1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፓኪስታን ጥምር መንግስት መፍረስ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 20 2000

የቀድሞ የፓኪስታን ፕሬዚደንት ፔርቬስ ሙሸራፍ ስልጣናቸውን ከለቀቁ ከአንድ ሳምንት በኋላ በአሲፍ አሊ ሳርዳሪ የፓኪስታን ህዝብ ፓርቲና የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ናዋስ ሸሪፍ የሙስሊም ሊጋ መካከል ተመስርቶ የነበረው ጥምር መንግስትም ፈርሶዋል።

https://p.dw.com/p/F5Fh
ናዋስ ሸሪፍ
ናዋስ ሸሪፍምስል AP

ከብዙበምህጻሩ ፒፒፒ ሳምንታት ንትርክ በኋላ ነበር አራት ፓርቲዎችን ያጠቃለለው የሙስሊም ሊጋ ኤን ፓርቲ ጥምሩን መንግስት ለቆ የወጣው።

በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል የመጀመሪያዎቹ ልዩነቶች የታዩት ጥምረቱ ባለፈው የካቲት ወር ከተመሰረተ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ስለነበረ፡ አሁን ጥምሩ መንግስት መፍረሱ ማንንም አላስገረመም። በጥምሩ መንግስት ብርቱ ግፊት ከጥቂት ጊዜ በፊት ስልጣናቸውን የለቀቁት የቀድሞው የፓኪስታን ፕሬዚደንት ፔርቬስ ሙሸራፍ ባለፈው ዓመት ከስራቸው ያባረሩዋቸው ስድሳ ዳኞች እንደገና ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ የናዋስ ሸሪፍ ፓርቲ በዋነኛነት ያቀረበው ጥያቄ ተጣማሪዎቹን ከመጀመሪያ ጀምሮ ያነታረከ ዋነኛው ጉዳይ ነበር፤ በፕሬዚደንት ፔርቬስ ሙሸራፍም ላይ ክስ ይመስረት የተባለውንም ጥያቄ ትልቁ ተጣማሪው የፓኪስታን ህዝብ ፓርቲ ፡ ጥምረቱ በተቋቋመበት ጊዜ የገባውን ቃል በማጠፍ፡ በፍጹም ሊቀበላቸው አለፈለገም። እነዚህ ልዩነቶች እስካልተወገዱ ድረስ አብሮ መስራቱ አዳጋች መሆኑን ነው ናዋስ ሸሪፍ ያስታወቁት።

« እነዚህ በተደጋጋሚ የታዩት ጉድለቶችና ጥሰቶች ለጥምሩ መንግስት የምንሰጠውን ድጋፍ እንድናቋርጥና የተቃዋሚውን መንበር እንድንይዝ አስገድዶናል። »

እንደሚታወሰው፡ ፒ ፒ ፒ በሙስሊም ሊጋ ኤን ውትወታ መሰረት ነበር ሙሸራፍ ያባረሩዋቸውን ዳኞች ጥምሩ መንግስቱ ከተመሰረተ ከሰላሳ ቀናት በኋላ ለመመለስ ተስማምቶ የነበረው። ግን ዳኞቹ እስካሁን ወደ ስራ ገበታቸው አልተመለሱም። ለዚህም ሁኔታ እንደ የሙስሊም ሊጋ ኤን አባባል ተጠያቂው የፒ ፒ ፒ ሊቀመንበር ሳርዳሪ ቃላቸውን ያጠፉበት ድርጊት ነው። ሆኖም ሳርዳሪ ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዳስረዱት፡ ይህ አባባል ሁኔታውን በትክክል አይገልጸውም።

« ቃሌን አለመጠበቄ አይደለም። በተወሰነ የፖለቲካ ሁኔታ ወቅት የተደረሰ ስምምነት ነበር። እና ስምምነቱን የያዘውን ሰነድ ከፈረምንና የፈረምነውንም ተገባራዊ ለማድረግ ከተነሳን በኋላ ግን በሀገሪቱ ሌሎች ሁኔታዎች ተፈጠሩ። »

በፓኪስታን ሁኔታውን የቀየረው ጉዳይ በግልጽ አይታወቅም። ይሁንና፡ ባልተቤታቸው የቀድሞዋ ጠቅላይ ሚንስትር ቤናዚር ቡቶ በሰው እጅ ከተገደሉ ከታህሳስ 2007ዓም ወዲህ ፒፒፒን የሚመሩት ሳርዳሪ ዳኞቹ ቢመለሱ በአንጻራቸው በሙስና ክስ እንዳይመሰርቱባቸው በመስጋታቸው ሳይሆን አልቀረም። እንደሚታወቀው ሁለቱን በአቋም የተለያዩትን ፓርቲዎች ያቀራረባቸው ብቸኟው ምክንያት በፕሬዚደንት ሙሸራፍ አንጻር የነበራቸው ተቃውሞ ነበር። እና ሙሸራፍ ሲወርዱም መሰረቱ ያልጸናው ጥምረታቸው መፍረሱ ለብዙዎች አዲስ አልሆነም። የሙስሊም ሊጋ ኤን ፓርቲ ጥምሩን መንግስት ለቆ እንደሚወጣ የጠበቀው ፒፒፒ አሁን ከሌሎች ንዑሳን ፓርቲዎች ጋር ባንድነት በመሆን በፓኪስታን ስልጣኑን እንደያዘ ይቆያል። በቅርቡ በሀገሪቱ ከሚደረገው ፕሬዚደንታዊ ምርጫም በኋላ ስልጣኑን እንደሚያስፋፋ ነው የሚገመተው። ምክንያቱም፡ ፒፒፒ ሳርዳሪን በዕጩነት አቅርቦዋል። በአንጻሩ የሙስሊም ሊጋ ኤን ለዚሁ ከፍተኛ ስልጣን አንድ ነጻ ዕጩ ሰይሞዋል። ይህም ቢሆን ግን ሳርዳሪ ናዋስ ሸሪፍ ወደ ጥምሩ መንግስት እንዲመለሱ ተማጽኖ አሰምተዋል። የፓኪስታን መንግስት የሚከተለው መስመር በግልጽ ባልታወቀበት ባሁኑ ጊዜ የተቃውሞውን መንበር የያዙት ናዋስ ሸሪፍ በቀላሉ የማይገመት ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉና ከፓኪስታን ህዝብም ዘንድ ተጨማሪ ድጋፍ ሊያገኙ እንደሚችሉ ተገምቶዋል።