1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ ሱዳን ፦ጦርነት፤ስደትና ነጻነት

ዓርብ፣ ሐምሌ 3 2007

የደቡብ ሱዳን የ19ወራት ጦርነት ከገደለ፤ ካሰደደና ካስራበዉ ሕዝብ በተጨማሪ ከ4 መቶ ሺ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ አስገድዷል። ተማሪዎችና መምህራን እርሳስና ጠመኔያቸውን ጥለው የጦር መሳሪያ ጨብጠዋል። የርስ በርስ ጦርነቱ ሳይቆም የዜጎች ስደት ጋብ ሳይል ትናንት ደቡብ ሱዳን አራተኛ አመት የነጻነት በዓሏን አክብራለች።

https://p.dw.com/p/1Fwh9
Symbolbild Frauen Opfer Konflikt Südsudan
ምስል GetttyImages/AFP/C. Lomodon

[No title]

ደቡብ ሱዳን አራተኛ አመት የነጻነት በዓሏን ስታከብር የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ምስል ያረፉባቸው የመገበያያ ሳንቲሞችን ይፋ አድርጋለች። የአምስት፤ሃያ እና ሐምሳ ሳንቲሞችን ላይ ያረፈው የፕሬዝዳንቱ ምስል ግን በአገሪቱ ዜጎች ዘንድ የተደበላለቀ ስሜት ፈጥሯል። በመላ አገሪቱ ለግብይት የተዘጋጁት ሳንቲሞች የዲንካ ነገድ አባል የሆኑትን ፕሬዝዳንት ምስል ይዘው በተቀናቃኛቸው የሪየክ ማቻር ኑዌሮች ዘንድ ያለው ተቀባይነት ጥያቄ ውስጥ ወድቋል። ከሳልቫ ኪር ይልቅ የየደቡብ ሱዳን የነጻነት ትግል መሪ የነበሩት የጆን ጋራንግ ምስል በሳንቲሞቹ ላይ ቢቀረጽ ይሻል ነበር ያሉ ዜጎችም አሉ።የደቡብ ሱዳን ፓውንድ የምንዛሪና የመግዛት አቅም ማሽቆልቆል ያሳሰባቸው የኢኮኖሚ ፋይናንስና ልማት ኮሜቴ ሰብሳቢ ጋክ ማኩአች አንድ ቀን የዋጋ ግሽበቱ መቀነሱ አይቀርም ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል። የአገሪቱ ብሄራዊ ባንክ ገዢ ኮርኔሊዮ ኮርዮም አሁን ወደ ገበያ የገቡት ሳንቲሞች መርፌ፤የልብስ ቁልፍ እና ትምባሆ ይገዛሉ ሲሉ አዲሶቹ ሳንቲሞች ያላቸውን አነስተኛ ግልጋሎት ተናግረዋል።

ደቡብ ሱዳን አራተኛ አመት የነጻነት በዓሏን ትናንት ስታከብር « ቀኑ ኢ-ፍትሃዊነትንና ኢ-እኩልነትን የቀለበስንበት ነው።» ያሉት ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ከተቀናቃኞቻቸው ጋር የገቡበትን ጦርነት «ትርጉም አልባ» ብለው የአገራቸው ዜጎች ከሱዳን ነጻ የወጡበትን ቀን መለስ ብለው እንዲያስቡ ጠይቀዋል። ሲቲዝን የተባለዉ ጋዜጣ አዘጋጅ ቪክቶር ኬኒዋኒ ለአስራ ዘጠኝ ወራት በዘለቀው የርስ በርስ ግጭት ምክንያት አራተኛው የነጻነት በዓል ትርጉም ማጣቱን ይናገራል።

Afrika Bildergalerie Kindersoldaten im Süd-Sudan
ምስል DW/A. Stahl

«ብዙ ሰዎች አሁን በጦርነቱ ውስጥ ያሉትን ጨምሮ ወደ ሱዳን ተመልሰው መሄድ አይፈልጉም። ደቡብ ሱዳን ከካርቱም በመገንጠሏ የሚጸጸት የለም። ይሁንና ደቡብ ሱዳን በጥሩ ሁኔታ ላይ ብትገኝ ኖሮ ከፍተኛ ፈንጠዝያ በኖረ ነበር። ብዙ ሰዎች የሰላም ስምምነት ቢፈረም ኖሮ ደስታቸው ከፍተኛ ይሆን ነበር ብለው ያምናሉ።»

በዋና ከተማዋ ጁባ የጆን ጋራንግ አደባባይ የተከበረው በዓል የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒና በሺዎች ከሚቆጠሩ የደቡብ ሱዳን ዜጎች ታድመውበታል። በዓሉ እንደ ኢድሙን ያካኒ ባሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ግን ተቀባይ ነት አላገኘም።«አሁን የምንደሰትበት አንዳችም ነገር የለም ያሉት» ኢድሙንድ «ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ የበርካታ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል፤ንብረት ወድሟል። ሰብዓዊ ቀውሱም መፍትሄ አላገኘም።» ሲሉ ይናገራሉ። ቪክቶር ኬኒዋኒ ደቡብ ሱዳናውያን በተቀናቃኞቹ አሸማጋዮች ገለልተኝነት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ይናገራል።

«ሰዎች ሲጋጩ ወገንተኝነት የሌላቸው እንደ የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግስታት-ኢጋድ አይነት አሸማጋዮች ያስፈልጋሉ። አንዳንድ ሰዎች ግን የምስምራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግስታት-ኢጋድ ሸማጋዮች ለአንደኛው ወገንተኛ ናቸው የሚል ቅሬታ አላቸው። ጦርነቱ ሲካሄድ አስራ ዘጠኝ ወራት አስቆጠረ። ይህ ጊዜ የሰላም ቢሆን ኖሮ በርካታ ስራዎች በተሰሩ ነበር። አሁን መንገዶች የሉንም። ነጻነት ቢኖረንም ግዛቶቹን የሚያገናኙ መንገዶች ሊኖሩን ይገባል።»

Afrika Bildergalerie Kindersoldaten im Süd-Sudan
ምስል DW/A. Stahl

ከደቡብ ሱዳን ዜጎች ግማሽ ያህሉ የረሃብ አደጋ ተጋርጦበታል።የመንግስትና የአማጺው ቡድን ታጣቂዎች በዜጋቸዉ ላይ በየቀኑ አሰቃቂ ድርጊት ይፈፅማሉ። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ስደተኞች ጦርነቱ እንዴት እንደሚቆም ግራ እንደገባቸው ናቸው። የአገራቸው ህልውናም አደጋ ውስጥ እንደገባ የሚናገሩም አልጠፉም።

በተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ሃላፊ አንቶኔ ሌክ «በደቡብ ሱዳን ህጻናት ላይ የሚፈጸመው ግፍ ለመናገር የሚከብድ ነው። ነገር ግን እንናገረዋለን» ሲሉ በድርጅቱ ድረ-ገጽ አስፍረዋል። «በግንቦት ወር ሶስት ሳምንታት ብቻ በዩኒቲ ግዛት 129 ልጆች ተገድለዋል። ወንዶች ልጆች የዘር ፍሬያቸው ተቆርጦ ደማቸው በመፍሰሱ ህይወታቸውን አጥተዋል። የስምንት ህጻንን ጨምሮ ሴቶች ልጆችን በቡድን ከተደፈሩ በኋላ ተገድለዋል። ህጻናት በቡድን በገመድ እጃቸው ተጠፍሮ አንገታቸው በስለት ተቀልቷል።» ያሉት አንቶኔ ሌክ «ይህ ድርጊት ሊቆም ይገባል።» ሲሉ ተማጽነዋል። የአንቶኔ ሌክ ተማጽኖም ይሁን የደቡብ ሱዳናውያን መከራ ለሳልቫ ኪርና ሪየክ ማቻር ሰላም የሚያወርዱበት ልቦና አልሰጣቸውም። ይባስ ብሎ አንዳቸው ሌላውን ይወነጅላሉ። ከምስራቁም ይሁን ከምዕራቡ ጎራም ወዳጅ አላጡም።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ