1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኬንያ በፈንዱ ብዙ ወጣቶችን አልጠቀመችም

ዓርብ፣ የካቲት 3 2009

ኢትዮጵያ- 10 ቢሊዮን ብር፡፡ ኬንያ - 12 በሊዮን ሽልንግ፡፡ ደቡብ አፍሪካ - ሶስት ቢሊዮን ራንድ ገደማ፡፡ ሶስቱም ሀገራት በሀገራቸው መገበያያ መጠኑ ገዘፍ ያለ ገንዘብ የመደቡት የወጣቶች የስራ አጥነት ችግር “እንቅልፍ ነስቶናል” ብለው ነው፡፡ 

https://p.dw.com/p/2XMTG
Äthiopien Addis Abeba Autowerkstatt Binyam Tesfaye
ምስል Hilina Abebe

የጸደቀው የወጣቶች ፈንድ ተግዳሮቶች

ተነሳሽነቱን በመውሰድ ኬንያ ትቀድማለች፡፡ የምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ለወጣቶች ብቻ የተመደበ ፈንድ አዘጋጅታ እርሱን የሚያስተዳድር ተቋም የመሰረተችው የዛሬ 10 ዓመት ግድም ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ ከሁለት ዓመት በፊት ኬንያን ተከትላታለች፡፡ የወጣቶችን ጉዳይ የሚከታተለው መንግስታዊ ተቋሟ ኢንዱስትሪዎችን እና አነስተኛ ድርጅቶችን ለመደገፍ ከተመሰረቱ አቻ መስሪያ ቤቶች ጋር ጥምረት ፈጥሮ ፈንዱን እውን አድርጎታል፡፡ 

የኢትዮጵያ ገና ትኩስ ነው፡፡ ስለ ፈንዱ መጀመሪያ የተሰማው ከፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ አንደበት ነበር፡፡ ፕሬዝዳንቱ የተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶችን ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ በይፋ ሲከፍቱ ባሰሙት ንግግር መንግስት የወጣቶች የስራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ 10 ቢሊዮን ብር መመደቡን አሳውቀው ነበር፡፡ ድንገት ዱብ ያለው የዚህ ዕቅድ ዝርዝር እስከዚህ ሳምንት ድረስ ግልጽ አልነበረም፡፡ 

ባለፈው ማክሰኞ ጥር 30 በተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የፈንዱ ማቋቋሚያ አዋጅ እዚህም እዚያም ስለ ገንዘቡ ሲነገሩ የነበሩ ጭምጭምታዎችን ገሃድ አውጥቷል፡፡ በአምስት ገጽ አጠር ተደርጎ የተዘጋጀው አዋጅ ስለ ፈንዱ ዓላማ፣ የገንዘብ ምንጭ እና መጠኑን እና የትኛው አካል የማስተዳደር ስልጣን እንደተሰጠው በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡ አዋጁን በማስፈጸም ረገድ ለተለያዩ አካላት የተሰጡ ኃላፊነቶችንም ይደነግጋል፡፡ 

በተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ አማኑኤል አብርሃም አዋጁ ከመጸደቁ አስቀድሞ ስለ ዓላማው እንዲህ ብለው ነበር፡፡

Äthiopien Addis Abeba Kaffee Wirtschaft Aster Endale
ምስል DW/James Jeffrey

“የወጣቶች ገቢ ማስገኛ እንቅስቃሴዎችን አደራጅቶ በማስገባት ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸውን ማጎልበት የሚያስችል የ10 ቢሊዮን ብር በዚሁ ምክር ቤት ለተዘዋዋሪ ፈንድ እንዲውል ባለፈው ጊዜ መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡ ይህ ተዘዋዋሪ ብድር የሚተዳደርበትን ተቋማዊ አሰራር ለመዘርጋት የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ነው” ብለዋል፡፡   

አዋጁን አስመልክቶ ለምክር ቤት አባላት የቀረበ መግለጫ እንደሚያትተው ከፈንዱ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት በ18 እና 34 የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች ናቸው፡፡ ወጣቶቹ ከፈንዱ ብድር ለማግኘት የንብረት ዋስትና እንዲያቀርቡ ባይጠየቁም በጥቃቅን ድርጅቶች  መደራጀት ግድ ይላቸዋል፡፡ የፈንዱ ተጠቃሚዎች እንዲደራጁ የተፈለገው ከፈንዱ ለሚያገኙት ብድር እርስ በእርሳቸው ዋስ በመሆን ኃላፊነት እንዲወስዱ ለማስቻል እና ገንዘቡን ለተፈለገው ዓላማ እንዲያውሉት አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሆነ መግለጫው ያብራራል፡፡    

በኬንያም ሆነ በደቡብ አፍሪካ ተግባራዊ የሆነው ተመሳሳይ ዕቅድ ግን ወጣቶችን የግድ ተደራጁ አይልም፡፡ በኬንያ በግለሰብ ደረጃ ከወጣቶች ፈንድ መበደር ይቻላል፡፡ የግል ኩባንያዎች፣ የህብረት ስራ ማህበራት እና ቡድኖች በወጣቶች እስከተቋቋሙ ድረስ ከፈንዱ ለመበደር አይከለከሉም፡፡ የደቡብ አፍሪካው ደግሞ የመንገድ ዳር ነጋዴዎች እና አዟሪዎች ጭምር ከገንዘቡ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይጋብዛል፡፡ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዘርፎች በሚል ከሚጠቅሳቸው ውስጥ በኢትዮጵያ ብድር ለማግኘት አዳጋች የሆነባቸው የኢንፎርሜሽና እና ኮሚዩኒኬሽን፣ የፊልም እና የመገናኛ ብዙሃን ዘርፎች ሁሉ ተካትተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያው አዋጅ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድን በመንግስት ስም ያስተዳድር ዘንድ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኃላፊነቱን ሰጥቶታል፡፡ ሆኖም ብድሩን የማቅረቡን ስራ የሚያከናውኑት አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት እንደሆኑ ይደነግጋል፡፡ የአዋጁ መግለጫ ለዚህ የሰጠው ምክንያት “በዚህ ፈንድ ተጠቃሚ የሚሆኑ ድርጅቶች በጥቃቅን የሚፈረጁ በመሆናቸውና ለእነዚህ ዓይነቶቹ ድርጅቶች ብድር ማቅረብ የሚችሉት ደግሞ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ስለሆኑ” የሚል ነው፡፡ እነዚህ የፋይናንስ ተቋማት በሌሉባቸው አካባቢዎች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እነርሱን ተክቶ ይሰራል፡፡ 

Äthiopien Bohrungen nach Wasser in Afar Einheimische
ምስል DW/Getachew Tedla

በፈንዱ የተቀመጠውን 10 ቢሊዮን ብር የየክልሉን የወጣቶች ብዛት መሰረት በማድረግ የመደልደል ስልጣን በአዋጁ የተሰጠው ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ነው፡፡ ለክልሎች የተከፋፈለውን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተቀብሎ ለአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት የማስተላለፍ ሚና የተሰጠው ደግሞ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ በአነስተኛ የፋይናንስ ተቋምነት የተመዘገቡ 33 ድርጅቶች አሉ፡፡ ተቋማቱ ለደንበኞቻቸው የብድርና ቁጠባ አገልግሎቶችን ይሰጣሉ፡፡ 

እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በኬንያም የወጣቶች ፈንድ ለተጠቃሚዎች የሚሰጠው በፋይናንስ ተቋማት በዋናነትም በባንኮች አማካኝነት ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ አሰራር ወጣቶችን ከፈንዱ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ካደረጋቸው ምክንያቶች አንዱ እንደሆነ የሀገሪቱ ዕለታዊ ጋዜጣ “ዴይሊ ኔሽን” ከሁለት ወር በፊት ባወጣው ዘገባ ጠቁሟል፡፡ እንደ ዘገባው ከሆነ አብዛኞቹ የሀገሪቱ ወጣቶች የፋይናንስ ተቋማቱ አሰራር ለእነርሱ ምቹ አይደለም የሚል እምነት አላቸው፡፡ 

በኢትዮጵያ ባሉ አነስተኛ ተቋማት ላይም ተመሳሳይ ጥያቄ ይነሳል፡፡ ስማቸው እንዳይጠቀስ የሚፈልጉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የዘርፉ መምህር በተቋማቱ ዙሪያ ስለሚነሱ ችግሮች አንድ ሁለት ብለው ይዘርዝራሉ፡፡  

“አንደኛ ቶሎ ሂደቱ ተጠናቅቆ ለተጠቃሚዎች ገንዘቡ አይለቀቅላቸውም፡፡ የመዘግየት ነገር ይታያል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የማበደሪያ ዋጋው በአብዛኛው ውድ ነው፡፡ የስራ ማስኪያጃ ወጪ አብሮ ስለሚታሰብ ይሆናል የሚያበድሩበት ዋጋ ከፍ ያለ ነው፡፡ ራሳቸው እነዚህ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት የማበደር ስራቸውን የሚያከናውኑት ተያዥ በመጠየቅ ስለሚሆን ተያዥ የሚሆናቸው አባል፤ ሌላ አብሯቸው የሚሰራ ሰው በህብረት ተያዥ ስለሚሆን፣ አባላት አንዳንድ ጊዜ ፍቃደኛ አይሆኑም፡፡ የሚያበድሩት ገንዘብ መጠንም አነስተኛ ነው፡፡ ይሄ ችግር አለባቸው” ሲሉ ይተነትናሉ፡፡ 

በአዋጁ መሰረት አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ከፈንዱ ብድር ለማግኘት የሚጠይቁ ወጣቶች የሚያቀርቧቸውን ፕሮጀክቶች አዋጪነት ገምግሞ የመወሰን ስልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ ተቋማቱ ፕሮጀክቱ አዋጭ መሆኑን ሲያምኑበት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በሚወስነው የብድር ደንቦችና ሁኔታዎች መሰረት ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን ብድር ለተጠቃሚዎች ያቀርባሉ፡፡  የአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማትን የከዚህ ቀደም አሰራርን ለሚያውቁት ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው መምህር ግን ብድር አሰጣጡ ለወጣቶች ቀላል እንደማይሆን ይታያቸዋል፡፡ ለዚህም ምክንያቶች ይጠቅሳሉ፡፡   

Äthiopien Textilindustrie Fabrik Näherinnen
ምስል Jeroen van Loon

“እነዚህ ደግሞ አሁን የሚመጡ የወጣቶች ፕሮጀክቶች ወይም ሊሰሯቸው የሚፈልጉ ስራዎች መሬት ላይ ገና ያላረፉ በመሆናቸው ለአበዳሪዎች በስጋት ደረጃም ከፍተኛ ናቸው፡፡ እንደዚህ በመሆናቸውም እዚህን አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ሁለት ሶስት ጊዜ ማሰብን ይጠይቃቸዋል፡፡ ብድር ለመልቀቅ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ ሌሎች ተቋማት ላያበድሩ የሚችሉበት የራሳቸው ምክንያት አለ፡፡ ለምሳሌ ባንኮች የማያበድሩት መያዣ ስለሚፈልጉ ነው፡፡ እነዚህ ደግሞ ደሃ ጠቀም ሆነው ነው የሚታዩት እና ቶሎ ለቅቀው፣ ቶሎ ገንዘቡን  ወስደው፣ እነዚህ ወጣቶች ስራ ላይ አውለው ራሳቸው ተጠቃሚ ሆነው፣ ምርት አምርተው ወደ ገበያ እንዲያመጡ ነው የሚፈለገው፡፡ ይሄን ለማድረግ የአቅም ችግር አለባቸው፡፡ የአቅም ስል የአስተዳደራዊ እና የፋይናንስ አቅም [ችግር] አለባቸው፡፡ አሁን ይሄ ገንዘብ በእነርሱ በኩል ሲያልፍ የገንዘብ አቅማቸውን ሊያዳብር ይችላል፡፡ ነገር ግን የአስተዳደር አቅማቸው ካልዳበረ በስተቀር፣ ሌላ ስራ ካልተሰራ በስተቀር የሚቸገሩ ይመስለኛል” ሲሉ ምልከታቸውን ያጋራሉ፡፡    

ከፈንዱ ተጠቃሚ መሆን የሚፈልጉ ወጣቶች ወደ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ከሚሄዳቸው በፊት አንድ ልብ ሊሉት የሚገባ ነገር አለ፡፡ እርሱም በወጣቶች ፈንድ ማቋቋሚያ አዋጅ እና አዋጁን ለማስፈጸም ወደፊት በሚወጣ መመሪያ የሚጠየቁ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ይገባቸዋል፡፡ ከቅድመ ሁኔታዎቹ አንዱ የገቢ ማመንጫ የንግድ ሥራ ፕሮጀክቶችን በሚመለከተው አካል ማስገምገም ነው፡፡ በአዋጁ መሰረት ተጠቃሚዎች የሚያቀርቧቸውን ፕሮጀክቶች የመገምገምና ተቀባይነት ያገኙተን ለአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት የማስተላለፍ ኃላፊነት የተሰጠው በክልል ወይም በከተማ አስተዳደር ያሉ የወጣቶች ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት ናቸው፡፡ 

እነዚሁ አካላት የብድሩ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉ ወጣቶችን የመለየት እና በአነስተኛ ድርጅቶች የማደራጀት ስልጣንም ተሰጥቷቸዋል፡፡ ወጣቶችን በማደራጀት ዙሪያ በሚመለከታቸው የክልልም ሆነ የከተማ አስተዳር አካላት ላይ ተደጋጋሚ ስሞታ ሲቀርብ ይደመጣል፡፡ ወጣቶችን “በማደራጀት ስም የገዢው ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች እንዲሆኑ ያስገድዳሉ” የሚል ውንጀላ ይቀርብባቸዋል፡፡ “የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የሆኑ አሊያም የገዢውን ፓርቲ አመለካከት የማይጋሩ ወጣቶች ብድርም ሆነ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች እንዳያገኙ ያደርጋሉ” በሚልም ይተቻሉ፡፡   
የተቃዋሚው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ተመሳሳይ አስተያየት አላቸው፡፡ 

Eröffnung eines Ausbildungszentrum von Menschen für Menschen in Sheno, Äthiopien
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

“ይሄ ስራ በኢትዮጵያውነቱ አይደለም የሚሰጠው፡፡ በአባልነቱ፣ ለኢህአዴግ በሚያሳየው እና በሚያደርገው አስተዋጽኦ ነው፡፡ ከዚያ ነው ስራ የሚያገኘው፡፡ ስራ ለማግኘት እዚያ የሚመጡት ይደራጃሉ፡፡ ሲደራጁ ማነው የሚያደራጀው? የኢህአዴግ ካድሬ ነው፡፡ ካድሬው ደግሞ ሲደራጁ የኢህአዴግን ጸበል እንዲቀምሱ ነው የሚያደርገው” ይላሉ፡፡  

በዚህም ተባለ በዚያ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶለታል፡፡ የፈንዱ ማቋቋሚያ አዋጅ በምክር ቤት ሲጸድቅ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ የነበሩ ባለስልጣናት ደጋግመው የሚጠቀሙበት ሀረግ “በአፋጣኝ ወደ ስራ ለመግባት” የሚለውን ነበር፡፡ ጥድፊያውን ጋብ አድርጎ በፈንዱ ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች ሩቅ ሳይሄዱ የኬንያን ተሞክሮ መመልከት ተመሳሳይ ስህተቶች ላለመስራት ያግዛል፡፡ 

ፓርስ የተሰኘ በኬንያ ያለ የምርምርና አማካሪ ድርጅት በሀገሪቱ ላለፉት 10 ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ ስለቆየው የወጣቶች ፈንድ ያወጣው ጥናት እንደሚያመለክተው 81 በመቶ የሚሆኑ የኬንያ ወጣቶች ለእነርሱ ተብሎ ከተቋቋመው ፈንድ በፍጹም ተጠቅመው አያውቁም፡፡ ሃምሳ አንድ በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ስለ ፈንዱ ምንነት አሊያም ብድር ማግኘት ስለሚቻልበት አሰራር ዕውቀቱ የላቸውም፡፡ ቢሊዮኖች መድቦ እንዲህም አልተገናኝቶም መሆን አለ፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ