1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፓኬት ቦምቦችና የአውሮፓ ስጋት

ሰኞ፣ ጥቅምት 29 2003

በታሽጉ ፓኬቶች ውስጥ ተደብቀው የተጓጓዙ ቦንቦች ጉዳት ሳያደርሱ በፊት ከተደረሰባቸው ወዲህ በአውሮፓ ስጋቱ እያየለ መጥቷል። ሰኞ ጥቅምት 29 ቀን 2003 ዓ.ም. ብራስልስ ላይ የአውሮፓ የሀገር ውስጥ ሚንስትሮች ስጋቱን ተከትሎ ተወያይተዋል።

https://p.dw.com/p/Q1o2
የጀርመን የሀገር ውስጥ ሚንስትር ቶማስ ደ ሜዚየር
የጀርመን የሀገር ውስጥ ሚንስትር ቶማስ ደ ሜዚየርምስል dapd

ሰሞኑን አውሮፓ በታሽጉ ፓኬቶች ላይ የተጠመዱ ቦንቦች ስጋት ወጥሮ ይዟታል። በርካታ በፓኬቶች ውስጥ የተደበቁ ቦንቦች ጉዳት ከማድረሳቸው አስቀድሞ ከተደረሰባቸው በኋላ የአውሮፓ የሀገር ውስጥ ሚንስትሮች ሰኞ ብራስልስ ላይ ውይይት አድርገዋል። ውይይቱ በዋናነት የአየር ላይ ጭነት ማመላለሻ ወይንም የካርጎ ጭነቶች ቁጥጥር የሚጠብቅበት ሁኔታ ላይ የሚያተኩር ነው። የጀርመን የሀገር ውስጥ ሚንስትር ቶማስ ደ ሜዚየር ለዚሁ አስቸኳይ ስብሰባ ወደ ብራስልስ ቤልጂየም ከማቅናታቸው አስቀድሞ ስጋቱን በዚህ መልኩ ገልጸዋል።

« ከየመን ተጓጉዘው ከደረሱት ፓኬቶች ጋር በተያያዘ የካርጎ ማጓጓዣ አካባቢ ችግር እንዳለ አሁን አረጋግጠናል። በተለይ ጭነት ከመንገደኞች ጋር በሚጓጓዝበት ወቅት የተለየ የደህንነት ቁጥጥር ነው ያለን። ሀላፊነቱ እዚህም እዚያም የተበታተተነ ነው። አሁን ያን በአጠቃላይ ነቅሰን ማውጣት እንፈልጋለን።»

Brüssel Trauerzeremonie im Europaparlament für Absturzopfer
የአዉሮጳ ምክር ቤትምስል AP

የአየር ላይ ጭነት ማመላለሻ ወይንም የካርጎ መስክ ለአውሮፓ እንዲሁም ለጀርመን እጅግ ጠቃሚ የንግድ ዘርፍ ነው ሲሉ ሚንስትሩ ገልፀዋል። ከዚያም ባሻገር ወደ ጀርመን በርካታ እሽጎች ይጎርፋሉ፣ በዚያው መጠን ደግሞ ለየት ያለ አደጋ እያንዣበበ ነው ሲሉም አክለዋል። ይሄ ደግሞ ባለፉት ጊዜያት ተገቢው ትኩረት አልተደረገበትም፤ እናም አሁን በአንድ ጥሩ የካርጎ ማጓጓዣና በደህንነቱ መካከል ያለው ፍላጎት ላይ ልዩ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል። አሁን የነዚህ በፓኬቶች ውስጥ የታሽጉ ቦንች ስጋት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱንም በዚህ መልኩ አብራርተዋል።

«የተጋነነና ግልፅ ያልሆነ ማስጠንቀቂያ መስጠት አልፈልግም። ይሁንና ግን ለተዓማኒነቱ በአንድ ቃል ይህ ነው ብለን መናገር ባንችልም፤ በአውሮፓና በአሜሪካ የአሸባሪዎች ጥቃት ሊከሰት እንደሚችል የተለያዩ ምንጮች እየገለፁ ነው። ሆኖም በቸልታ የምናልፈው ነገር አይኖርም። የደህንነት ሰዎቻችን የህብረሰሰቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ሁሉንም ነገር በንቃት ነው የሚከታተሉት። ይህ ነው የተባለ አሳማኝ ዱካ ባይኖርም ባለፉት ወራት ግን እያየለ የመጣ ማስጠንቀቂያ ነው ያለው። ስለዚህም ይህን አሁን ይፋ ለማድረግ ጊዜው መሆኑ ይሰማኛል። ህብረተሰቡ በንቃት እንዲከታተልና አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት በቀጥታ ለፖሊስ እንዲያመለክት እጠይቃለሁ።»

የጀርመን የሀገር ውስጥ ሚንስትር በብራስልሱ ጉባኤ ላይ የአየር ላይ ማጓጓዣ ስርአት የበለጠ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግበት የሚጠይቅ ዕቅድ አቅርበዋል። ሚንስትሩ ያቀረቡት ዕቅድ ባለ አምስት ነጥብ ሲሆን፤ በገና ዋዜማ ውሳኔ እንደሚሰጥበትም ታውቋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ