1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ 2009 ዐበይት ሳይንሳዊ ክንውኖችና ክሥተቶች፤

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 21 2002

2009 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት፣ በተለያዩ ፣ የፖለቲካ ፣ የኤኮኖሚና ማኅበራዊ ኑሮ ጉዳዮች የተለያዩ አዎንታዊና አሉታዊ ሂደቶች እንደተከሠቱበት ሁሉ በሳይንሱም ዓለም ብዙ የምርምር ተግባራት መከናወናቸው፣

https://p.dw.com/p/LHMT
ምስል picture alliance / dpa

በሥነ-ቴክኒኩም የፈጠራ ውጤቶች መመዝገባቸው ቢታወቅም፣ የሰው ልጅ ካለው ሰፊ የማወቅ ጉጉት አንጻር ገና ያልተደረሰባቸው አያሌ ጉዳዮች መኖራቸውን ነው የምንገነዘበው።

በሥነ-ህይወት፣ የዝግመታዊ ለውጥ አባት የሚሰኘው የቻርለስ ዳርዊን 200ኛ ዓመት የልደት በዓልና ስለዝግመታዊ ለውጥ፣ ነባቤ ቃሉን ይፋ ያደረገበት 150ኛ ዓመት በተለያዩ ስብሰባዎች መታሰቡ አልቀረም። የቻርለስ ዳርዊን የፍጥረታት ዝግመታዊ ለውጥ ነባቤ-ቃል፣ አሁንም ለዛሬው ዘመን የሥነ ፍጥረት ሊቃውንት የሚሰጠው ትርጓሜ አለ ወይ?

በጀርመን ደቡባዊ ከተማ በኮንስታንዝ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ጀርመናዊው የሥነ ህይወት ፕሮፌሰር አክሰል ማየር--

«የዘመናዊው ሥነ ህይወት መሠረት ነው። እርግጥ ነው ዳርዊን ከ 150 ዓመት ይህን ነባቤ -ቃል ቢጽፍም፣ ከ 50 ዓመት በኋላ ምን ሊከሠት እንደሚችል የሚያውቅበት ሁኔታ አልነበረም። ያም ሆኖ፣ ያኔ የጻፈው፣ ዛሬም ቢሆን የዝግመታዊ ለውጥን ክንውን የሚያስሽር አይደለም።»

በሳይንሳዊ አገላለጽ፣ ሥልጡን እንስሳ የሚባለው ሰው፣ ከጦጣዎችና ዝንጀሮዎችም

ጋር የሚያዛምደው ነገር እንደሌለ የዘንድሮው እጅግ አስደናቂ የሥነ ፍጥረት በተለይም የቅሪተ-አፅም ምርምር ውጤት ይፋ አድርጎታል። የዳርዊን መታሰቢያ ዘመን ከማክተሙ በፊት በተለይም On the Origin of Species የተሰኘውን የዝግመታዊ ለውጥ ነባቤ-ቃሉን ያሠፈረበትን ፣ 1,250 ቅጂ መጸሐፍ ያሳተመበት 150 ኛ ዓመት ባለፈው ኅዳር ከመታሰቡ በፊት ፣ አንድ ወር ቀደም ሲል ባለፈው ጥቅምት መሆኑ ነው፣ የቅሪተ አፅም ተመራማሪዎች፣ የዓመቱ እጅግ አስደናቂ ግኝት ያሏትን የሰው የዘር ግንድ አስተዋወቁ። በአትዮጵያ ምድር የተገኘችው ፣ 4,4 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረችው ፍጡር ፣ በዕድሜ፣ «ድንቅነሽ»ን «ሉሲ»ን ማስከንዳቷ ነው የተመሠከረላት ።

በአፋርኛ «አርዲ» በሳይንሳዊ አጠራር( Ardipithecus Ramidus ) «ሥረ-መሠረት » ማለት ነው ፣ ትርጉሙ!፣ በዚህ ስም የምትታወቀው ፍጡር፣ አካላቷ በጸጉር የተሸፈነ እንደነበረ የሚገመት ሲሆን፣ ቁመቷ 1,20 ሜትር ያህል ክብደቷም፣ 50 ኪሎግራም ያህል ነበረ፣ ተብሏል። አርዲ በመጀመሪያ የተገኘችው እ ጎ አ በ 1992 ዓ ም እንደነበረ ቢታወቅም፣ በአርሷ ዙሪያ ለቀረቡ ጥያቄዎች የነጠሩ መልሶች ለማግኘት ብዙ ዓመት ወስዷል። ከተመራማሪዎቹ መካከል ፣ በዩናይትድ እስቴትስ ፣ ካሊፎርኒያ፣ የበርክሌይ ዩኒቨርስቲ ባልደረባ Tim White ስለአርዲ የአጽም ቅሪት ሲያስረዱ እንዲህ ነበረ ያሉት።--

«ይህች ፍጡር ገና ፍጹም የተሟላ ዕድገት እንዳላሳየች ብናይም፣ ዝግመታዊው ለውጥ ልዩ የሚያደርጉዋት ባኅርያት እንደነበሯት አመላክቷል። እናም ፣ ይህ የሚያሳየው (ከሰው)የቤተሰብ ግንድ በኩል መሆንዋን ነው። ከዝንጀሮ/«ቺምፓንዚ» ዝርያ ሥረዎ-ግንድ ግን የምትደብ አይደለችም። ከጋራ የዘር ሐረግ ግንድም ሆነ ምንጭም አይደለችም።»

በፈረንሳይና እስዊትስዘርላንድ ድንበር በትኅተ-ምድር ፣ ስለፍጥረተ ዓለም መቅድማዊ ይዘት ለማወቅ የሚመራመሩት ሳይንቲስቶች፣ በ 2000 ዓ ም ጳጉሜ ማለቂያ ላይ ሥራቸውን ጀምረው ከ ዘጠኝ ቀናት በኋላ ቢያቋርጡም የአቶም ቅንጣቶችን መጨፍለቂያው መሣሪያ ተጠግኖ ባለፈው መጸው እንደገና ሥራውን በመጀመር፣ አዲስ ክብረወሰን ባስመዘገበ መልኩ እጅግ ኅይለኛ የሙቀት ኃይል ማመንጨት መቻሉ የሚታወስ ነው።

በመረጃ ሥነ ቴክኒክ ረገድ መልእክትን በፍጥነት በመላክና በመቀበል ረገድ አፍሪቃን እንደተቀረው ዓለም ተጠቃሚ ለማድረግ ባለፈው ዓመት በሐምሌ ወር የምሥራቅ አፍሪቃ አገሮች በባህር ወለል በሚዘረጋ ልዩ የመረጃ ማስተላለፊያ ሽቦ ለመገልገል የሚያስችለው መረብ ተዘርግቶላቸዋል። በዚህ ተግባር የተሠማራው «ሲኮም» የተባለው ድርጅት ነው።

ድበብ አፍሪቃ ቀደም ሲልም በሰፊው አገልግሎት የምታገኝ አገር ስትሆን አዲሱ ፕሮጀክት ይበልጥ ተጠቃሚ ያደርጋታል ፣ ኢትዮጵያ በዚህ ፈጣንና ጠቃሚ የመረጃ አግልግሎት አልተካተተችም።

ባለፈው ሐምሌ 14 ቀን 2002 ዓ ም፣ አሜሪካውያን አፖሎ 11 በተሰኘችው መንኮራኩር ሰው ጨረቃ ላይ እንዲያርፍ ያበቁበት 40ኛ ዓመት በልዩ ታዝታ ነበረ የታሰበው።

በፀሐያዊ ጭፍሮች ከሚገኙት አያሌ ጨረቃዎች ሁሉ በግዝፈት የ,5ኛነቱን ቦታ የያዘችው ፣ 3,476 ኪሎሜትር ወርድ ያላት የኛይቱ ጨረቃ ፣ ጨለማውን ሰማይ በማድመቅ ለዓይን ሲሳይ ከመሆን ባሻገር በምድር ላይ ለለሚገኘው ፍጡር ሁሉ፣ ኅልውና እጅግ ተፈላጊ ናት። ጨረቃ፣ በስበት ኃይል የውቅያኖስን ማዕበል የምትቀሰቅስ መሆኗ ባይካድም፣ ምድራችን በራሷ ዛቢያ የምትሽከረከርበትን ፍጥነት በማስተካከል አንዱ ቀን 24 ሰዓት እንዲኖረው ያበቀች ናት። እርሷ ባትኖር ኖሮ፣ አንዱ የምድር ቀን (መዓልትና ሌሊቱ )

24 ሰዓት መሆኑ ቀርቶ ስምንት ሰዓት ብቻ ይሆን ነበር። ምድራችን ፣ አሁን ካላት የተስተካከለ ፍጥነት በተዛባ እጅግ ፈጥና ብትሽከረከር ኖሮ ልክ በጁፒተርና ሳተርን እንደሚከሠተው ሁሉ በአኛዋም ፕላኔት በሰዓት እስከ 500 ኪሎሜትር የሚከንፍ ነፋስም ሆነ ወጀብ ለፍጥረታት ኅልውና ጠንቅ በሆነ ነበር።

ጨረቃ ሌላው ዐቢይ ጠቀሜት ፣ ምድራችን በዛቢያዋ 23 ዲግሪ ዘመም ብላ በመሽከርከር፣ በዚሁ እንድትጸና ማድረጓ ነው። ያለጨረቃ ማስተካከያ እርምጃ ምድራችን እስከ 85% ያህል ዘመም በማለት የፀሐይ ብርሃንና ሙቀት ሥርጭት ሊለወጥ በቻለ ነበር። ይህም ማለት ሞቃቱ የምድር ሰቅ፤ በቀዝቃዛ በረዶ ተሸፍኖ፣ የምድር ዋልታዎች፣ 80 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ገደማ በሚደርስ ሙቀት ይቃጠሉ ነበር። በመካከለኛው አውሮፓም የበጋው ወራት የተራዘመና ሙቀቱም 60 ዲግሪ፣ የክረምቱም ከዜሮ በታች 50 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ገደማ ሊደርስ በቻለ ነበር። ከዚህ ሌላ ራቅ ያሉ ፕላኔቶችንና ስባሪ ከዋክብትን ለማሰስ ጨረቃ ስንቅ ማሸጋገሪኢ መናኸሪያ ሆና እንድታገለግል መታሰቡም ሆነ መታቀዱ አልቀረም።

ከዚህ ቀደም እንደተገለጠውም ፣ የዩናይትድ እስቴትስ የኅዋ ምርምር ድርጅት፣ ጨረቃ ላይ ፣ በረጋ በረዶነት መልኩ ውሃ መገኘቱን አረጋግጧል።

2009 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት የሥነ-ፈለክ መታሰቢያ ዘመን ተብሎ እንደመዘከሩ መጠን የዘመናዊው ሥነ-ፈለክ ተመራማሪዎች ፣ ጋሊሊዮ ጋሊሊዪ ፣ እ ጎ አ በ 1609 ዓ ም፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በቴሌስኮፕ ሰማዩን የቃኘበት ድርጊት እንዲሁም ጀርመናዊው የሥነ-ፈለክ ሊቅ ዮሐንስ ኬፕለር ስለፕላኔቶች እንቅሥቃሤ የተፈጥሮ ህግጋትን ያሳወቀበት 400 ኛ ዓመት በልዩ ልዩ ስብሰባዎችና ገለጣዎች ነው የታወሰው።

2009 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት እንዳጋጣሚ ከዚሁ የሥነ ፈለክ መታሰቢያ ዘመን ጋር በተገጣጠመ ሁኔታ ዓመቱን በነገው ዕለት የሚሰናበተውና ለ 2010 ቦታውን የሚለቀው፣ ሌሊቱን፤ በሙሉ በጨረቃ ብርሃን በማድመቅ ነው። ጨረቃ ፣ በዓመት መጨረሻ (በአዲስ ዓመት ዋዜማ)ደምቃ ሙሉ-ብርሃን የምትሰጥበት ሁኔታ አዘውትሮ የሚያጋጥም አይደለም። በአጠቃላይ በ 20ኛ ው ክፍለ-ዘመን ፣ እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ የተከሠተው፣ 4 ጊዜ ብቻ ነው። እ ጎ አ ፣ በ 1933፣ በ 1952፣ በ 1971 እና በ 1990 ! ከእንግዲህ ወዲያ፣ በያዝነው ክፍለ ዘመን፤ የአንድ ዓመት ፍጻሜም ሆነ ሽግግር በሙሉ ደማቅ ጨረቃ የሚሸኘውና አዲሱ የሚያብተው፣ በ 2028 ዓ ም ይሆናል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በነገው ዕለት (በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ) በመሃል አውሮፓ ሰዓት አቆጣጠር ፣ ከምሽቱ ለ 8 ሰዓት 8 ደቂቃ ጉዳይ ላይ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ ለ 4 ሰዓት 8 ደቂቃ ጉዳይ ላይ 8 ከመቶው የጨረቃ አካል በምድራችን ጥላ ሳቢያ ግርጃ ያጋጥመዋል።

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ