የጦር መሳሪያ ርክክብ በሊቢያ
ሰኞ፣ መስከረም 21 2005የአዲሱን መንግስት ትዕዛዝ በመከተል እስካሁን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሊቢያውያን ትጥቃቸውን ፈተዋል። ይሁንና በሺዎች የሚቆጠሩ ወሳሪያዎች እስካሁን በመንግስት እጅ አልገቡም። አንድ ወጣት ሊቢያዊ በጁ ሙሉ የያዛቸውን ጥይቶች ጠረቤዛ ላይ ይዘረግፋል። የአዲሱ የሊቢያ ፖሊስ ደግሞ ካላሺንኮፍ ውስጥ የሚገቡትን ጥይቶች ቆጥሮ ይረከባል። 21 ናቸው። ይህም በመዝገብ ይያዛል። ሌላ ጠረጴዛ ላይ ደግሞ እንዲሁ ሌላ ሰው ሽጉጡን ያስረክባል። ትጥቅ ፈቺው ወደ ፖሊስ ጣቢያ የመጣበትን ምክንያት እንደሚከተለው ይገልፀዋል።
« የዚህ ርምጃ አካል መሆን ስለፈለኩ ነው ሽጉጤን የመለስኩት። አገራችን የተረጋጋች እና ሰላም የሰፈነባት እንድትሆን እፈልጋለሁ። መሳሪያ የትም ተበትኖ እንዲቆይ አንፈልግም። የምንፈልገው ነገር ቢኖር ሰላም የሰፈነበት ህይወት ነው። የአምባገነኑን ስርዓት ተገላግለናል፤ ስለዚህ ጠመንጃ አያስፈልገንም።»
ይሁንና 200 000 የሚደርሱ የጦር መሳሪያዎች አሁንም በሀገሪቱ ተበትነው እንደሚገኙ ይገመታል። ፈንጂዎች፣ ሽጉጦች እና ጥይቶቹ የተገኙት ከቀድሞው ገዢ ሙአመር አል ጋዳፊ የጠመንጃ ስብስብ ነው።
ከ800 በላይ ሽጉጦች፣ 200 ጓዳ ሰራሽ ፈንጂዎች፣ 100 የታንክ ጥይቶች እና 20 000 የጠመንጃ ጥይቶች 6 ሮኬቶች እና አንድ ታንክ ለማስረከብ በተቋቋሙ ጣቢያዎች ተመላሽ ሆነዋል።
ይህ ገና መጀመሪያው ነው። በዚህ አይነት መንገድ ብቻ ነው የሊቢያ ደህንነት ሊሻሻል የሚችለው ይላል ሌላ ሽጉጡን ሊመልስ የመጣው ሊቢያዊ፤« ቀን በቀን ሲካሄድ የነበረው መታኮስ በቅቶናል ነው ያለው አንዱ ታጣቂ፤ አዎ ይህ ይበቃል። መቆም አለበት ሁሉም ጥይቁን ማስረከብ አለበት።»
ከተረካቢዎቹ አንዱ ፖሊስ ይህንን የትጥቅ መፍታት ሂደት በአድናቆት ሲመለከት ቆይቷል። ድርጊቱም በዚህ መልኩ ለሚቀጥሉት ሳምንታት መቀጠል አለበት ባይ ነው።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት አነጋጋሪ በነበረው እስልምናን የሚያንቋሽሽ ፊልም ሳቢያ በተነሳው ተቃውሞ ቤንጋዚ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ ለደረሰው ጥቃት ፣ ለአምባሳደሩ እና ለሌሎች ሶስት ባለስልጣናት ሞት መነሻ የሆነው በአመፁ ላይ ተሳታፊዎች መሳሪያ እንደ ልብ ስለታጠቁ ነው የሚሉ አልጠፉም። ይሁንና የዮናይትድ ስቴትስ የስለላ ቡድን በሳምንቱ መጨረሻ እንዳስታወቀው፤ መስከረም 1 ቀን በአሜሪካ ኤምባሲ ላይ የደረሰው ጥቃት ሆን ብሎ በአልቃይዳ የታቀደ ነው።
ያም ሆነ ይህ ግን በሊቢያ መረጋጋት እንዲሰፍን ህዝቧ ጦር መፍታት አለበት።የዶይቸ ቬለ ዘጋቢ ፔተር በቦታው በመገኘት እንደተከታተለው ከሆነ በጥብቅ ቁጥጥር መበመካሄድ ላይ የሚገኘው የጦር መሳሪያ ምለሳ አሰራር ሽልማት ስለሚያስገኝ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በህዝቡ ዘንድ ድጋፍ ያገኘ ይመስላል። ጠመንጃ እና ጥይት ላስረከቡት እጣ ይወጣና፤ በስተመጨረሻ ሁለት ሰዎች የመኪና ባለቤት ይሆናሉ።
ፔተር እሽቴቬ
ልደት አበበ
ነጋሽ መሐመድ