1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዩክሬይንና ያልተገታው የእርስ በርስ ውጊያ፣

ረቡዕ፣ የካቲት 11 2007

በምሥራቅ ዩክሬይን የአውራ ጎዳናና ባቡር ሐዲድ መገናኛ መሥመር ላይ በምትገኘው ዴባልትሴቭ በተሰኘችው ከተማ ፤ የተከበበው የኪቭ መንግሥት ጦር ሠራዊትና የምሥራቅ ዩክሬይን አማጽያን ለሳምንታት ብርቱ ውጊያ ሲያካሄዱ ከቆዩ በኋላ ከተማይቱ በአማጽያኑ ቁጥጥር ሥር መዋሏ ተረጋገጠ።

https://p.dw.com/p/1Edux
Ukraine ukrainische Soldaten verlassen Debalzewe
ምስል Reuters/G. Garanich

በምሥራቅ ዩክሬይን የአውራ ጎዳናና ባቡር ሐዲድ መገናኛ መሥመር ላይ በምትገኘው ዴባልትሴቭ በተሰኘችው ከተማ ፤ የተከበበው የኪቭ መንግሥት ጦር ሠራዊትና የምሥራቅ ዩክሬይን አማጽያን ለሳምንታት ብርቱ ውጊያ ሲያካሄዱ ከቆዩ በኋላ ከተማይቱ በአማጽያኑ ቁጥጥር ሥር መዋሏ ተረጋገጠ። የኪቭ መንግሥት ፕሬዚዳንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ፣ ወታደሮቻቸው ከተጠቀሰችው ከተማ እንዲወጡ ማዘዛቸውን አስታውቀዋል፤ አማጽያኑ በበኩላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች በምርኮ መያዛቸውን ገልጸዋል።

AP የተሰኘው የዜና አገልግሎት ድርጅት ዘጋቢዎች እንዳስታወቁት ፣ በዛ ያሉ የዩክሬይን ወታደሮች ዛሬ ጧት የጦር መሳሪያ እንደያዙ አፈግፍገዋል። አንዳንዶች በተሽከርካሪ አቅራቢያ ወደምትገኝ አርተሚቭስክ ወደተባለችው ከተማ በጭነት ተሽከርካሪዎች አምርተዋል። ጺማቸውን ያልላጩ የተናደዱና ድካም የሚታይባቸው ወታደሮችም በእግራቸው ሲጓዙ ታይተዋል። ከመካከላቸው አንደኛው ወታደር በመንግሥት ወታደሮች ላይ ብርቱ ጉዳት መድረሱን ሌላው ደግሞ በአማጽያኑ ድብደባ ሳቢያ ለቀናት ያለምግብ መሰንበታቸውን ገልጿል።


ፕሬዚዳንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ፤ «ዴባልትሴቭ ፣ ከእኛ ቁጥጥር ወጥታና ተከባም አታውቅም፤ ወታደሮቻችን የወጡትም በሥርዓት በተደራጀ መልክ ነው» ሲሉ በቴሌቭዥን መግለጫ ሰጥተዋል።
የሩሲያ ቴሌቭዥን ፣ በዛ ያሉ የኪቭ መንግሥት ወታደሮች ፤ በአማጽያኑ እየተመሩ በአንድ የገጠር መንገድ ሲጓዙ አሳይቷል።
የዩክሬይን መንግሥት ምክትል መከላከያ ሚንስትር ሰርጌይ ጋሉሽኮ በበኩላቸው እንዲህ ነበረ ያሉት---
«የከተማይቱና አካባቢዋን ይዞታ በአሁኑ ይዞታ መግለጽ አስቸጋሪ ነው። በሩሲያ ወታደሮች በመደገፍ አሸባሪዎቹ ከሌሎች አካባቢዎች ተጓዳኞቻቸውን ወደ ጦር ግንባር ፣ ወደ ዴባልትሴቭ በማምጣት ፤ በእግረኛ ጦር ፤ በካባድ መሳሪያ በመድፍና በመሳሰለው ተዋግተዋል። ስምምነቱ ሁሉ ተጥሶ በኛ ይዞታ ላይ 5 ጊዜ ነው ጥቃት የተሰነዘረው። »
አማጽያኑ፣ በዴባልትሴቭ ከቀናቸው በኋላ፣ ሌሎች ከተሞችንም ከዩክሬይን ጦር ሠራዊት ይዞታ እናስለቅቃለን በማለት ዝተዋል። 25,000 ኑዋሪዎች ባሏት ከተማ በተዋጊዎችና በሲቭሉ ሕዝብ ስለደረሰ ጉዳት ዘልቆ በመግባት የገለጠ ታዛቢ የለም።
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን፤ ትናንት ቡዳፔይት ሃንጋሪ ውስጥ በጉብኝት ላይ እንዳሉ ለዩክሬይን ውዝግብ በጦር መሣሪያ መፍትኄ እንደማይገኝ ከመግለጻቸውም ዛሬ የተከሠተው የማይቀር እንደነበረ ቀደም ሲል የሚታወቅ ጉዳይ ነበረ ብለዋል።

Ukraine ukrainische Soldaten verlassen Debalzewe
ምስል Reuters/G. Garanich


«በዚያ የሆነው ሁሉ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ይታወቅ ነበር። እኛ እንደምንገነዘበው ከሚንስኩ ስብሰባ በፊት፣ እንዲያውም ከዚያ አንድ ሳምንት ያህል ቀደም ሲል፤ የዩክሬይን ጦር ሠራዊት ከፊል በተጠቀሰው ቦታ ተከቦ ነበር። በሚንስኩ ስብሰባ ላይም ስለዚህ ጉዳይ በግልጽ ነበረ የተናገርሁ።»
የአውሮፓው ሕብረት የውጭ ፖለቲካ መርሕ ኀላፊ ፌደሪቻ ሞጌሪኒ ፣ የምሥራቅ ዩክሬይን አማጽያን የተኩስ አቁሙን ስምምነት ጥሰዋል ሲሉ ወቅሰዋል።
ከዋሽንግተን የዩናይትስ ስቴትስ አስተዳደር፤ የምሥራቅ ዩክሬይን አማጽያን የተኩስ አቁም ስምምነትን አፍርሰዋል በማለት ጠንከር ባሉ ቃላት ከማውገዙም፤ የተኩስ አቁሙ ስምምነት ከእንግዲህ መጣሱ ከቀጠለ፤ ሩሲያን የበለጠ ዋጋ ያስከፍላታል ማለቱ ተጠቅሷል።

Flüchtlinge aus Donezk kommen in Sewastopol an
ምስል Reuters/E. Korniyenko

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ