1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ ሱዳንና ሰላም ማውረድ ያልቻሉት መሪዎችዋ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 12 2007

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር 20 ወር የሆነውን የሃገራቸውን የርስበርስ ጦርነት ያበቃል የተባለውን የሰላም ውል ሳይፈርሙ ወደ ሃገራቸው መመለሳቸውን የዩኤስ አሜሪካ መንግሥት በጥብቅ ነቅፋ፣ ፕሬዚደንቱ በሚቀጥሉት 15 ቀናት ውሉን እንዲፈርሙ አሳሰበች።

https://p.dw.com/p/1GHLg
Bildkombo Südsudan Riek Machar und Salva Kiir
የደቡብ ሱዳን አማፅያን መሪ ሪየክ ማቸርና፤ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርምስል Getty Images/Zacharias Abubeker/Ashraf Shazly/Montage

[No title]

የዩኤስ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ጆን ከርቢ ትናንት በዋሽንግተን እንዳስታወቁት፣ ሳልቫ ኪር ከምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት፣ ኢጋድ እና ዩኤስ አሜሪካ ጎን ብሪታንያ፣ ኖርዌይ፣ ቻይና፣ የአፍሪቃ ህብረት እና የተመድ፣ በሌላ አጠራራቸው «ኢጋድ ፕላስ» የደገፉትን የሰላም ስምምነት ለመፈረማቸው በጣም አሳዝኗታል። ተቀናቃኛቸው ያማፅያኑ መሪ ሪየክ ማቸር ግን ውሉን የፈረሙበትን ድርጊት ከርቢ ሳያሞግሱ አላለፉም። 15 ቀናት እንዲሰጣቸው የጠየቁት ሳልቫ ኪር ከዚሁ ጊዜ በኋላ ስምምነቱን ካልፈረሙ ዓለም አቀፍ ማዕቀብ ሊጣልባቸው ይችላል። ሳልቫ ኪር ውሉን እንደሚፈርሙ ተስፋቸውን የገለጹት ሪየክ ማቸር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ውሉን ተግባራዊ የማስደረግ ኃላፊነት እንዳለበት አስታውቀዋል።

Fahnen der IGAD-Mitgliedsländer
ምስል Yohannes G/Eziabhare

« ስምምነቱን ተግባራዊ ማድረግ እንችል ዘንድ ፕሬዚደንት ኪርን እና መንግሥታቸውን ተከታትለው ስምምነቱን እንዲፈርሙ የማድረጉ ኃላፊነት የኢጋድ ፕላስ እና ከደቡብ ሱዳን ጋር ጥሩ ግንኙነት ያላቸው ወገኖች ነው። ያን ጊዜ እየጠበቅን ነው። ግፊት አድርገው ውሉን ማስፈረሙ እንደሚሳካላቸው ተስፋ አድርገናል። »

ሪየክ ማቸር እንዳስረዱት፣ ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ የሶስት ወር የመጠበቂያ ጊዜ በተሰጠው ውል መሠረት፣ የሥልጣን ክፍፍልን በተመለከተ ስምምነቱ አብዛኛውን ሥልጣን ለፕሬዚደንት ኪር ይሰጣል። ይሁን እንጂ፣ የደቡብ ሱዳን ማስታወቂያ ሚንስትር ማይክል ማክዌይ ትናንት በአዲስ አበባ የቀረበው እና እርሳቸው የማይረባ ያሉት ገላጋይ ሰነድ የደቡብ ሱዳንን ሕዝብ የማይጠቅም በመሆኑ እንደማይቀበሉት እና መንግሥታቸም ስለውሉ ይዘት በሚቀጥሉት 15 ቀናት ውስጥ ከሕዝቡ ጋር እንደሚወያይበት አስታውቀዋል። ይህ በዚህ እንዳለ፣ የደቡብ ሱዳን መንግሥት በወቅቱ በኢማቶንግ ተራራማ አካባቢ የሚገኙትን ሠፈሮቻቸውን ደብድቧል ሲሉ ዓማፅያኑ ወቀሳ ሰንዝረዋል።

የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ጌታቸዉ ተድላ ኃይለጊዮርጊስ ሪየክ ማቸርን አነጋግሮ ዘገባ ልኮልናል።

አርያም ተክሌ

ጌታቸዉ ተድላ ኃይለጊዮርጊስ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ