1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ «ሽሉክስፔስት» አዲስ የዓለም ክብረወሰን ፤

ሐሙስ፣ ነሐሴ 19 2003

ባለፈው ሳምንት ባቀረብነው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን፤ የአየር ንብረት ለውጥ በጀርመን ፤ ምን እንደሚመስል መዳሰሳችን ይታወስ ይሆናል።

https://p.dw.com/p/Rhvr
የ «ሽሉክስፔስት» የዓለም ክብረ ወሰን፣ምስል Hochschule Offenburg

በአቶም ኃይል ማመንጫ አውታሮች ላይ ሊደርስ በሚችል ድንገተኛ አደጋ ሳቢያ፤ ሊያጋጥም የሚችለውን ጠንቅ በማሰላሰል፤ የህዝቡንና የተቃውሞ ፓርቲዎችን ግፊትም ሆነ ውትወታ በማጤን፤ የወቅቱ የጀርመን ፌደራል መንግሥት፣ የአቶም ኃይል ማመንጫ አውታሮች ቀስ -በቀስ ከአነአካቴው እንዲዘጉና በአማራጭ፣ ታዳሽ የኃይል ምንጮች እንዲተኩ መወሰኑ የሚታወስ ነው።

ከዚህ ሌላ የተፈጥሮ አካባቢን ከሚበክሉት መካከል በቤንዚንና ናፋጣ የሚሽከረከሩ አውቶሞቢሎች እንደመሆናቸው መጠን፣ እነርሱንም በኤልክትሪክ ሞተርና ባትሪ በሚንቀሳቀሱ ኣ,ውቶሞቢሎች ለመተካት ዕቅድ አለ።በጀርመን ጎዳናዎች እ ጎ አ እስከ 2020 አንድ ሚሊዮን በኤሌክትሪክ ሞተርና ባትሪ የሚሠሩ አውቶሞቢሎች እንዲሽከረከሩ ለማድረግ መወሰኑን ባለፈው ግንቦት በርሊን ላይ ያስታወቁት ራሳቸው መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ናቸው። እናም መንግሥት፤ በኤሌክትሪክ ሞተር በሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ላይ ምርምር ማጠናከሪያ ገንዘብ በእጥፍ በመጨመር፣ እ ጎ አ እስከ 2013፣ በአጠቃላይ 2 ቢሊዮን ዩውሮ መመደቡ ታውቋል።

ጀኔብ፤

በፊዚክሱ ዓለም፣ እስካሁን እጅግ ዐቢይ እንቆቅልሽ መሆኑ የሚነገርለት፤ ለፍጥረተ ዓለም ሁሉ በተለይም ለቁስ አካል ዋና መነሻ ሳይሆን እንዳልቀረ የሚታመንበት Higgs-Boson ወይም የእግዚአብሔር ቅንጣት በመባል የሚታወቀው ኢምንት አካል፣ እስካሁን በተደረገው ምርምር ሊገኝ የሚችልበት ምልክት አለመታየቱን ዓለም አቀፍ የሳይንስ ተማራማሪ ጠበብት አስታወቁ።

እስዊትስዘርላንድና ፈረንሳይ ድንበር በሚገኘው ዐቢይ የአውሮፓውያን የኑክልየር ምርምር ማዕከል ፣ የፊዚክስ ሊቅ ሃዋርድ ጎርደን እንዳሉት ፤ ባለፈው ወር የተደረገው ሙከራ እምብዛም አመርቂ አልነበረም። ይሁንና የታሰበው ውጤት ለጊዜው ባይገኝም፤ የፊዚክስ ሊቃውንቱ፤ ተስፋ አልቆረጡም ፤ ግዙፉ መግነጢሳዊ የአቶም ቅንጣቶች ጨፍላቂው መሳሪያ (LHC)ም የተለያዩ አያሌ መረጃዎችን ለማግኘት አልበጀም አይባልም። ምርምሩ አሁንም በመቀጠል፤ በሚመጡት 12 ወራት ተጨማሪ ውጤት ለማስመዝገብ ሳያስችል እንደማይቀር ይታመናል። LHC በሚል ምኅጻር የሚታወቀው መሣሪያ፣ የቤት ያህል ስፋት ባላቸው አብያተ-ሙከራ «ፕሮቶንስ»ን ፤ ከሞላ ጎደል በብርሃን ፍጥነት በማሽቀንጠርና በመጨፍለቅ፤ የአቶም ክፍልፋዮችን ክምር፤ ተቆጣጣሪ መሳሪያዎች እንዲመዘግቡት ያስችላል። በተጠቀሰው ቤተ-ሙከራ፤ የአቶም ቅርንጣቶች በተጨፈለቁበት ድርጊት የተፈጠረው የሙቀት መጠን፣ ከፀሐይ 100 ሺ እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን ፣ ይህም፣ ፍጥረተ ዓለም(ዩኒቨርስ)፤ ከ ኃይለኛው ፍንዳታ በኋላ በሴኮንድ ክፋይ ሊዘረጋ የቻለበትን ሁኔታ የመድገም ያህል እንደነበረ ነው የተገለጠው። የፊዚክስ ሊቃውንቱ እንደሚሉት፤ ዩኒቨርስ የተዘረጋው፤ ከ 13,7 ቢሊዮን ዓመት በፊት ነው።

በ CERN የሚገኙ ተመራማሪዎች፤ Higgs-Boson እንዲሁ ውልብልቢት ከሆነ፤ እንደሚባለው «አዲስ ፊዚክስ» ለሚሰኘው ልዩ የምርምር ዘርፍ በር መክፈቱ የማይቀር ይሆናል።

ለንደን፤

አውስትሬሊያ ውስጥ ከ 3,4 ቢልዮን ዓመት በላይ ያስቆጠሩ የተኀዋስያን ኢምንት ቅሪተ-አካላት የተገኙ ሲሆን፤ እነዚህም፣ ምድራችን፣ «ኦክስጂን » አልባ በነበረችበት ዘመን ፣ በድንጋይ ውስጥም ሆነ በሚፈንፈቀፈቅ የድኝ ባህር ውስጥ ተኀዋስያን እንደነበሩ የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ፤ የምዕራብ አውስትሬሊያ ዩኒቨርስቲና የኦክስፈርድ ዩኒቨርስቲ ተማራማሪዎች አስታወቁ። በድንጋይም ሆነ ዐለት ውስጥ የተገኘው የተኀዋስያን ቅሪተ አካል ነው የተባለውን ግኝት፤ አንዳንድ ጠበብት፤ ፈንጣጣ ያጠቃው ፊት የሚመስሉ ዐለቶች ህይወት የነበረው ባክቴሪያ (ተኀዋሲ)የተዋኻዳቸው ሆነው ሳይሆን ፤ ዐለቱ ወደ ማዕድንነት መለወጡን የሚጠቁም ነው በማለት ይከራከራሉ።

ከ 3,4 ቢልዮን ዓመታት በፊት ህይወት ያለው ነገር ምልክት አግኝተናል የሚሉት ፣ እነዚሁ ተመራማሪዎች ደግሞ፣ በዘመናዊ መመርመሪያ መሳሪያ ካንዴም 3 ጊዜ፤ ግኝቱ ከሥነ ህይወት ጋር መያያዙን አረጋግጠናል ባዮች ናቸው። ተኀዋስያኑ፤ ለህልውናቸው የሚመኩት በድኝ ውሁድ ቅመማት ወይም ማዕድናት እንደነበረም ገልጸዋል። የተገኙት የተኀዋሲ መጠጊያ ዐለቶች መጠን ከሜትር አንድ ሚሊዮንኛ ነው። እርግጥ ቅርጹ ከባክቴሪያ ህዋሳት ቅርጽ ጋር የተዛመደ ሲሆን፤ የብረትና የድኝ ቅልቅል በሆነ ፣ አንዳንዴም የሞኝ ወርቅ ከሚሰኘው የዐለት ዓይነት ጋር ነው የተገኘው። ከምዕራባዊው አውስትሬሌያ፣ ዩኒቨርስቲ፤ ዴቪድ ዌሲ በተሰኙት ተመራማሪ የተመራው ቡድን፤ የምርምሩን ውጤት Nature Geoscience በተሰኘው መጽሔት እንዲታተም አድርጓል።በብሪታንያው የኦክስፈርድ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ማርቲን ብሬዚር ፣

«መጨረሻ፤ ከ 3,4 ቢሊዮን ዓመት በፊት ህይወት እንደነበረ፣ ጥሩና አስተማማኝ ፍንጭ አግኝተናል። በዚያ ዘመን ያለኦክስጂን መኖር የሚችል ተኀዋሲ ነበረ» ሲሉ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ድኝ የሚወዱ ባክተሪያዎች ዛሬም ድረስ መኖራቸው የታወቀ ነው። እነርሱም የሚገኙት የድኝ ሽታ በማይለያቸው አፈር ባለባቸው ዲቦች፣ በተፈጥሮ ፍል ውሃ በሚገኝባቸው ጣቢያዎች፤ እንዲሁም በተፈጥሮ ወይም በእሳተ ገሞራ ሳቢያ፤ የሚሞቅ የውሃ ክፍል በሚገኝባቸው ውቅያኖሶች ነው። ይህን መሰል ምልክቶች ደግሞ በማርስ ሊኖር እንደሚችል የማርቲን ብሬዚር ግምት ነው።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ