1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ አፍሪቃና የመሬት ይዞታ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 11 1998

ለታዳጊ አገሮች ልማት መሰናክል ሆነው ከሚገኙት ችግሮች አንዱ የመሬት ስሪት በሚገባ አለመካሄድ ነው። በአብዛኞቹ አገሮች የሰፊው ሕዝብ መሠረታዊ ሕልውናና የዕድገት ዕጣ ከዚሁ ከመሬት ይዞታ ጋር ሲበዛ የተሳሰረ ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። ስለዚህም ለውጡ ወሣኝነት ይኖረዋል። ብዙሃኑ ዜጋ የመሬቱ ባለቤት ሊሆን ካልበቃባቸው ታዳጊ አገሮች አንዷ ደቡብ አፍሪቃ ናት።

https://p.dw.com/p/E0db
የደቡብ አፍሪቃ የድህነት ገጽታ
የደቡብ አፍሪቃ የድህነት ገጽታምስል AP

የደቡብ አፍሪቃ ጥቁሮች ዛሬ ዘረኛው የአፓርታይድ አገዛዝ ከተወገደ ከ 12 ዓመታት ወዲህም መሬታቸው ከነጮች ተመልሶ እንደሚሰጣቸው የተገባላቸው ቃል ዕውን አልሆነም። በአፓርታይዱ አገዛዝ ዘመን ጥቁሮች መሬታቸውን በግድ መልቀቅ ነበረባቸው። ታዲያ መንግሥት ካሣ በመክፈል መሬታቸውን ሊያስመልስላቸው ቢያቅድም ውጥኑ በተለያዩ ምክንያቶች ገቢር የሆነው እጅግ በጥቂቱ ነው። አሁን በቅርቡ ግን መንግሥት ቁርጠኛ ሆኖ መነሣቱን ጉዳዩ የሚመለከታቸው ከፍተኛ ባለሥልጣን ሉሉ ሢንግዋና አስገንዝበዋል።
ሢንጉዋና ሰሞኑን የደቡብ አፍሪቃ የመሬት ጥያቄ ኮሚሢዮን ዓመታዊ ዘገባውን ካወጣ በኋላ ለጋዜጠኞች እንዳስረዱ ከሆነ የመሬት ሽግግሩን ዕቅድ በ 2008 እንዲያጠናቅቁ ፕሬዚደንት ታቦ እምቤኪ ሥልጣን ሰጥተዋቸዋል። የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት ቀደም ሲል ቃል የገባው 30 በመቶ የሚሆነውን የንግድ እርሻ መሬት እስከ 2014 ዓ.ም. ድረስ ወደ ጥቁሮች ዕጅ ለማሸጋገር ነበር። ይሁንና ባለፈው ዓመት ጆሃንስበርግ ላይ ተቀማጭ በሆነ በአገሪቱ የልማትና የንግድ ማዕከል ቀርቦ የነበረ የጥናት ውጤት እንዳመለከተው ከነጻነት ማግሥት ከ 1994 ጀምሮ እስከ 2004 በአሥር ዓመታት ውስጥ የተሸጋገረው መሬት ከ 4.3 በመቶ አይበልጥም።

የፕሬቶሪያ መንግሥት እስካሁን ዘረኛው አገዛዝ ያዛባውን የመሬት ባለቤትነትን ሚዛን ለማስተካከል “ፈቃደኛ ሻጭ፤ ፈቃደኛ ገዢ” የሚል በውዴታ የሚደረግ ሽግግር ፖሊሲን መርጦ ነው የቆየው። በሌላ በኩል ለሽግግሩ መዘግየት የተለያዩ ምክንያቶችም ይጠቀሳሉ። ከነዚህም አንዱ ጉዳዩን እንዲያከናውኑ ሃላፊነት በተሰጣቸው ተቋማት ውስጥ ያለው የሥራ ድክመት ነው። ተቀጣሪዎቹ በሥራቸው ላይ ይተኛሉ፤ ወይም በሕመም አስባብ ፈቃድ እየወሰዱ ይቦዝናሉ። ሥራቸውን በሚገባ አያከናውኑም ማለት ነው። ሁኔታው የብዙዎቹን የአፍሪቃ አገሮች ሃቅ የሚያንጸባርቅ ነው።

በአፓርታይዱ ዘመን መሬታቸውን የተነጠቁ ዜጎች ዘረኛው አገዛዝ ከወደቀ ከአንድ ዓመት በኋላ ከ 1995 አንስቶ እስከ 1998 ርስታችው ይመለስላቸው ዘንድ ማመልከቻ ማቅረብ ተፈቅዶላቸው ነበር። በሰሜናዊቱ ክፍለ-ሐገር በሊምፖፖ ለምሳሌ በዚሁ ጊዜ ለሚመለከተው ባለሥልጣን ከቀረቡት ጥያቄዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት መፍትሄ ሊያገኙ በቅተዋል። እርግጥ ሽግግሩ በጅምሩ ያስከተለው ችግር ቀላል አልነበረም። ሆኖም የደቡብ አፍሪቃ የእርሻ አስተዳደር ተቋም ለጥቁር ገበሬዎች የሥልጠና ትምሕርት በመስጠትና ዕርዳታ በማቅረብ እክሉን ሊቋቋመው በቅቷል።
ሰፊ የእርሻ መሬቶችን በማስተሳሰር የማሕበር ንብረት አድርጎ የማስተዳደሩ በ 2001 የጠተናቀቀ ዕርምጃ እጅግ ገንቢ ሆኖ ነው የተገኘው።

በአጠቃላይ ግን በጎረቤቲቱ ዚምባብዌ በነጮች መሬት መነጠቅ የተከሰተው የፖለቲካና የኤኮኖሚ ቀውስ ያስከተለው ፍርሃቻ ለውጡ ለመጓተቱ ዓቢይ ምክንያት መሆኑ አልቀረም። ቢሆንም ደቡብ አፍሪቃ ነጭ ገበሬዎችን የለውጡ አበር ለማድረግ እንጂ ለማባረር እንደማትፈልግ ነው ባለሥልጣኑ የሚያረጋግጡት።