዎች ማንነት በመለየት እንደገና ስማቸው እንዲጠራ የሚያበቃ ነው። በሌሎች ዘዴዎች ባህላዊው ማንነትን ማወቂያው ብልሃትም ቢሆን በዚህ አካባቢ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል አይደለም። »

ለምሳሌ ያህል፤ ከቦስኒያው ጦርነት በኋላ፤ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ደብዛቸው እንደጠፋ መቅረቱ የሚዘነጋ አይደለም። ሰዎች በጅምላ ከተቀበሩባቸው ጉድጓዶች የተገኘው የአጽም ክምችት በመጀመሪያ የትኛው የየትኛው ነው በትክክል ለማወቅ አስቸጋሪ ነበረ። ከ 15 ዓመታት ወዲህ ም ቢሆን ፣ በመቶ የሚቆጠሩ ፤አጽም የታጨቀባቸው ኬሻዎች በቀዝቃዛ ቦታዎች እንደተቀመጡ የሚገኙ ሲሆን፣ የሟቾቹን ማንነት የመለየቱ ተግባር ገና ይካሄዳል። ግን ቀላል ተግባር አይደለም። ነፍሰ-ገዳዮቹ፤ የጦር ወንጅል መፈጸማቸውን ለማድበስበስ ያላደረጉት የለም።»

7,«አንድ ግለሰብ በአንድ የመቃብር ቦታ ብቻ አይደለም የተቀበረው።ግለሰቦች፤ በ 4 ወይም 5 ቦታ አካላቸው ተከፋፍሎ ሳይቀበሩ አልቀሩም። በተቻለ መጠን የግለሰብን የአካላት ክፍሎች አንድ ላይ ለመሰብሰብ ነው ጥረት የምናደርገው። ደብዛው የጠፋውን ሰው አስከሬን መልሶ ለቤተ-ዘመድ የማስረከቡ ተግባር ከገጠሙን ዐበይት ችግሮች አንዱ ነው።»

ደብዛቸው የጠፋ ሰዎችን አፈላላጊው ዓለም አቀፍ ኮሚቴ፤ ከ 15,000 በላይ የሚሆኑ የጠፉ ሰዎችን የደረሰባቸውን ዕጣ-ፈንታ ለይቶ ለማሳወቅ በቅቷል። ካለፈው ዓመት ሐምሌ እስከሁን በአንድ ዓመት ብቻ የ 775 ሰዎችን አጽም ለይቶ አሳውቆአል። የእነዚህም ሰዎች አጽም ተለቅሞ ባለፈው እሁድ ለቤተሰብና ቤተዘመድ ተሰጥቶአል።

«ተስፋ አለኝ በሰፊው በዓለም ዙሪያ ትምህርት እንደሚሰጥ። ሰዎች የሚፈጽሙት ወንጀል ምንጊዜም ሊደበቅ እንደማይችልመገንዘባቸው አይቀርም። ተሸፋፍኖ አይቀርም። ይህ ዓይነቱ የ DNA ሥነ ቴክኒክ ምን እንደተፈጸመ እውነቱን አፍረጥርጦ የሚያወጣ ነው»።

ICMP ወደፊት በሌሎች የዓለም ክፍሎች የጦርነታ ቀጣናዎች ደብዛቸው የጠፋ ሰዎችን አጽም እየመረመረ እውነት እንዳይደበቅ የሚጥር መሆኑን አስታውቆአል። ሚኻኢል ላንገ

ተክሌ የኋላ