1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የHIV ቫይረስ ስርጭትና ያለበት ደረጃ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 14 2005

ኢትዮጵያ ዉስጥ በHIV ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መሄዱ እየተነገረ ነዉ። በአንጻሩ የጸረ ኤድስ መድሃኒት የሚወስዱ HIV በደማቸዉ የሚገኝ ወገኖች ቁጥር መቀነሱ ተገልጿል። መድሃኒቱ ከተጀመረ መቋረጥ እንደማይኖርበት ነዉ ባለሙያዎች የሚያሳስቡት።

https://p.dw.com/p/19TgP
ምስል picture-alliance/dpa

ታማሚዎችን በቅርበት የመከታተሉ እድል ያላቸዉ ቫይረሱ በደማቸዉ የሚገኝ ወገኖች ያቋቋሟቸዉ ድርጅቶች የመድሃኒት አወሳሰድ ክትትሉን ማድረግ ትተዉ ኃላፊነቱን ሌላ አካል እንደያዘዉ ይናገራሉ። መድሃኒቱ ምግብ ያስፈልገዋል የሚሉ ወገኖች በበኩላቸዉ ችግር አንዱ ምክንያት ነዉ ባይናቸዉ።

የወንጌላዊት ቤተክርስቲያን የዜና ወኪል ከጆሃንስበርግ እንደዘገበዉ ከሆነ የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ከሰተብርሃን አድማሱ ኤድስን ከኢትዮጵያ ፈጽሞ ማጥፋት የሚቻል እንደሆነ ነዉ የገለጹት። እንደዘገባዉ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2001ዓ,ም እስከ 2011ዓ,ም ድረስ አዲስ በHIV ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል፤ 90 በመቶ። ይህን ማድረግ የቻለም ሌላ አፍሪቃዊ ሀገር የለም።

Medikament AIDS Truvada
ምስል AP

UNAIDSን የጠቀሰዉ ይኸዉ ዘገባ እንደሚለዉ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2005ዓ,ም ወዲህም በኤድስ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር 50 በመቶ ቀንሶ ታይቷል። በጎረቤት ኬንያና ጅቡቲ አዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በ32 በመቶ እና 58 በመቶ ነዉ እንደቅደም ተከተላቸዉ የቀነሰዉ። የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩን የጠቀሰዉ የዜና ወኪል ከአራት ዓመት በፊት ሃኪም ቤቶች በርካታ የኤድስ ታማሚዎች እንደነበሯቸዉ፤ እንዲያም ሆኖ ግን አንድ ሰዉ HIV በደሙ እንዳለ ለመግለጽ የሞት ፍርድ ያህል እንደሚከብደዉ ማመልከታቸዉን ዘግቧል። ስለበሽታዉ በግልጽነት መነጋገሩ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ከነበረዉ ቀስ በቀስ እየተሻሻለ የመጣበት ሁኔታ መኖሩ ይታያል። ቫይረሱ በደማቸዉ እንዳለ በመግለጽ ሌሎችን ስለቫይረሱ ለማስተማር አደባባይ የወጡ ወገኖች በማኅበራት ተሰባስበዉም የተሻሉ እንቅስቃሴዎች ያደረጉባቸዉ ጊዜያትም ታይተዋል። ኅብረተሰቡ ስለHIV ቫይረስ ምንም አልሰማም የሚባልበት ጊዜ ላይ አይደለም ያለዉ፤ መድሃኒቱም በነፃ መታደል ከጀመረ ከአምስት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። የተሻለ ዉጤት ሲበቅ ተገኘ የተባለዉም ቢሆን ስጋት ላይ መንጠላጠሉ ግን ገና ብዙ መሠራት እንደሚጠበቅ አመላካች ነዉ። ቫይረሱ በደማቸዉ ከሚገኝና መድሃኒት ከሚወስዱ ወገኖች 15 በመቶዉ የሚሆኑት መድሃኒት መዉሰድ አቁመዋል። ምን ያህል ታማሚ መድሃኒት አቆመ የሚለዉን ለመግለጽ እንደማይችሉ ያመለከቱት የመቅድም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ዘመነ የመድሃኒት አወሳሰድ ክትትሉ መዳከሙን በእርግጠኝነት ይናገራሉ።

Clinton in Äthiopien HIV AIDS The Clinton Foundation
ቢል ክሊንተን ታማሚዎችን ሲጎበኙምስል picture-alliance/ dpa

ዶክተር ይገረሙ አበበ የክሊንተን ፋዉንዴሽን የኢትዮጵያ ተጠሪ ምንም እንኳን ስለተጠቀሰዉ ጉዳይ የሰሙት ባይኖርም መድሃኒቱን ማቋረጥ ፈጽሞ እንደማይገባ ነዉ ያመለከቱት። መድሃኒቱን መዉሰዱን ያስታጎለ ታካሚ ወዲያዉ በሰዉነቱ ላይ የሚያየዉ ለዉጥ ላይኖር ይችላል። ያ ግን ረዥም ጊዜ አይፈጅም ዶክተር ይገረሙ እንደሚሉት የሰዉነትን የበሽታ መቋቋም አቅም እያዳከመ ከወራት በኋላ ሌላ መዘዝ ይከተላል።

HIV ቫይረስ በደማቸዉ የሚገኝ ወገኖች መድሃኒት ለማቋረጣቸዉ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ምክንያቶችን ሲሰጡ ይደመጣል። ዋነኛዉ ተመጣጣኝ ምግብ አለማግኘት ነዉ። HIV በደማቸዉ የሚገኝ ወገኖችን በሚችሉት አቅም በመደገፍ የበኩላቸዉን ለማድረግ የሚንቀሳቀሱት ወ/ት ሂሩት ገድሉም፤ መድሃኒቱ እኮ ምግብ ያስፈልገዋል ይላሉ።

ቀደም ሲል የተለያዩ የአሜሪካን ዩኒቨርሲቲዎች ከCDC ጋ በመሆን ለያንዳንዱ HIV በደማቸዉ የሚገኝ ወገኖች ላቋቋሙት ማኅበራት የገንዘብ ድጋፍ እየሰጡ ማኅበራቱ በአባላት አማካኝነት የመድሃኒት አወሳሰድ ክትትሉን ያካሂዱ ነበር ያላሉ አቶ መንግስቱ። ያ አካሄድ አምስት ዓመት ሆነዉ ከተለወጠ። በማኅበራቱ ጥምረት እንዲከናወን ነዉ CDC አደረገ የሚሉት እሳቸዉ። አሁን ችግሩ መድሃኒት ከሚወስዱ ወገኖች የሚያቋርጡት 15 በመቶ መድረሳቸዉ ይህም አዲስ አበባ አካባቢ ብቻ መሆኑን ነዉ አንዳንድ ዘገባዎች ያመለከቱት። እንዲህ ያለዉ መዘናጋት እንዳይከሰት ጥምረቱ ማድረግ የነበረበት ይላሉ የመቅድም ኢትዮጵያ ዳይሬክተር፤ የመድሃኒት አወሳሰዱ በትክክል ክትትል የሚያስፈልገዉ መሆኑ እየታየ ነዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ