የፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ንግግር
ዓርብ፣ ጳጉሜን 2 2004
የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ሐገራቸዉን የገጠመዉ ምጣኔ ሐብታዊ ድቀትን ለማስወገድ ረጅም ጊዜ እንደሚጠይቅ አስታወቁ።ኦባማ የዲሞክራቲክ ፓርቲያቸዉን ወክለዉ ለድጋሚ ዘመነ-ሥልጣን እንደወዳደሩ የፓርቲዉ ጉባኤ ያሳለፈዉን ዉሳኔ መቀበላቸዉን ትናንት ሲያስታዉቁ እንዳሉት ለዘመናት የተጠራቀመዉ የሐገራቸዉ ችግር ባጭር ጊዜ አይወገድም።ያም ሆኖ ችግሩን ለማቃለል መስተዳድራቸዉ የወሰደዉ እርምጃ አበረታች ዉጤት ማሳያቱን አስታዉቀዋል።ኦባማ ዩናይትድ ስቴትስ በ1930ዎቹ ሥልጣን ላይ በነበሩት በፕሬዝዳት ሩዘቬሌት ዘመን ከታየዉ ኪሳራ ወዲሕ ለመጀመሪያ ጊዜ የገጠማትን ያሉትን ኪሳራ ለማስወገድ በመጀመሩት ጎዳና መቀጠሉ አስፈላጊ ነዉ።
«የቀየስኩትን መንገድ ፈጣንና ቀላል ለማስመሠል አልፈልግም። ይሕን አድርጌዉ አላዉቅምም። የመረጣችሁኝ ለመስማት የምትፈልጉትን እንድነግራችሁ አይደለም።እዉነቱን እንድነግራችሁ እንጂ።እዉነቱ ደግሞ ለብዙ አስርታት የተጠራቀሙትን ፈተናዎች ለማለፍ ከጥቂት አመታት በላይ ጊዜ ይጠይቃል።ኪሳራዉን ለማቃለል፥ አሁን ከገጠመን የከፋዉን ብቸኛ ድቀት ለማስወገድ ፕሬዝዳት ሩዘቬልት እንዳደረጉት አይነት የጋራ ጥረት፥ የጋራ ሐላፊነት፥ ጠንካራና ያልሠለሠ እርምጃ ያሻል።»
ኦባማ ለድጋሚ ዘመነ-ሥልጣን ከተመረጡ የሥራ አጡን ቁጥር፥ የ,መንግሥታቸዉንና ወጪና ግብር ለመቀነስ ቃል ገብተዋል።ፕሬዝዳት ኦባማ ትናንት ያደረጉት ንግግር ከአራት ዓመት በፊት እንዳደረጉት ያድማጭ ስሜትን የሚፈነቅል አይነት ግን አልነበረም።ኦባማ በመጪዉ ጥቅምት አጋማሽ ለሚደረገዉ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከሪፐብሊካኑ ተቀናቃኛቸዉ ከሚት ሮምኒ ጋር ይፎካከራሉ።
ነጋሽ መሐመድ
አበበ ፈለቀ
ሂሩት መለሰ
ተክሌ የኋላ