1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዩጋንዳና የቀጣዩ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ዕጩ ጉዳይ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 6 2007

የዩጋንዳ «ናሽናል ሬዚዝተንስ ሙቭመንት» ፓርቲ ፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒን እአአ ለ2016 ዓም ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በዕጩነት ለማቅረብ የያዘው ዕቅድ ብርቱ ክርክር አስነስቷል።

https://p.dw.com/p/1Dnpi
Yoweri Museveni, Präsident von Uganda
ምስል AP

ዮዌሪ ሙሴቬኒ እአአ ከ1986 ዓም ወዲህ በዩጋንዳ የፕሬዚደንትነቱን ሥልጣን እንደያዙ ይገኛሉ። ፕሬዚደንት ሙሴቬኒ የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት በተደጋጋሚ ባማሻሻል ካለፉት 28 ዓመታት ወዲህ ሀገሪቱን መምራታቸውን ቀጥለዋል።

በአንድ ወቅት የአንድ አፍሪቃዊ ሀገር ርዕሰ ብሔር ከአስር ዓመት በላይ በሥልጣን መቆየት የለበትም ሲሉ የተናገሩት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ከሥልጣናቸው ለመውረድ ሀሳብ እንደሌላቸው የፖለቲካ ተንታኞች ገልጸዋል። በዩጋንዳ የሚታዩት ሁኔታዎች እንደጠቆሙት፣ በምሕፃሩ «ኤን አርኤም» በመባል የሚታወቀው ገዢው የዩጋንዳ «ናሽናል ሬዚዝተንስ ሙቭመንት» ፓርቲ እአአ በ2016 ዓም በሀገሪቱ ለሚካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ብቸኛው ዕጩ አድርጎ ለማቅረብ እየጣረ ነው። ሙሴቬኒ ለአምስተኛ የሥልጣን ዘመን በዕጩነት እንዲወዳደሩ የተያዘውን ጥረት የተቃወሙ ሶስት የመብት ተሟጋቾች ይህንኑ ተቃውሟቸውን ለምሥራቅ አፍሪቃ የፍትሕ ፍርድ ቤት አቅርበዋል።

Wahlen in Uganda Yoweri Museveni
ምስል AP

የዴሞክራቲክ ፓርቲ የወጣቶች አማካሪ የሆኑት ጠበቃዋ ወይዘሪት ሊሊያን ንዳጊሬት ሮቪንስ ፣ ጆ ናኪቢንጌ በካዩንጋ አውራጃ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀ መንበር እና የዴሞክራቲክ ፓርቲ ወጣቶች ምክትል ኃላፊ ሞዘስ ቢጊርዋ የዩጋንዳ መንግሥት እና ገዢው ፓርቲ «ኤን አርኤም» ሙሴቬኒን ለ2016 ዓም ምርጫ እንደ ብቸኛው ዕጩው ለማቅረብ የጀመረው ጥረቱ ዩጋንዳ አባል የሆነችበትን የምሥራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ የተቋቋመበትን ውል እንደሚጥስ በማስታወቅ ነበር ጉዳዩን እአአ ባለፈው ህዳር አምስት ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት። የ «ኤን አርኤም» እንደራሴዎች ባለፈው የካቲት ወር በኪያንክዋንዚ ሙሴቬኒን በዕጩነት ለማቅረብ ማቀዳቸውን ባወጡት መግለጫ ካስታወቁ በኋላ፣ ለዚሁ ዕቅድ በሀገር አቀፍ ደረጃ ድጋፍ ለማሰባሰብ የካቢኔ ሚንስትሮች እና እንደራሴዎች፣ ሕዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት ችላ በማለት፣ ወደየአካባቢያቸው በመሄድ ቅስቀሳ ከመጀመራቸውም ጎን፣ በመንግሥት ገንዘብ ተጠቅመዋል። ለያንዳንዳቸው አራት ሚልዮን ሺሊንግ ነበር የተሰጣቸው። ይኸው የገዢው ፓርቲ እና የመንግሥቱ ዕቅድ ሕጋዊ እንዳልሆነ በማመልከት ብዙ የሀገሪቱ ዜጎች ተቃውመውታል።የፖለቲካ ተንታኝ አንጀሎ ኢዛማ እንደሚሉትም፣ ይኸው ሕጋዊ ክርክር ሙሴቬኒ በሥልጣን ለመቆየት ለሚያደርጉት ጥረት አንዳችም ተፅዕኖ አይኖረውም።

Uganda Wahlen
ምስል picture alliance/dpa

«ይህ አማራጭ እንደሌለ ያንፀባርቃል። በዩጋንዳ ፖለቲካ መድረክ ላይ የሙሴቬኒ ተፅዕኖ በጣም ከፍተኛ ነው። የሕጉ ማህበረሰብ ለምሳሌ ሙሴቬኒ ለፍትሑ ሥርዓት አንድ ፕሬዚደንት እንዲሾሙ ሀሳብ ቢያቀርብላቸውም፣ እስካሁን ይህን አላደረጉም፣ ስለዚህ ከአንድ ዓመት ገደማ ወዲህ የፍርድ ቤቶች እና የዓቃብያነ ሕጉ ጽሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ የለውም። እና በዩጋንዳ ፍርድ ቤቶች ውስጥ ክስ ለመመሥረት ብታስብ የሚያስገኘው ውጤት አይኖርም። ከዚህ ሌላም ሙሴቬኒ ምክር ቤቱን ተቆጣጥረዋል ። በምክር ቤቱ ውስጥ ፓርቲያቸው ብቸኛው ፓርቲ ነው ሊባል ይቻላል፣ ከሰማንያ ከመቶ በላይ መንበሮች አሉት። »

በዚሁ ክሳቸው ለመድረስ የሚፈልጉት በገዢው ፓርቲ ውስጥ ሌሎች ም በዕጩነት መቅረብ ለሚፈልጉ ዕድል ለመክፈት ሳይሆን እንዳልቀረ ነው አንጀሎ ኢዛማ የሚገምቱት።

« ጉዳዩን ለፍርድ ቤት ባቀረቡበት ድርጊት፣ ዩጋንዳ ውስጥ ዕጩዎችን በማቅረቡ ረገድ የብዝኃነት አሰራር ሊኖር ይገባል የሚለውን አስተሳሰባቸውን ለማሰረፅ የፈለጉ ይመስለኛል። በገዢው ፓርቲ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ አሰራርሊኖር እንደሚገባም ለማሳየት ነው። እንደሚባለው፣ ፓርቲው ሙሴቬኒን ብቸኛው ዕጩ ለማድረግ የሚጥረው ከቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትራቸው እና ከ«ኤን አርኤም» ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አማማ ምባባዚ ሊገጥማቸው የሚችለውን ፉክክር ለማስወገድ በማሰብ ነው። ሆኖም፣ ገዢው ፓርቲ ሙሴቬኒን ብቸኛው ዕጩ አድርጎ ማቅረቡ ሕጋዊ አለመሆኑን እና ፀረ ዴሞክራሲ መሆኑንም ለማጉላት ሲሉ ነው በፍርድ ቤት ክስ የመሠረቱት። »

Uganda Wahlen 2011 Opposition Kizza Besigye
ምስል MARC HOFER/AFP/Getty Images

የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደታዘቡት በገዢው ፓርቲ ውስጥ የሥልጣን ፉክክሩ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው። ይሁንና፣ እንደ ፖለቲካ ተንታኙ አንጀሎ ኢዛማ ግምት፣ ይኸው ፉክክር ለቀጣዩ ምርጫ ያን ያህል ስጋት የሚፈጥርባቸው አይሆንም።

« ፕሬዚደንቱ ቀጣዩን ምርጫ በተመለከተ እየተከተሉት ያለውን አሰራር ስንመለከት፣ ፉክክሩ ቀላል አለመሆኑን ለመረዳት እንችላለን። በተለያየ ደረጃ፣ ማለትም ከቀድሞ ታጋይ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲን ማጠናከር ከሚፈልገው የወጣቱ ትውልድም ፉክክር ገጥሟቸዋል። በቀጣዩ ምርጫ ግን ፕሬዚደንት ሙሴቬኒ ከገዛ ራሳቸው የ«ኤን አርኤም» ፓርቲም ሆነ በጠቅላላ ከዩጋንዳ የፖለቲካ መድረክ ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆንባቸው የሚችል አንድም ተቀናቃኝ የላቸውም። »

አርያም ተክሌ

ልደት አበበ