1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ጉዳይ

Merga Yonas Bulaረቡዕ፣ ሰኔ 8 2008

የኢትዮጵያ የትምህርት ሚንስቴር የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ለመስጠት ጥቂት ቀናት ሲቀር ነበር የፈተናዉ መልስ ሾልኮ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ በመሰራጨቱ ፈተናዉን ለማቆም መገደዱን ማስታወቁ ይታወሳል።

https://p.dw.com/p/1J6xQ
Karte Äthiopien englisch

[No title]

ይህንንም ተከትሎ የሚንስቴር መሥርያ ቤቱ ፈተናዉን ከሰኔ 27 እስከ 30 2008 ዓ/ም ለመስጠት አቅዶ እንደነበር በመግለጫዎቹ አስታዉቋል። ይሁን እንጅ ፈተናዉ የሚጀመርበት ቀን የራመዳን ፆም ፍቺ በዓል ላይ ስለሚደረብ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የፈተናዉ ጊዜ እንዲራዘም ለትምህርት ሚኒስቴር ባቀረበዉ ጥያቄ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከሃምሌ 4 እስከ 7 2008 ድረስ እንዲሰጥ መወሰኑን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ያቀረበዉን ጥያቄ ይዘት በተመለከተ የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝደንት ሼኺ ኡመር ኢማም ተማሪዎቹ ፆሙን እያሰቡ የሚፈተኑት ፈተና ጥሩ ዉጤት አያመጣም በሚል ሰብብ መሆኑን ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል።

የፈተናዉ ጊዜ በድጋሚ የተለወጠዉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አቀረበ በተባለዉ ጥያቄ እንዳልሆነ ግን በድምጻችን ይሰማ እና በኦሮሞ መብት ተሟጋቾች መሆኑን የፖለትካ ተንታኝ እና የኦሮሞ መብት ተሟጋች አቶ ጀዋር መሐመድ ይናገራሉ።

Oromo Proteste in Äthiopien
ምስል Oromia Media Network

አሁንም ለፈተናዉ የተሰጠዉ ቀነ ገደብ በቂ ባለመሆኑ ለሦስተኛ ግዜ እንዲራዘም ግፊት የማድረግ እቅደ እንደነበራቸዉ ያመለከቱት አቶ ጀዋር መሀመድ ይህኛዉን ሃሳባቸዉን የቀየሩበት ምክንያትም ተማሪዎቹ እና ፈታኞቹ ላይ የበለጠ ጉዳት እንዳይደርስ ታስቦ መሆኑ ገልጸዋል።

የተራዘመዉ የፈተናዉ ጊዜ በቂም ባይሆን በኦሮሚያ ክልል ያሉት ተማሪዎች ፈተናዉን እንዲፈተኑ የመከሩት አቶ ጀዋር መምህራንም ሆኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለተፈታኞቹ የማካካሻ ትምህርት አስቀድመዉ እንዲሰጡም አሳስበዋል።
ከኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር የበለጠ መረጃ ለማገኘት ያደረግነዉ ጥረት አልተሳካም።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ