1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፓርቲዎች ዉህደት እና እዉቅና

ሐሙስ፣ የካቲት 21 2005

የኦሮሞ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄና የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስ ተዋሕደው የመሰረቱት ፓርቲ ህጋዊ እውቅና ማግኘቱ ተገለጸ። አሁን የኦሮሞ ፌደላዊ ኮንግረስ የሚል ስያሜ ያገኘው የሁለቱ ፓርቲዎች ውህደት ከኦሮሞ ህዝብ ጥያቄና የጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ መሆኑ ተነግሯል።

https://p.dw.com/p/17oLg
ምስል derejeb/Fotolia
Bulcha Demeksa vom Oppositionsbündnis Medrek
የቀድሞዉ የኦፌዴን ሊቀመንበር ቡልቻ ደመቅሳምስል DW

ባለፈው ሐምሌ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ በሚል ስያሜ የተዋሃዱት የኦሮሞ ፌደራላዊ ዲሞክራሳያዊ ንቅናቄ (ኦፌደን) እና የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስ (ኦህኮ)በየካቲት አንድ ህጋዊ እውቅና ማግኘታቸውን የውህደቱ መሪ ዶክተር መረራ ጉዲና አስታወቁ። ፓርቲው የተዋሄደው በኦሮሞ ህዝብ በተለይም በከፍተኛ የትምህርት ተቋም ተማሪዎች ተደጋጋሚ ጥያቄ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። ገንዘብ፣ አባላትንና የፓርቲዎቹን አመራር ማሰባሰብ ሌላው ምክንያት ነው ይላሉ ዶክተር መረራ፤
የኦሮሞ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄና የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ያሰባሰበውን መድረክን ከመሠረቱት ፓርቲዎች ይመደባሉ። የኦሮሞ ህዝብ ፌደራላዊ ኮንግረስ በኦሮሚያ ክልል ብቻ ሳይሆን በሁሉም ኢትዮጵያ እንደሚንቀሳቀስ የተናገሩት ዶከተር መረራ፤ ፓርቲያቸው
በኢትዮጵያ ሁሉንም ህዝቦች ያጠቃለለ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲፈጠር ይሰራል፤
የኢህአደግ እህት ፓርቲ የሆነውና የኦሮሚያ ክልልን እያስተዳደረ ያለው የኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ኦህደድ በኦሮሚያ መልካም አስተዳደር እንዲፈጠር አልሰራም የሚሉት ዶከተር መረራ፣ ፓርቲያቸው በኦሮሚያም ሆነ በኢትዮጵያ ከቀበሌ እስከ ከፍተኛ የመንግስት እርከኖች ህዝቡ የራሱን መሪ የመሾምና የመሻር ስልጣን እንዲኖረው ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ በሚካሄደው የአከባቢ ምርጫ ውስጥ የኦሮሞ ፌደራላዎ ኮንግረስ ስለመሳተፉ ግልጽ ውሳኔ ላይ አልደረሰም። መንግስት የፖሊቲካ ፓርቲዎች ተሰሚነት እንዳያገኙ ካደረገ ፓርቲያቸው በምርጫው እንደማይሳተፍ የተናገሩት ዶከተራ መረራ ፤መንግስት የሚያስልጉትን ቅድመ ሁኔታዎች ካሟላ ግን በምርጫው ይሰታፋሉ፤
ከአምስት ዓመታት በፊት ኦፌደን እና ኦህኮ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር መድረክን ካቋቋሙበት ጊዜ ጀምሮ በመድረክ የሚገኙ ፓርቲዎች የፕሮግራም አንድነት ስለሌላቸው አብሮ መስራት አይችሉም የሚሉ ወገኖች ነበሩ። የመድረክ አባል ፓርቲዎች በአብዛኞቹ የሀገሪቷ የፖሊቲካ ጥያቄዎች ላይ የጋራ አቋም ቢኖራቸውም መሬትና የፌደራሊዝም አወቃቀር በመሳሰሉ ጥያቄዎች ላይ አሁንም ከስምምነት ባለመድረሳቸው ምክንያት የመድረክን የፖሊቲካ ዓላማ ዘላቂነት ይጠይቃሉ።

ገመቹ በቀለ

አርያም ተክሌ