1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ ምሥራቅ እስያና በዓለም ውስጥ እጅግ የደኸዩ አገሮች፧

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 29 1997

ታኅሳስ ፲፯ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓ ም፧ ከኢንዶኔሺያ ደሴት፧ ከሱማትራ በስተምዕራብ በህንድ የውቅያኖስ ወለል፧ የደረሰ ብርቱ የምድር ነውጥ ባስከተለው ጠረፎችን ባጥለቀለቀው ማዕበል ሳቢያ ብዙ ህዝብ ካለቀ ወዲህ፧ ዓለም አቀፍ ድንጋጤና ኀዘን ብቻ ሳይሆን፧ ለእርዳታም፧ በገንዘብ መዋጮ ረገድ ርብርቦሽ ታይቷል። በየፊናው የሚፍጨረጨረው የዓለም ፮ ቢልዮን ህዝብ፧ በተናጠል ሳይሆን በኅብረት ሰብአዊነትን ማሳየቱ፧ የሚደነቅ ሠናይ ክስተት ነው። ይሁንና፧ የእርዳታው

https://p.dw.com/p/E0ka

መንፈስም ሆነ መነሳሳቱ፧ በቅጽበታዊ ስሜታዊነት ላይ ብቻ የተመረኮዘ ሆኖ እንዳይቀር ሥጋት መኖሩን፧ የደቡብ ጀርመን ጋዜጣ፧ Südedeutsche Zeitung «ተደራራቢው ድቀት« በሚል ርእስ፧ ባቀረበው ሐተታ ላይ ገልጿል።

አሁን በዓለም ዙሪያ፧ ለደቡብ ምሥራቅ እስያ ህዝብ የታየው አጽናኝ፧ የእርዳታ መዋጮ፧ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፧ ሊከስም እንደሚችል፧ ጥርጣሬውን ያንጸባረቀውSüddeutsche Zeitung በአዳጊ አገሮች፧ ድህነትን ከሥር-ከመሠረቱ፧ ለመታገል የሚደረገውን ጥረት እንዳያሰናክልም ያሠጋል ይላል።
ታህሳስ ፲፯ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓ ም፧ በደቡብ እስያ የደረሰው የተፈጥሮ መቅሠፍት ያካባቢውን ድሆች ተወላጆችና ለመዝናናት ከበለጸገው የዓለም ክፍል ተጉዘው በዚያ ይገኙ የነበሩትን ሰዎች መፍጀቱ ነው። በሞቃት የዓለም ክፍሎች የሚቀሰቀስ የውቅያኖስ ማዕበልና የጎርፍ ማጥለቅለቅ በየጊዜው ነውሰው የሚፈጀው። ለዚህ ዋንኛ ምሳሌ፧ ባንግላዴሽ ነው። ከሞላ ጎደል በያመቱ በማዕበል የምትመታው ባንግላዴሽ፧ ብዙ ዜጎቿን በአሰቃቂ አደጋ ታጣለች። ይሁንና በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን አደጋውን፧ ጥፋቱን አግዝፎ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ሥዕል ያን ያህል ስለማይቀርብ ፧ እንዲሁ እርዳታ እንደሚደረግ ብቻ ነው በመግለጫ መልክ ሲቀርብ የሚሰማው። ያሁኑ ልዩ ነው። ብዙ አገር ጎብኝዎች ጭምር አልቀዋልና! ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን፧ በከፍተኛ ደረጃ፧ በመረባረብ፧ ማዕበሉ ስላደረሰው ጥፋት፧ በዝርዝር ያቀረቡት በተእቀሳቃሽ ሥዕል የተደገፈ ዘገባ፧ ለመዋጮ ያነሳሳው ህዝቡን ብቻ ሳይሆን መንግሥትም ጠቀም ያለ የእርዳታ ገንዘብ እንዲመድቡ ግፊት ሳያስከትል አልቀረም። መራኄ መንግሥት ጌርሃር ሽሮዖደር፧ ድሆች አገሮችን በሰፊው መርዳት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ኣቃል የተገባው፧ በተግባር ይፈጸም ይሆን? የጋዜጣው ጥያቄ ነው። የበለጸጉ መንግሥታት፧ ካልተጣራ ብሔራዊ ገቢያቸው 0.7 ከመቶውን ለልማት እርዳታ እንዲያውሉ ይጠበቅባቸዋል። ይህን፧ ጀርመን ገና አላሟላችም። የደቡብ ምሥራቅ እስያውን የተፈጥሮ መቅሠፍት የመሰለ አደጋ በዓለም ዙሪያ፧ እጅግ የደኸዩ አገሮችን፧ ለምሳሌ ያህል ከሰሐራ ምድረ-በዳ በስተደቡብ የሚገኙ የተጎሳቆሉ አገሮችን ለመርዳት የሚደረገውን ጥረት ሊገታ ይችላል። ኡን፧ በቢልዮን የሚቆጠር ዶላር/ዩውሮ፧ ለደቡብ ምሥራቅ እስያ ተመድቦ ሌላው የዓለም ክፍል እንዳይረሣ ማሳሰብ ተፈላጊ ይሆናል። የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፧ አፍጋኒስታንን ለማቋቋም ብዙ ገንዘብ ሲያፈስ፧ በምዕራብ አፍሪቃ፧ የጦርነት ሰለባዎችን፧ ከስደትየተመለሱ ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችል በቂ ገንዘብ አልተገኘም። ላይቤሪያና ሴራሊዮን፧ ከዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ሰላም የሚያሠፍንና የሚያረጋጋ፧ እርዳታ ካልቀረበላቸው፧ እንደገና ውዝግብ አዘቅት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ሱዳን በምዕራባዊው ክፍለ-ሀገር፧ ዳርፉር፧ ኮንጎ ዴሞክ’ራቲክ ሪፓብሊክ፧ በምሥራቃዊው
ክፍለ ሀገር አሳሳቢ ችግር የተደቀነባቸው አገሮች መሆናቸው ሊዘነጋ አይገባም። በያመቱ በወባ ብቻ፧ ከ ፩ ሚልዮን በላይ ህዝብ፧ በ «ኤይድስ« ፫ ሚልዮን፧ በምግብ እጦትና፧ ተመጣጣኝ ምግብ ባለማግኘት ደግሞ ፲ ሚልዮን ያህል ህዝብ ይሞታል። የሱናሚው ምዕበል የህንድንና የኢንዶኔሺያን የተሻለ የእድገት ደረጃ አይገታም። በመሆኑም በተንቀሳቃሽ ፊልም ረዳትነት፧ ያን ያህል ችግራቸው ለዓለም ኅብረተሰብ የማይቀርበው፧ ከሰሃራ ምድረ-በዳ በስተደቡብ ያሉ አገሮች እጅግ ሰፋ ያለ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል በማለት፧ ጋዜጣው ሐተታውን ደምድሟል።