ዩኤስ አሜሪካ በሩዋንዳ ላይ የጣለችዉ ማዕቀብ
ዓርብ፣ መስከረም 24 2006በዴሞክራቲክ ኮንጎ የሚንቀሳቀሰዉን M23 የተሰኘዉ ቡድን ትደግፋለች ሲል ባቀረበው ምክንያት ነው ። የሩዋንዳ መንግሥት ግን የዩናይትድ ስቴትስን ክስ አይቀበልም። ዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ትናንት እንዳስታወቀው ሩዋንዳ በተጣለባት ማዕቀብ ምክንያት ዩናይትድ ስቴትስ የምትሰጠው ዓለም ዓቀፍ ወታደራዊ የትምህርትና የሥልጠና እርዳታ ይቋረጥባታል ። የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ማሪየ ሃርፍ እንደገለጹት የአሜሪካንንወታደራዊ ቁሳቁሶችን ለመግዛትና አገልግሎት ማግኘት የሚቻልበትን ወታደራዊ የፋይናንስ ድጋፍም አታገኝም ። መሰል ወታደራዊ ማዕቀብ የሚጣለው በሩዋንዳ ላይ ብቻ ሳይሆን በሱዳን፤ በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ እና በማይንማርም ላይ መሆኑን ትናንት አስታወቋል። ሆኖም ሱዳን፣ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክና ማይንማር እስካሁን ከዩኤስ አሜሪካ ወታደራዊ ድጋፍ ያግኙ አያግኙ ግልፅ ግልጽ አይደለም። በዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪቃ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሊንዳ ግሪንፊልድ እንዳስታወቁት፤ የመንግሥታቸው ዓላማ ህፃናትን በውትድርና እንዳይሰማሩ ና እንዳይመለምሉ ከሚያደርጉ ሃገራት ጋር በትብብር መስራት ነው። ረዳት ሚኒስትሯ በሩዋንዳ ላይ ማዕቀብ የተጣለው ሃገሪቱ ህፃናትን በውትድርና የሚመለምለውንና የሚያሰልፈውን M23 የተባለውን ቡድን በመደገፏ መሆኑን አስታውቀዋል። በሩዋንዳ ላይ የተጣለዉ ማዕቀብ ህጻናት በማንኛዉም ወታደራዊ እንቅስቃሴ ላይ መሳተፋቸዉ እስካልቆመ ድረስ፤ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። ዩኤስ አሜሪካ ሩዋንዳ ቡድኑን ለመደገፏ በማስረጃነት የምታቀርበው ዓለም ዓቀፉ የስብዓዊ መብት ተሟጋች ሂዩመን ራይትስ ዋች ስለ ሩዋንዳ ያወጣውን ዘገባ ነዉ ።ሂዩመን ራይትስ ዋች ዘገባውን ያቀረበው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማነጋገር መረጃዎችን ካሰባሰበ በኋላ ነበር። የሂዩመን ራይትስ ዋች አጥኚ ካሪና ቴርትሳኪን እንደሚሉት ሩዋንዳ አማፂውን M23ን የምትረዳው በተለያየ መንገድ ነው፤
« ሩዋንዳ የምትሰጠው ድጋፍ የተለያየ ቅርፅ አለው ። ለምሳሌ የታጠቁና የደንብ ልብስ የለበሱ ወታደሮች ከሩዋንዳ ወደ ኮንጎ ድንበር አቋርጠው በተደጋጋሚ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አንዱ ነው ። ኮንጎ ለሚገኘው ለ M 23 የጦር መሣሪያዎችን ጥይቶችንና ምግብ ማቅረብን ያካትታል ። ከM23 ጋር የሚዋጉ ወጣት ወንዶችን ከሩዋንዳ መመልመልንና በመጨረሻም የሩዋንዳ ወታደራዊ መኮንኖች በኮንጎ ድንበር ላይ በተካሄደ የአዳዲስ የ M 23 ምልምሎች ሥልጠና ላይ መሳተፈቸውንም ይጨምራል»
ዩናይትድ ስቴትስ በጉዳዩ ላይ ከሩዋንዳ መንግስት ጋር ዉይይት እንደምትቀጥል በዩኤስ አሜሪካ የአፍሪቃ ጉዳዮች ረዳት ፀሃፊ ሊንዳ ግሪንፊልድ ገልጸዋል።
የተመድ እና የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፤ በኮንጎ እና ሩዋንዳ ወሰን ላይ የሚንቀሳቀሰዉ አማጺውን ቡድን M23ን፤ ሰዎችን በመግደል ወንጀል፤ ዉጥረት በበረታበት አካባቢ፤ ሕጻናትን በዉትድራና በማሳማራት፤ እና ህብረተሰቡንም ከቤት ንብረቱ በማፈናቀል ወንጀል፤ በተደጋጋሚ መክሰሳቸዉ ይታወቃል። የቀድሞ የኮንጎ ጦር አባላት ስብስብ የሆነው ቱትሲዎች የሚያመዝኑበት M23 የተባለው አማፂ ቡድን ደግሞ፣ እጎአ በ2009 ዓ,ም የተደረሰበትን የሰላም ስምምነት አላከበረም ሲል የኮንጎ መንግስት ይከሳል።
ሩዋንዳ የM23አማጺያን ትረዳለች በሚል በተደጋጋሚ ብትወነጀልም፤ የኪጋሊ መንግስት ግን ሲያስተባብሉ ቆይቷል ።አሜሪካን በሩዋንዳ ስለጣለችው ማዕቀብ የሩዋንዳ ጦር ዛሬ በሰጠው አስተያየት ሃገሪቱ በማይመለከታት ጉዳይ ተጠያቂ መሆኗ አስገራሚ መሆኑን አስታውቆ ሩዋንዳም ህፃናትን በውትድርና ከሚያሰልፉ ሃገራት ጋር መደመሯ መረጃ አልባ ነዉ ሲል አጣጥሎአል።
አዜብ ታደሰ
ሂሩት መለሰ