1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፓሪሱ ስምምነት እና የዓለም ምላሽ

እሑድ፣ ታኅሣሥ 3 2008

የዓለም የሙቀት መጠን ጭማሪን ከ2.0 ዲግሪ ሴልሽየስ ወይም 3.6 ፋራናይት በታች ለማቆየት ትናንት የተፈረመው የፓሪስ ስምምነት ሙገሳ እየተቸረው ነው። የጀርመኗ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ስምምነቱን እንደ ተስፋ ምልክት ቆጥረውታል።

https://p.dw.com/p/1HMim
Frankreich Cop21 Klimagipfel in Paris Klimaabkommen beschlossen
ምስል Reuters/S. Mahe

መራሒተ-መንግስቷ ስምምነቱ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት ቁርጠኝነቱን ያሳየበት እንደሆነ ተናግረዋል። ስምምነቱን 'ታሪካዊ' ያሉት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ደግሞ በ195 አገራት የተፈረመው 'የፓሪስ ስምምነት' ምድርን በአየር ንብረት ለውጥ ከሚፈጠር ውድመት ለመታደግ የተሻለው አማራጭ መሆኑን ተናግረዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ባን ኪ ሙን በበኩላቸው ይህ ስምምነት ባይፈረም ኖሮ ሁለተኛ አማራጭ እንዳልነበር ጠቁመው ከዓለም ቁልፍ ችግሮች አንዱን ለመፍታት የተፈጠረውን ትብብር አድንቀዋል። የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርሲያን ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በበኩላቸው ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ያልተቆጠበ ቁርጠኝነት እና የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ አሳስበዋል። ስምምነቱ ድሆችን ሊረዳ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ትናንት የፀደቀው ስምምነቱ ከኪዮቶው በተለየ ሁሉንም የዓለም አገሮች ያካተተ ሲሆን በቀዳሚነት የዓለም የሙቀት መጠንን ከኢንዱስትሪው አብዮት በፊት ወደ ነበረበት ለመመለስ አቅዷል። ስምምነቱ ግን በህግ አስገዳጅ አይደለም። በእቅዱ መሠረት በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሀገራት ለደሀ አገሮች ከ 2020 እስከ 2025 ድረስ በየዓመቱ 100 ቢሊዮን ዶላር መስጠት ይኖርባቸዋል። አገሮች የበካይ ጋዝ ልቀት መጠናቸውን ለመቀነስ የማቀድ፤የመተግበር እና ውጤቱንም ይፋ የማድረግ ኃላፊነት የተጣለባቸው ሲሆን ከጎርጎሮሳዊው 2023 ዓ.ም. ጀምሮ በየ አምስት አመቱ የሚመዘን ይሆናል። በፓሪስ ስምምነት መሠረት በጎርጎሮሳዊው ከ2050 እስከ 2100 ባሉት ዓመታት ከካርቦንዳይ ኦክሳይድ ነጻ የሆነ ዓለም ተስፋ ተደርጓል።

Frankreich Cop21 Klimagipfel in Paris Klimaabkommen beschlossen
ምስል Getty Images/AFP/F. Guillot

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ