1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

----

ዓርብ፣ ጥር 1 2007

ፓሪስ ፈረንሳይ ውስጥ፤ ሻርሊ ኤብዶ በተሰኘው በአሥቂኝ ስእሎች የታጀበ የምጸትና ሥላቅ መጽሔት ዝግጅት ባልደረቦችና በሁለት ፖሊሶች ላይ የተፈጸመው ግድያ ፣ ምዕራቡን ዓለም ብቻ ሳይሆን የአፍሪቃውን ክፍለ ዓለምም ማሳዘኑ ተነግሯል። የፓሪሱ

https://p.dw.com/p/1EI9p
ምስል AFP/Getty Images/S. Diallo

የአሸባሪዎች ጥቃት በአፍሪቃ ስላሳደረው ስሜት ፣ የተሰናዳው ዝግጅት ቀጥሎ ይቀርባል።ፓሪስ ውስጥ በተፈጸመው አሸባሪ ርምጃ ሳቢያ ፤ ጥልቅ ሐዘናቸውን ከገለጹት መካከል በዛ ያሉ አፍሪቃውያን ጋዜጠኞች ይገኑበታል። በተለይ ፈረንሳይኛ በሚነገርባቸው የአፍሪቃ ሃገራት የሚሠሩት ጋዜጠኞች ፣ ብዙዎቹ ፈረንሳይ ሀገር የተማሩና የሠሩ በመሆናቸው ፣ ግንኙነታቸው የጠበቀ ነው። ለምሳሌ ያህል በቡርኪና ፋሶ መዲና ዋጋዱጉ እየታተመ የሚቀርበው Journal du Jeudi የኀሙስ ጋዜጣ የተሰኘው ምጸትና ሥላቅ አዘል ጋዜጣ አዘውትሮ ከሻርሊ ኤብዶ ጋር ተባብሮ ይሠራ እንደነበረ ተገልጿል። ጋዜጠኛ ኮፊ አሜቴፔ፣ «ጋዜጠኞች፤ የአንድ መጽሔት አዘጋጂዎች የሽብር ዒላማዎች መሆናቸው በጣም አሳዝኖኛል» ብሏል። ጋዜጠኛ ኮፊ አሜቴፔ፤ ሃይማኖትን በተመለከተ የቡርኪና ፋሶ ሰዎች ወግ አጥባቂዎች ናቸው። የቡርኪና ፋሶ ዜጎች አብዛኞቹ ሙስሊሞች ናቸው፤ በአፍሪቃ ባህል እንደ እርም የሚታዩ አንዳንድ ጉዳዮች አሉ ፣ ሃይማኖት ነክ ጉዳይ አንዱ ነው፤ ስለሆነም ስናቀርብ ጥንቃቄ እናደርጋለን። ሕዝቡ ማየት የማይፈልገውን እንዲያይ አናደርግም» ነው ያለው።

የ DW የኪስዋሂሊ ዝግጅት በተለይም የ«ፌስቡክ» ተጠቃሚዎች በምዕራባውያን እሴቶች ላይ ጥቃት መሰንዘሩ ብቻ አይደለም በሰፊው የዝግጅቱ ተሳታፊዎች ያደረጋቸው። ኤሊሻ ማዞያ፣ የተባለችው ተሳታፊ፣ 2 አበሳ የሌለባቸው ሰዎች መገደላቸው አንዳች ይቅርታ የማይደረግለት ወንጀል ነው ፤ የጸጥታ ኃይሎች፤ ነፍሰ ገዳዮቹን አድነው በመያዝ ለፍርድ ማቅረብ ይኖርባቸዋል ማለቷ ተጠቅሷል።

Titelseiten zum Anschlag auf Charlie Hebdo in Dakar, Senegal
ምስል AFP/Getty Images/S. Diallo

በሰሜን ምሥራቅ ናይጀሪያ በሸሪያ የሚተዳደር ግዛት ለመመሥረት አልሞ የተነሣው፣ ቦኮ ሃራም የተባለው አካራሪ ድርጅት መላይቱን ናይጀሪያ እንዳሳሰበ ፤ እንዳስጨነቀ ቢገኝም፤ ከመዲናይቱ ከአቡጃ፤ Peoples‘ Daily የተሰኘው ጋዜጣ ባልደረባ ፤ ጋዜጠኛ ሙሐመድ ኢብራሂም በፓሪስ የጋዜጠኞች መገደል እጅግ እንዳስደነገጠው ተናግሯል። እንዲህ ሲል---

« እርግጥ ነው ክው ብዬ ደንግጬአለሁ ፤ ባልደረቦቼ ናቸውና የተገደሉት። እንደ ሰብአዊ ፍጡር ማዘን ይኖርብሃል። አንዳንድ ጊዜ፤ ምንድን ነው እዚህ ርምጃ ላይ ያደረሰ? ለግድያው ምንeን ነው ሰበቡ ብሎ መመርመር መልካም ነው።»

በአያሌ ሃገራት ጋዜጠኞችን የማይወዱ ወገኖች ጥቂቶች አይደሉም። ጋዜጠኛም ፤ ምን እንደሚጽፍና እንደማይጽፍ ፣ ሁኔታዎችን ጠንቅቆ ማወቅ ይኖርበታል ብሏል። የናይጀሪያ መንፈሳዊ ሰዎች ፣ ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች፣ ጋዜጠኞች ሃይማኖትን በአክብሮት መመልከት ይኖርባቸዋል ብለዋል። በካዱና አንድ ወንጌላዊ የሚባሉ የሃይናኖት ሰው ፤ በፓሪስ በአሸባሪዎች የተገደሉት ሰዎች በእግዚአብሔር የማይቀልዱ ቢሆን ኖሮ እርሱ ራሱ ከክፉ ነገር ይሠውራቸው ነበረ ማለታቸው ነው የተጠቀሰው። ያም ሆኖ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ መበቀል የኔ ሥልጣን ነው ይላልና ሰው በሰው መበቀል የለበትም የሚል መልእክት አሰምተዋል።

በዚያው በናይጀሪያ እስላማዊ ሕግጋትን የሚመለከተው ብሔራዊ ም/ቤት የፕረስ ጉዳይ ተጠሪ አብዱላሂ ባየሮ በበኩሉ ይህን ነበረ ያለው።

«ያለው ችግር ፤ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሲባል ያለን የተሣሣተ ችግር ነው። ሰው ምን የፈለገውን ፤ የወደደውን ለመናገር ይነሣል? መቼ ፤ ምን ብሎ ይናገራል?

ግምት ውስጥ ማስገባት የራስን ሐሳብ ማንጸባራቂያውን ጊዜና ቦታ ነው። ምን ያስከትላል ብሎ ማሳላሰል ይበጃል። የምናገረው ቃል ዓለምን በሙሉ ጦርነት ውስጥ የሚከት ነው ወይስ በሰላም አብረን እንድንኖር የሚያደርግ ነው?»

ሲያጠቃልልም፣ ጥንቃቄና መከባበር እንደሚያስፈልግ አስገንዝቦ፤ መግደል ግን የአስልምና ትምህርት አይደለም ብሏል።

ተክሌ የኋላ/ካትሪን ማታይ

ኂሩት መለሰ