የጡት ካንሰር ቅድመ ጥንቃቄ
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 11 2007በያዝነዉ የጥቅምት ወር በተለያዩ ሃገራት ሰዎች ስለጡት ካንሰር መንስኤና ምንነት አዉቀዉ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተደጋጋሚ ቅስቀሳ ይደረጋል። የጡት ካንሰር በአብዛኛዉ ሴቶችን የሚያጠቃ ይሁን እንጂ ወንዶችም ሊያጋጥማቸዉ ይችላል።
በየዕለቱ ለግማሽ ሰዓት ያህል በእግራቸዉ የሚጓዙ ሴቶች የጡት ካንሰርን ስጋት ሊቀንሱ እንደሚችሉ ጥናቶች ያመለክታሉ። በተለይም የወር አበባ ዑደት ካቆመ በኋላ የተለያዩ የአካል እንቅስቃሴዎችን ካዘወተሩ በበሽታዉ የመያዝ እድላቸዉ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ ጥናቱ ጠቁሟል። ጥናቱን ያከናወኑት የፈረንሳይ የዘርፉ ተመራማሪዎች እንደሚሉትም በብዙዎቹ ላይ እንደታየዉ መደበኛና ተከታታይ እንቅስቃሴ የሚያድርጉ ሴቶች በጡት ካንሰር የሚያዙበት አጋጣሚ መቀነሱን አስተዉለዋል። ለዚህም ነዉ ሌሎች የስፖርት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንኳ ባይሳካ በእግር ለ30 ደቂቃ ያህል በቀን መጓዝ ከበሽታዉ ሊታደግ እንደሚችል ያመለከቱት። ኢትዮጵያዊዉ የዘርፉ ባለሙያና ሃኪም ዶክተር ቦጋለ ሰሎሞንም ስለበሽታዉ የሰጡን ማብራሪያ ይህንኑ ያጠናክራል። ዶክተር ቦጋለ የጡት ካንሰርን ሊያስከትሉ የሚችሉ ምክንያቶችን በትክክል ይኽ ነዉ ብሎ ለመወሰን እንደሚያዳግት በመጠቆም ለበሽታዉ ሊጋልጡ ይችላሉ የሚባሉትን ያብራራሉ። ሴቶች ብቻ አይደሉም የጡት ካንሰር ሰለባዎች፤ ቁጥራቸዉ ከመቶ ሲሰላ ይቀንስ እንጂ ወንዶችንም አይምርም።
ሸዋዬ ለገሠ
አርያም ተክሌ