1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዩክሬይን፤ ፕሮሼንኮ ቃለ ማሃላ ፈፀሙ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 30 2006

አዲስ ተመራጩ የዩክሬይን ፕሬዚዳንት ፔትሮ ፕሮሼንኮ፤ ቃለ ማሃላ ፈፀሙ። በበዓለ ሲመቱ ላይ ከ50 በላይ የዉጭ ሀገር ልዑካን የተገኙ ሲሆን ከመካከላቸዉ የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ዮአሂም ጋዉክ፤ የአዉሮጳ ኅብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሄርማን ቫን ራንፖይ እንዲሁም የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ይገኙበታል።

https://p.dw.com/p/1CEMc
Ukraine Präsident Petro Poroschenko Vereidigung 07.06.2014
ምስል Reuters

የ 48 ዓመቱ ፕሮሼንኮ፤ የቃለ ማሃላዉን ከፈፀሙ በኃላ ባደረጉት ንግግር፤ ሩስያ የያዘቻት የክሪሚያ ደሴት፤ የዩክሬን መሆንዋ፤ እንዲሁም ዩክሬይን በአዉሮጳዉ ኅብረት መግባት ድርድር የሚያስገባ አደለም ሲሉ በግልፅ ተናግረዋል። የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት «ኔቶ» እና የአዉሮጳዉ ኅብረት አዲሱን የዩክሬን ፕሬዚዳንት ፔትሮ ፕሮሼንኮን ቃለ መሃላ መፈፀም በማወደስ ድጋፋ እንደሚያደርጉላቸዉ ገልፀዋል።

የሩስያዉ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸዉ በዩክሬይን ድንበር አካባቢ ጥበቃዉ እንዲጠናከር ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። እንደ ሞስኮዉ መንግሥት ገለፃ ሕጋዊ ዝዉዉርን ለመግታት የተደረገ ርምጃ ነዉ ። ትናንት የጀርመን መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ጋር ተገናኝተው በተነጋገሩበት ሰዓት፤ የሩሲያው መሪ ለዩክሬይን መረጋጋት የታቻላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። ፑቲን፤ «ባለፉት ዐሠርተ ዓመታት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጠብ ጫሪነት ርምጃ እየወሰደች ያለች አገር አሜሪካ ናት። እኛ ፤ በውጭ ሀገር፣ ከሞላ ጎደል አንድም የጦር ሠፈር የለንም። አሜሪካውያን ግን በመላው ዓለም ነው ያላቸው። እነርሱ ከራሳቸው ሀገር ድንበር፣ በሺ ኪሎሜትሮች ርቀት ተጉዘው የሌላውን አገር ሕዝብ ዕጣ ይወስናሉ» ማለታቸው ተገልጿል።

Ukraine Präsident Petro Poroschenko Vereidigung 07.06.2014 Joe Biden
ምስል Reuters

በሌላ በኩል ምስራቅ ዩክሬይን በመፍቀረ ሩስያ ተገንጣዩችና በዩክሬይን ወታደሮች መካከል የሚታየዉ ዉጥረት ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ። ትናንት መፍቀረ ሩስያ ተገንጣዮች በምስራቃዊ ዩክሬይን ስሎቭያንስክ አንድ የዩክሬይን የወታደር የሟጓጓዣ አዉሮፕላንን መተዉ መጣላቸዉ ተመልክቷል። ዛሬ ቃለ ማሃላን የፈፀሙት አዲሱ የዩክሬይን ፕሬዚደንት ፕሮሼንኮ፤ በዩክሬይን ዉጥረት በበዛባቸዉ አካባቢዎች በአፋጣኝ ሰላም ለማምጣት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

አዜብ ታደሰ

ልደት አበበ