1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጠፈርተኛ አርምስትሮንግ ኅልፈትና ጨረቃ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 23 2004

ያኔ ፤ በኅዋ ምርምር ረገድ እኔ እበልጥ ፣ እኔ እበልጥ በነበረው ፉክክር ፤ልቆ፣ በልጦ ለመገኘት እንጂ የገጠጠ አካል ባላት፤ በምድረ በዳዋ ፣ የፕላኔታችን የቅርብ አጃቢ የሰማይ አካል (ጨረቃ) አንዳች ጥቅም ይገኛል የሚል መላ ምት

https://p.dw.com/p/15zXA
ምስል NASA/dapd
Mondlandung 1969 Neil Armstrong
ምስል Getty Images

አልነበረም ። ይሁንና ቀድሞ መገኘት ስለተፈለገ፤ ዩናይትድ እስቴትስ እ ጎ አ ሐምሌ 21 ቀን 1969 ዓ ም፤ ጨረቃ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰው እንዲያርፍባት አደረገች። በጨረቃ ላይ እግሩን ያሣረፈው የመጀመሪያው ሰው ፤ ባለፈው ቅዳሜ ፤ በ 82 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ኒል አርምእስትሮንግ ፤ አንድ ጊዜ እንዳለው፤ በዚያ ዘመን ከሶቭየት ኅብረት ጋር ጠንካራ ፉክክር ባይኖር ኖሮ ፣ ዩናይትድ እስቴትስ ያን አስደናቂ ተግባር ማከናወን ባልቻለች ነበር።

«አፖሎ 11» የተሰኘችው የጠፈር መንኮራኩር ወደ ጨረቃ በመጠቀጭበት እርምጃ ኒል አርምእስትሮንግና ባልደረቦቹ፣ ኤድዊን ኦልድሪንና ማይክል ኮሊንስ ፤ተልእኮአቸውን አሳክተው ከተመለሱ በኋላ ፤ የአርምስትሮንግ ዝና ገዝፎ በመስተጋባቱ ደስተኛ አልነበረም። ሰው ጨረቃ ላይ ሲያርፍ 8 ኛ ዓመታቸውን ሊያከብሩ 2 ሳምንት ቀርቷቸው የነበሩት የአሁኑ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤

Kombibild Astronaut Neil Armstrong
ምስል picture-alliance/dpa/DW

«አርምስትሮንግ ያከናወኑት ፈጽሞ የማይረሳ የሰው ተግባር ውጤት ነው » ነው ያሉት። ቤተሰቦቻቸው የሟቹን የሥራ ክንዋኔ በማድነቅ ፣ «አሜሪካዊው ጀግና» መባልንም ሆነ ውዳሴን ይጠሉ የነበሩት ትኁቱ አርምስትሮንግ፤ ያበረከቱት ድርሻ፤ ወጣቶች ተነቃቅተው ፤ በትጋት ጠንክረው እንዲሠሩና ህልማቸውን እውን እንዲያደርጉ ያለውን ተስፋ ገልጾአል።

በ 16 ዓመቱ የበረራ ፈቃድ ያወጣውና በኮሪያው ጦርነት 78 ጊዜ የበረራ ተልእኮ ያከናወነው አርምስትሮንግ ፣ በ 1955 ከ NASA በፊት ብሔራዊ የበረራ ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ የተሰኘው ድርጅት አባል ሆነ። በኤድዋርድስ ፣ ካሊፎርኒያ የ NASA የበረራ ምርምር ማዕከል የተለያዩ እጅግ ፈጣን ጄት አኤሮፕላኖችን፤ ያበር የነበረው አርምስትሮንግ በመጨረሻ እ ጎ አ በ 1962 ወደ ጠፈርተኛነት ተዛውሮ፣ በመጀመሪያ «ጀሚናይ-8 » የተባለችውን መንኮራኩር በአብራሪነት የተሣካ ተልእኮ አከናወነ። ከፍተኛ ዝናን ያተረፈው ግን ቀደም ስል እንደተጠቀሰው በአፖሎ መንኮራኩር ከ2 ባልደረቦቹ ጋር ተጉዞ ጨረቃ ላይ በመራመዱ ነበር።

Mond Vollmond
ምስል picture-alliance/dpa

በ 1971 ጡረታ ከወጣ በኋላ፤ በዩንቨርስቲ የጠፈር ኢንጂኔሪንግ አስተማሪ በመሆን ከሞላ ጎደል ለ 10 ዓመት ያህል አግልግሏል። ትንሽ ዕድሜ ቢቀጥልለትና 89 ዕድሜ ላይ ቢደርስ ኖሮ፣ (እ ጎ አ በ 2019 ዓ ም መሆኑ ነው፤)የአፖሎ 11 ባልደረባው ኤድዊን ኦልድርን እንዳለው ጨረቃ ላይ ሰው እግሩን ማሳረፍ የቻለበትን 50ኛ ዓመት፣ 3 ቱም አብረው የማክበር ምኞት ነበራቸው።

ቀደም ሲል እንዳልነው ፤ ሰው ጨረቃ ወደ እንዲጓዝ በተደረገበት ወቅት ፤ ዛሬ የሚታወቀውን ያህል ስለጨረቃ አንዳንድ ተጨማሪ ምሥጢሮች አይታወቅም ነበር። ለምሳሌ ያህል ፤ ጨረቃ በረጋ በረዶ አማካኝነት ውሃ ያላት መሆኑን NASA ያረጋገጠው እ ጎ አ ጥቅምት 9 ቀን 2009 ዓ ም፤ በደቡባዊው የጨረቃ ዋልታ ፣ አንድ ጉድጓድ ያለው ተራራ በሮኬት እንዲመታ በማድረግ ነው። ከዚህ ጎድጓዳ ተራራ 6 ከመቶ ገደማው የረጋ የበረዶ ውሃ መሆኑ ታውቋል።

ይኸው ቦታ አንድ ቢሊዮን «ጋለን» የበረዶ ውሃ የሚገኝበት፣ ማለትም 1,500 የኦሊምፒክ ዋና መወዳዳሪያ ኩሬዎችን ያክል ቦታ በውሃ መሙላት የሚያስችል ነው። ስለዚህ ጨረቃ ወደፊት ወደ ማርስም ሆነ ሌላ የጠፈር አካል ለታሰቡ ጉዞዎች ፣ ማረፊና ስንቅ ማዘጋጂያ ቦታ መሆኗ አይቀሬ ነው ማለት ይቻላል።

ስለጨረቃ ምንነት፤ ለፕላኔታችን ስላላት ዘርፉ ብዙ ጠቀሜታ ዝግጅታችን ይበልጥ ያብራራል----።

የጨረቃ ምንነትና ለፕላኔታችን ያላት ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ፣

ተክሌ የኋላ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ