የፍልሥጤማውያን በተመድ የታዛቢነት ዕውቅና ማግኘት
ዓርብ፣ ኅዳር 21 2005ማስታወቂያ
ሥርዓት ከ 193 የተመድ አባል ሀገራት መካከል 138 የፍልሥጤማውያን ፕሬዚደንት ማህሙድ አባስ ያቀረቡትን ማመልከቻ ሲደግፉ ዘጠኝ ተቃውመውታል፤ 41 ደግሞ ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል። ድምጽ ከመስጠት ከተቆጠቡት መካከል ጀርመን አንዷ ስትሆን፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ ከደገፉት ሀገራት መካከል ናቸው። ፍልሥጤማውያን አሁን በተመድ የያዙት የታዛቢነት አቋማቸው በድርጅቱ ውስጥ ይዘውት የነበረውን ብቸኛውን የመናገር መብት በማሻሻል ወደፊት በድርጅቱ በሚካሄዱ ክርክሮች በጠቅላላ እንዲሳተፉ፡ እንዲሁም፡ በተለያዩት የተመድ አካላት ውስጥ በአባልነት እንዲገቡ ያስችላቸዋል። እስከትናንቱ ውሳኔ ድረስ በተመድ ውስጥ የታዛቢነት አቋም የያዘችው የድርጅቱ አባል ያልሆነችው ቫቲካን ብቻ ነበረች። በራማላህ እና በጋዛ ሲቲ በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ የ,ተካሄደውን የድምፅ አሰጣጡን በትላልቅ ቴሌቪዥኖች የተከታተለው የፍልሥጤም ሕዝብ በውሳኔው መደሰቱን ገልጾዋል። በመላው ዓለም የሚገኙት ፍልሥጤማውያን ውሳኔውን ትልቅ ትርጓሜ የያዘና ሀገር ወደመሆን ደረጃ የሚያሸጋግር የመጀመሪያው ርምጃ አድርገው ተመልክተውታል። ዩኤስ አሜሪካ እና እሥራኤል የትናንቱን ውሳኔ በፍልሥጤማውያን እና በእእሥራኤል መካከል ዘላቂ ሰላም የማያመጣ ነው በሚል ተቃውመውታል።