1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ14 ዓመቷ የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ዩጋንዳዊት

Lidet Abebeረቡዕ፣ የካቲት 23 2008

የራፕ ሙዚቃ በምስራቅ አፍሪቃ ሀገራትም ዝነኛ እየሆነ መጥቷል። ራፕ « የወሮ በላ » ወይም «ዱርዬ ወንዶች» ሙዚቃ ነው መባሉ እየቀረ ነው። አንዳንድ የሂፕ ሆፕ ሙዚቃ አርቲስቶች ራፕን ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መልዕክቶችን ማስተላለፊያ አድርገው ይጠቀሙበት ጀምረዋል፣ ለምሳሌ የ14 ዓመቷ ዩጋንዳዊት የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ዞኤ ካቡዬ።

https://p.dw.com/p/1I54M
Uganda Zoe Kabuye, a.k.a. MC Loy
ምስል DW/G. Hofmann

[No title]

የ14 ዓመቷ ዩጋንዳዊት ዞኤ ካቡዬ የምታነሳቸው ርዕሶች በርካታ ናቸው። ሙስና፣ ህፃናት ላይ የሚፈፀም ጥቃት እና ወቅታዊ የማህበረሰብ ጉዳዮች ጥቂቶቹ ናቸው። ለወጣቷ ሙዚቃ የማይመቹ እውነታዎችን ለማንሳት እድል ፈጥሮላታል። ይህ በመድረክ ላይ ብቻ ሳይሆን በቴሌቪዥን ጭምርም ነው።የዞኤ ታሪኮች በነዚህ ጉዳዮች ላይ ካላወሱ ደግሞ ወጣቷ ስለ እግዚያብሔር ፍቅር ፣ ይቅር መባባል እና የክርስትና ዕምነት በራፕ መልክ ትጫወታለች።

ዞኤ ካቡዬ ከድምፅ ማጉያ ፊትለፊት ተቀምጣ መልዕክቷን ስታሰራጭ፤ ፊት ለፊቷ የተቀመጡ ሌሎች ወጣቶች አንገታቸውን እየነቀነቁ ለመልዕክቷ እውቅና ይሰጣሉ። በእድሜ ትንሿ የዩጋንዳ ራፕ አቀንቃኝ MC LOY በሚባል መጠሪያ ስሟ ነው የምትታወቀው። ወጣቷ በሀገሯ ዝነኛ መሆን የጀመረችው NTV በሚባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ዜናን በራፕ መልክ ስታቀርብ ነው። በዚህ መንገድም ዜና መከታተል የማያዘወትሩ ወጣቶችን በሙዚቃ ለመሳብ ችላለች።

« ሀገራቸው ውስጥ እና ውጭ ሀገር ምን እየተከሰተ እንደሆነ እንዲያውቁ ይረዳቸዋል።እውነት ነው የምልህ በአለም ላይ የሚሆነውን ለማወቅ ይረዳል። ምክንያቱም በዚህ አለም ላይ እየኖርክ የሚሆነውን ካላወቅ ወጥፎ ነገር ወይም ችግር ውስጥ ነው ያለኸው»

14.06.2014 DW Karte Online Uganda neu

የስርጭት ሰዓት ደርሷል። MC LOYም ድምፅ ማጉያውን ለመጨበጥ ዝግጁ ናት። የዛሬው ርዕስ የትምባሆ ቁጥጥርን ይመለከታል።« በትምባሆ ቁጥጥር ላይ እአአ በ2014 የቀረበው ረቂቅ በቅርቡ በዩጋንዳ ምክር ቤት ተግባራዊ እንዲሆን እና ጠንካራ ርምጃ እንዲወሰድበት ተላልፏል። ከዚህም በተጨማሪ ህጉ ኢኮሞሚውን እና የታባኮ ገበሬዎችን ሊጎዳ ይችላል።»

ትላለች ወጣቷ። ዞኤ በተለያዩ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎችን እና ያሉትን ዘርፈ ብዙ ነገሮች በዝግጅቶቿ በማንሳት በሀገሪቱ ፕረስ ነፃነት ላይ ያለውን ውስንነት ለማሻሻል ትሞክራለች። በቻለችው መጠን ጋዜጣ እየገዛች በሀገሪቱ ስላሉ ክስተቶች ታነባለች። ትልቁ ችግር ግን የትምህርት እጥረት ነው ትላለች።«ይህ ህፃናት ላይ ከሚፈፀሙ ጥቃቶች አንዱ ነው። አንድን ልጅ ወደ ትምህርት ቤት አለመላክ። ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ለመላክ ገንዘብ የሌላቸውን ወላጆች ለመውቀስ አልፈልግም። የምወቅሰው ለህፃናት፣ ለትምህርት ለመሳሰሉት መሰረተ ልማቱን ያልዘረጋው መንግሥትን ነው።»

ዞኤ ካቡዬ አንድ ቀን የመጀመሪያዋ ሴት የዩጋንዳ መሪ የመሆን ምኞት አላት። ለፕሬዚዳንትነት እጩ ሆና ለመወዳደር ግን በሀገሪቱ ህገ መንግሥት መሠረት 35 ዓመት ሊሞላት ይገባል። እስከዛው ሌሎች ወጣት የዩጋንዳ አድናቂዎቿን የምታዝና እና የምታስተምርበት በቂ ጊዜ አላት።

አየኮ ሙስባንሂሪ /ልደት አበበ
አርያም ተክሌ