1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግእዝ ፊደላት እና ሥነ-ቴክኒክ

ረቡዕ፣ ጥር 25 2008

አንድ ሰው በዙር አዙር ካልሆነ በአፕል ምርቶች ላይ በአማርኛ ለመጻፍ ወይንም ጽሑፎችን ለማንበብ አይችልም። አንድሮይድ የተሰኘውን የማስተናበሪያ እና ማንቀሳቀሻ ስልት Operating System)በሚጠቀሙ ዘመናዊ የእጅ ስልኮችም ሆኑ ሌሎች መሣሪያዎች ላይ ለብዙዎች አማርኛን በቀጥታ መጻፍ ያስቸግራል። በእርግጥ አስቸጋሪነቱ በቀላሉ ሊፈታ የሚችል ነው።

https://p.dw.com/p/1HoIP
Ein Amharischer Font
ምስል S. Mantegaftot

የግእዝ ፊደላት እና ሥነ-ቴክኒክ

በዘርፉ የተሠማሩ ባለሙያዎች በተናጠል የሚያደርጉትን ጥረት ማማከል ባለመቻሉ ግን ችግሩ አኹንም ድረስ ዘልቋል። አማርኛ ፊደላትን በዘመናዊ የስነ ቴክኒክ ውጤቶች ላይ በቀጥታ እና በቀላሉ ለመጻፍም ኾነ ለማንበብ በዘርፉ የተሠማሩ ባለሙያዎች ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል?

አንድ ኮምፒውተር ወይንም ዘመናዊ የእጅ ስልክ ላይገና እንደተገዛ የእንግሊዝኛ ቋንቋን ያለምንም ተጨማሪ ነገር መጻፍ እና ማንበብ ይችላል። አማርኛን ለማንበብ ግን ሌሎች ማንቀሳቀሻዎችን ማለትም (Apps) ካልተጠቀሙ በስተቀር ብዙውን ጊዜ አዳጋች ነው። በቀጥታ የግእዝ ፊደላትን ተጠቅሞ አማርኛን ማንበብም ኾነ መጻፍ ይከብዳል። እንግሊዝኛ ቋንቋን ለመጻፍ ግን በየትኛውም ዓለም ሁሉም ሰው የሚጠቀምበት ደረጃ ስለተበጀለ አያስቸግርም። የግእዝ ፊደላትን መጻፊያ ስልት እና የመጻፊያ ቁልፉ አቀማመጥ ሥራ ባልተማከለ ኹኔታ በተናጠል በተለያዩ ባለሙያዎች እየተከናወነ ይገኛል። አሜሪካን ሀገር ማሃሪሺ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በኮምፒውተር ሣይንስ የማስተርስ ዲግሪውን እየሠራ የሚገኘው ቴዎድሮስ አየለ ሥራው በተለያዩ ባለሙያዎች በተናጠል መቀጠሉ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ይናገራል።

ቴዎድሮስ ኢትዮጵያ ውስጥ በኮምፒውተር ሣይንስ ከተመረቀ በኋላ ለስድስት ዓመታት በኮምፒውተር ሣይንስ ዘርፍ አገልግሏል። ትልልቅ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን የሚያስተዳድሩበት የኢንተርኔት መረብ ሲዘረጋም ቆይቷል። አሜሪካን ሀገር ከገባ ሰባት ወራት አስቆጥሯል። አንድሮይድን የሚጠቀሙ መሣሪያዎች ላይ አማርኛን ማንበብ ተችሎ እንደ አይፎን እና አይፓድን በመሳሰሉ የአፕል ምርቶች ላይ ለምን እንደማይነበብ ያብራራል።

የተለያዩ ግዙፍ ተቋማት የየራሳቸው የተለያዩ የኮምፒውተር ቋንቋዎችን ይጠቀማሉ። ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያኽል፦ የጉግል አንድሮይድ የማስተናበሪያ እና ማንቀሳቀሻ ስልት የሚጠቀመው ጃቫ ነው። አፕል አይ ኦ ኤስ ደግሞ የራሱ እንደ ስዊፍት ያለ ቋንቋ አለው። ማይክሮሶፍት ዊንዶው መረጃዎችን የሚተነትነው በሲ ፕላስ ፕላስ እና ሲ ነው። አማርኛ የሚጻፍበት ግእዝ ፊደልም ጥቅም ላይ እንዲውል በባለሙያዎቹ ሲደራጅ እንዚህን ማንበቢያዎች በማገናዘብ ነው። የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የደረጃ ዝግጅት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ለገሠ ገብሬ ፊደላቱም ሆነ ማንኛውም ነገር በደረጃ እንደሚመራ ተናግረዋል።

የአፕል ምርቶች ገና እንደተገዙ ሌላ ነገር ሳይጨመርባቸው በቀጥታ የአማርኛ ጽሑፍ እንዲነበብባቸው እና እንዲጻፍባቸው ማድረጉ በጣም ቀላል ነበር ይለናል ቴዎድሮስ። ይሁንና ግን አፕል አማርኛ ፊደላትን በቀጥታ ያልተጠቀመው ኢትዮጵያ ውስጥ ገበያ ስለሌለው ሳይሆን አይቀርም ሲል አክሏል።

ከሣይንስ እና ቱክኖሎጂ ሚንሥትር የቴክኖሎጂ ሽግግር ልማት ዳይሬክቶሬት ያገኘነው መረጃም እንደሚጠቁመው ገበያው በራሱ ጊዜ ግዙፍ ኩባንያዎቹ ወደፊት በቀጥታ የአማርኛ ጽሑፍን እንዲጠቀሙ እንደሚያደርጋቸው ይጠቁማል። ይሁንና ግን ገበያው በራሱ ጊዜ መፍትኄውን እስኪያበጅ ድረስ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ምርምርም እየተደረገ መሆኑ ተጠቅሷል። ብዙ ነገሮች ጥናት ላይ መሆናቸውም ተገልጧል። የፊደላቱ አቀማመጥ ፊደል መምቺያ ቁልፉ ላይ ወጥ ሆኖ የሚሠራበት ስልት (Standard)መበጀት እንደሚገባው፤ በዚያ ዙሪያም ተጨማሪ ጥናቶች እንደሚኖሩ ከመሥሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። አማርኛ ፊደላትን ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጋር ማቆራኘት ለእውቀት ሽግግር ወሳኝ መሆኑን ቴዎድሮስ ይገልጣል።

የሣይንስ እና ቱክኖሎጂ ሚንሥትር አንድ ባለሙያ «ኅብረተሰቡ በአማርኛ ፊደላት ያለምንም ዙር አዙር በቀጥታ ኢንተርኔት ላይ መጠቀም ቢችል ጥቅሙ የጎላ ነው» ብለዋል። ለአብነት ያኽልም «-የሞባይል ስርጭት በኢትዮጵያ ሲስፋፋ በመጀመሪያ አካባቢ ለብዙ ሰዎች ሁሉም ነገር በእንግሊዝኛ መሆኑ ከባድ ነበር። አሁን ግን በአማርኛ ሲሠራ የኢትዮጵያ አምራች አርሶ አደርም ሆነ አርብቶ አደሮች ሞባይሎችን በቀላሉ መጠቀም ችለዋል» ብለዋል። የእንግሊዝኛ ፊደላት መተየቢያ ቁልፍ የአቀማመጥ ስልት (QWERTY) ላይ ከረዥም ዘመን አንስቶ ስምምነት በመደረሱ በዓለማችን የእውቀት ሽግግር እንዲፋጠን፤ ክፍሎት እንዲዳብር ብሎም የሥራ ፈጠራ እንዲስፋፋ አግዟል። የግእዝ ፊደላት ፎንት እና የመተየቢያ ቁልፍም ወጥነት ሊኖረው ይገባል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

USA Zentrale von AEP - Server
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Minchillo
Eine Amharische Tastatur
ምስል S. Mantegaftot

ነጋሽ መሐመድ