1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፎክላናድ (ማልቪናስ) ደሴቶች ዉዝግብ

ሰኞ፣ የካቲት 22 2002

ጀምበሯ-ደማቋ ጀምበር ጥልቅ።የብሪታንዉ አምስተኛ እግረኛ ጦር ብርጌድ አባላት ከመርከባቸዉ-ዉልቅ፣ከደሴቲቱ ግብት።ግንቦትም ሰላሳኛ ቀኑን አገባደደ።

https://p.dw.com/p/MG6t
ከደሴቶቹ-መሐልምስል picture-alliance/ dpa

01 03 10

በ1982 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የብሪታንያ-ጦር የአርጀንቲና ጠላቱን ድል ሲያደርግ-ዘመናት ያስቆጠረዉ ዉዝግብ የድርድር ፍፃሜ ያገኛል-አሰኝቶ ነበር።ጥያቄዉ ሲነሳ-በቅኝ ገዢ-ተገዢዎች የበላይ በታችነት ግፍ-እየተመረገ፣ቂሙ ሲያመረቅዝ፣ በጦር-ሐብት ጡንቻ እየተጆበነ ከያኔዉ ጦርነት ያደረሰዉ አሮጌ ዉዝግብ፥ ሃያ ስምንት አመት ያጀለዉን የድርድር ተስፋ በርቅሶ ብቅ አለ።አሁን።የፎክላንድ ወይም የማልቪናስ ደሴቶች።ለዘመነ-ዘመናት እንደሚታወቁበት የለንደን-ቦኒስ አይሪሶችን ሽኩቻ፥የቃላት እንኪያ ሰላንቲያ አንረዉ፣ ጦር ያስቃኙ ገቡ-ሰሞኑን።ከንግሕዲስ? የእስካሁን ዳራ፣ ያሁኑን እዉነት፣ እያነሳን-የወደፊቱን-ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
----------------------------------------------------------------------------------

ጀምበሯ-ደማቋ ጀምበር ጥልቅ።የብሪታንዉ አምስተኛ እግረኛ ጦር ብርጌድ አባላት ከመርከባቸዉ-ዉልቅ፣ከደሴቲቱ ግብት።ግንቦትም ሰላሳኛ ቀኑን አገባደደ።ሜጀር-ጄኔራል ጆን ጄርሚ ሙር ጊዜ አላጠፉም።ብዙ በተጠና ሥልታቸዉ መሠረት ያሰለፉትን-ጦር «ቀጥል» አይነት አሉ።ጠንካራዉ ጦር-ከሚያዚያ መጀመሪያ ጀምሮ ደሴቶቹን የሚቆጣጠረዉን የአርጀቲና ጠላቱን ይወቃዉ ገባ።1982።
-------------
የቺሊዉ ጄኔራል አጉስቶ ፒኖሼ-በ1973 ሕዝብ ጨፍጭፈዉ በሕዝብ የተመረጠዉን የሳልቫንዶር አያንዴን ኮሚንስታዊ መንግሥት ማስወገዳቸዉ፣ ጄኔራሉ ያደረጉትን እንዲያደርጉ ዙሪያ መለስ ድጋፍ ለሰጧቸዉ ለዩናይትድ ስቴትስና ለተባባሪዎችዋ ትልቅ-ድል፣ለሶቬት ሕብረትና ለተቀጥላዎችዋ ደግሞ አሳዛኝ ሽንፈት ነበር።የቼሌዉ ድል-ሽንፈት በደቡባዊ አሜሪካ የካፒታሊስት-ኮሚንስቶችን የሐይል አሰላለፍ መቀየር-አለመቀየሩ በቅጡ ሳያረጋገጥ ዮርግ ራፋኤል ኤዶንድ-የመሯቸዉ የአርጀንቲና ግራ-ዘመም የጦር መኮንኖች የሐገሪቱን ሲቢላዊ አስተዳደር በሐይል አስወግደዉ ሥልጣን ያዙ።1976።

ዩናይትድ ስቴትስ ፒኖሽን አይነት አርጀንቲናዊ ለማግኘት ስትባትል ሶቬት ሕብረት ባንፃሩ-እነ ጄኔራል ኤዶንዶ-ካስትሮን እንዲሆኑ ታባብል ገባች።አዲሶቹ የአርጀንቲና ገዢዎች ከሕዝብ የሚነሳባቸዉን ተቃዉሞ አቅጣጫ ለማስቀየር አርጀንቲናዊዉ እንደ ሐገሩ ግማደ ግዛት የሚከራከርላቸዉን ደሴቶች የምትቆጣጠረዉ ብሪታንያ እንድትመልስላቸዉ ይጠይቁ ያዙ።

መልስ ግን አልነበረም።ተደጋጋሚዉ ጥያቄ ወደ ጦር ፍጥጫ ቢንርም-የአለም ዘዋሪዎች አጋጣሚዉን ለየጥቅማቸዉ የሚያዉሉበትን ሥልት ከማሰላሰል ባለፍ-ፍትሕን ለማስፈን፣ ደም መፋሰስን ለማስቀረት፥ በአርጀንቲና ሕዝብ ላይ የሚፈፀመዉን ግፍ ለማስቆም የሞከረ አልነበረም።

ያሁንዋ የአርጀንቲና ፕሬዝዳንት ክሪስቲና ፌርናንዴዝ ደ ኪርሺነር-የቀድሞ የሐገራቸዉን ወታደራዊ ገዢዎች-ምናልባት ከማርጋሬት ታቸር፣ ከሮናልድ ሬጋን እኩል መኮነናቸዉ አይቀርም።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ገለልተኛነት ግን ይጠይቃሉ። የሐያላኑን ሸፍጥም ያወግዛሉ።
«የማልቪናስ ጉዳይ በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ላላቸዉ ሐገራት አለም አቀፍ ሕግን እንዴት ማድረግ እንደሚችሉ ግልፅ ምሳሌ ነዉ።ይሕ ሌሎች ሐገራት እንዲያከብሩት ለሚገደዱበት፥ ካለከበሩት እንደጠላት ምናልባትም ከዚያሕ በባሳ ሁኔታ ለሚወገዙበት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደንብን ሲበዛ የሚያረክስ ነዉ።»

Großbritannien Falkland Krieg Flagge in Axax Bay Jahrestag
የደሴቶቹ-ገዢ ባንዲራምስል AP

በራቀዉ ዘመን ከመርከበኞች፥ ካሳ አጥማጆች፥ ካገር አሳሾች ማረፊያ-መሸጋጋሪነት ባለፍ የሚፈልግ፣ የሚያዉቃቸዉም አልነበረም።የተለያዩ ሐገራት ሐገር አሳሾች የተለያየ ሥም እየሰጡ እንደነገሩ ካርታ ላይ አስፍረዋቸዋል።ቱርካዊዉ የባሕር ሐይል መኮንና የመልከዓ ምድር አዋቂ ሐጂ ሙሕዲን ፒሪ ኢብን ሐጂ መሐመድ በ16ኛዉ መቶ ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ በሠራዉ ካርታ በግልፅ እስከሚያመለክታቸዉ ድረስ ግን በትክክል ያወቃቸዉ፥ ብዙ ትኩረም የሰጣቸዉም አልነበረም።

በ1690 ወደ አርጀንቲና በመቅዘፍ ላይ የነበረዉ ብሪታንያዊ ካፒቴን ጆን ስትሮግ መርከቡን ንፋስ ያላጋትና እኒያ ደሴቶች ጥግ-ይወሽቀዋል።በሁለቱ ትላልቅ ደሴቶች መሐል የቀዘፈበትን የዉሐ መስመር-ባዝማቹ ስም ሰየመዉ።የፎክላንድ ወሽመጥ ብሎ።የመጀመሪያዎቹ ሰፋሪዎች እንደሆኑ የሚገመቱት ፈረንሳዉያን ግን በ1764 ከደሴቶቹ ሲደርሱ የዛሬዉን-የስጳኝኛ ስም ሰጧቸዉ።ላስ ኢዝላስ ማልቪናስ።

እና አሳ-ማስገሪያ፥ ማለፊያ፥ ማረፊያዎቹ ደሴቶች ለወንጀለኞች ማገዢያነት፥ ለጦር ማስፈሪያነት የሚፈልጓቸዉ የፈረንሳይ፣ የስጳኝ እና የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች ይሻኮቱባቸዉ ጀመሩ።ዛሬ ባለሙያዎች እንደሚገምቱት እነዚያ ደሴቶች ስልሳ ቢሊዮን በርሚል ነዳጅ ዘይት ተነጥፎባቸዋል።ሌላ የዉዝግብ-ምክንያት።ነዳጁን ለመዛቅ ቁፋሮ የጀመረዉ የብሪታንያ ኩባንያ የበላይ ቦብ ሊዮንስ-ያን ምድር አንለቅም ይላሉ።

«እዚሕ የመጣነዉ ለመቆፈር ነዉ።እዚሕ ሥለሚደረገዉ ነገር የአርጀቲና አመለካከት ምን እንደሆነ ምንጊዜም እናዉቀዋለን።ያቀድነዉም በዚሕ መሠረት ነዉ።እራሳችንን የቻልን ነን።ለሚሆነዉ ነገር ሁሉ የጎረቤት ሐገራትን ድጋፍ ለሚጠይቀዉ ለማናቸዉም ነገር አፀፋ ለመስጠት ሙሉ በሙሉ ተዘጋጅተናል።ሥራችንን የምናከናዉነዉ በዚሕ መሠረት ነዉ።»

ለፕሬዝዳት ኪሽነር-ግን የብሪታንያዉ ኩባንያ እቅድ-እርምጃ ሉአላዊነትን መጋፋት ብቻ አይደለም። ዘረፋ-ጭምር እንጂ።

«በባሕር ዳርቻዉ ላይ የሚደረገዉ ግንባታ ሉአላዊነታችንን የሚጋፋ ብቻ አይደለም።የተፈጥሮ ሐብታችንም ጭምር እየተመዘበረ ነዉ።ዘረፋ ነዉ።

ጥንት፣-ደሴቶቹን ከፈረንሳይ ተረክባ ከአርጀቲና ግዛቷ ጋር ያዋሐደችዉ ስጳኝና አስረካቢዋ ፈረንሳይ ባንድ አብረዉ ከብሪታንያ ጋር ሊዋጉ-ተፋጠዉ ነበር።1770።አል-ተዋጉም።ፈረንሳይ ወደ ኋላ ሸርተት ብላ ስጳኝ ብቻዋን መዋጋት ፈርታ-ፍጥጫዉ ረገበ።በ1831 የዩናይትድ ስቴትስ ባሕር ሐይል-ፖርት ሊዊስ ላይ የነበረዉን የአርጀቲና የሠፈራ መንደር-ደመሰሰ።ድሮ፣1982 -ዘመናት ያስቆጠረዉ ዉዝግብ እንዲሕ እንደዛሬዉ የብሪታንያና የአርጀንቲናን የቃላት-ዲፕሎማሲን ሽኩቻ ሲያግም አሉ-ከሚስብል-ማለት ባለፍ ሁለቱን ወገኖች ለመሸምገል ከልቡ የሞከረ አልነበረም።

ሚያዚያ ሁለት። ጄኔራል ማርዮ ቢንያሚን ሜኔንሴ-የሚያዙት ጦር አወዛጋቢዎቹን ደሴቶች ተቆጣጠረ።የግዙፎቹ ሐገራት ግዝፍ መገናኛ ዘዴዎች «የአርጀንቲና ወታደራዊ አምባገነኖች-የፎክላንድ ደሴቶችን ወረሩን» ያስተጋቡ ገቡ።የአርጀንቲና ገዢዎችና ደጋፊዎቻቸዉ-ባንፃሩ «የማልቪናስ ደሴቶቻችንን መለሰን እያሉ አራገቡት።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ነቃ።ቁጥር አምስት መቶ ሁለት ባለዉ ዉሳኔዉ-አርጀቲና ባስቸኳይ ጦርዋን አስወጥታ ከብሪታንያ ጋር እንድትደራደር አሳሰበ።

ማሰሰቢያዉ ከኒዮርክ ሲሰማ ጄኔራል ጆን ጄርሚ ሙር የሚያዙት የብሪታንያ ጦር ወደ ደሴቶቹ እየቀዘፈ ነበር።ግንቦት ሰላሳ ደረሰ።የሆነዉም-ወዲያዉ ሆነ።ከቺሌና ከኮሎምቢያ በስተቀር መላዉን ደቡብ አሜሪካ ከአርጀቲና ጎን፥ከስጳኝ በስተቀር ድፍን ምዕራብ አዉሮጳን፥ ዩናይትድ ስቴትስስ፥ ካናዳና አዉስትሬሊያን ከብሪታንያ ጎን ያቆመዉ ጦርነት አበቃ።በሁለት ሳምንት እድሜ የአርጀቲና ጦር ተፈታ።ጄኔራል ማሪዮ ቤንያሚን ሜኔንዴስ መሸነፋቸዉን በፊርማቸዉ አረጋገጡ።ሰኔ-14።

Falklandinselfuchs
የደሴቶቹ ቀበሮ

የብሪታንያ ድል-የአርጀቲና ጄኔራሎችን ከስልጣን አስወግዶ-በላቲን አሜሪካዊቷ ሁለተኛ ትልቅ ሐገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመትከል ምክንያትም ነበር።የአዲሱ ሥርዓት መመስረት እንደ ዲሞክራሲዉ ወግ-የደሴቶቹን ዉዝግብ በድርድር ለማስወገድ መሠረት ነዉ ተብሎም-ተስፋም ተሰጥቶ ነበር።
----------------

ዛሬ-የካፒታሊስ ኮሚንስቶች ሽኮቻ በርግጥ የለም።የአርጀንቲና ወታደራዊ ገዢዎችም አንድም ሞተዋል-አለያም አርጀተናዋል።የብሪታንያ ድል በተረጋገጠ ማግሥት «ብረቷ እመቤት» የሚል የቁልምጫ ቅፅል የተሰጣቸዉ የያኔዋ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ማርጋሬት ታቸርም አርጅተዋል።ፍጥጫዉ ግን በርግጥ ንሯል።አብዛኞቹ የደቡብ አሜሪካ ሐገራት ሜኪስኮ ላይ ባደረጉት ጉባኤ እንደረጋገጡት ከአርጀቲና ጎን ተሰልፈዋል።የያኔዎቹ-ብሪታንያ ወዳጆችም ዛሬም ካቋማቸዉ ፈቅ አላሉም።ዛሬ-ትናንት-ነገም ዛሬ።ፎክላንድ-ማልቪናስ።ነጋሽ መሐመድ አዲዮስ።

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ