የግብፅ ፕሬዝዳት ዉሳኔና ተቃዉሞዉ
ረቡዕ፣ ኅዳር 19 2005
የግብፁ ፕሬዝዳንት መሐመድ ሙርሲ በቅርቡ የሐገሪቱን ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ሥልጣን የሚገድብ ደንብ መደንገጋቸዉ ያስቆጠዉ ሕዝብ በየአደባባዩ የሚያደርገዉ ተቃዉሞ እንቀጠለ ነዉ።ፕሬዝዳት ሙርሲ ትናንት ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ጋር ቢነጋገሩም ያወጁትን ደንብ እንደማይሽሩት አስታዉቀዋል።ሙርሲ በአቋማቸዉ መፅናታቸዉ ከተነገረ በሕዋላ ፕሬዝዳንቱንና የፕሬዝዳንቱን ፓርቲ የሚቃወሙ ወገኖች በየከተማዉ የሚያደርጉት የተቃዉሞ ሠልፍ ተጠናክራል።ዘገቦች እንደጠቆሙት ትናንት ካይሮ ዉስጥ በተደረገዉ የተቃዉሞ ሠልፍ የተሳተፈዉ ሕዝብ ቁጥር የቀድሞዉ ፕሬዝዳት ሆስኒ ሙባረክ ከሥልጣን ከተወገዱ ወዲሕ እጅግ ከፍተኛዉ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝር ዘገባ አለዉ።
ያ-የነፃነት አብነቱ፥ የመስዋዕትነት ተምሳሌዉ፥ የሕዝባዊ አብዮት መናኸሪያዉ አደባባይ ሰሞኑንንም እንዳምና ሐቻምናዉ በተቃዉሞ ሠልፈኛ ተጨናንቋቋል።ተሕሪር።ያሁኑ ሠልፍ-ተቃዉሞ ያነጣጠረዉ ሕዝባዊዉ አብዮት በወለደዉ ሕዝባዊ ምርጫ ለሥልጣን በበቁት ፕሬዝዳት ላይ ነዉ።መሐመድ ሙርሲ።
ተንታኞች እንደሚሉት የግብፅ ሕዝባዊ አብዮት ታላቅ ድል በከፊል የመከሽፉ ምልክት።በግብፅ የዘመናት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ ድምፅ የተመረጡት መሐመድ ሙርሲ ተቃዋሚዎቻቸዉ እንደሚሉት አንድም የዘመኑ ፈርዖን አለያም ዳግማዊ ሆስኒ ሙባረክ ናቸዉ።ወይም ለመሆን ይሞክራሉ።
የሙርሲን ተቃዋሚዎች ላደባባይ ሠልፍ ያሳደመዉ፥ ሙርሲንና የቀድሞ ፓርቲያቸዉን ሙስሊም ወንድማማቾችን የሚያስወግዝ፥ የሚያስረግመዉ ፕሬዝዳንቱ የሐገሪቱን ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ሥልጣን የሚገድብ ደንብ ማወጃቸዉ ነዉ።በአዋጁ መሠረት ሕገ-መንግሥታዊዉ ፍርድ ቤት የሐገሪቱን ምክር ቤትና ሕገ-መንግሥታዊ ሸንጎን የማገድ ወይም የመበተን ሥልጣኑ ተገፏል።
እርምጃዉ የቀድሞዉ አምባገነን መሪ ሆስኒ ሙባረክ ለሾሟቸዉ ለሕገ-መንግሥታዊና ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች የሞት ሽረት ጥያቄ ነዉ።የሙርሲ ተቃዉሚ ፖለቲከኞችና አደባባይ ያስወጡት ሕዝብ ደግሞ ግብፅን «በሸሪዓ ሕግ ለመግዛት» ይፈልጋል የሚሉት የሙስሊም ወንድማማቾች ሐገሪቱን እንዳሻዉ ለመግዛት ፕሬዝዳንቱ ጥሩ መደላድል መፍጠራቸዉ ነዉ።
«የሙስሊም ወንድማማቾች ላዕላይ መሪ እዉነተኛዉ የግብፅ ገዢ ነዉ።ግቦፆችና ሙርሲ የሚያደርጉትን የሙስሊም ወንድማማቾች እንዲያደርጉ የሚነግሯቸዉን ነዉ።»
አሉ የካይሮዋ ነዋሪ።
የፕሬዝዳንቱ ደጋፊዎች ተቃዋሚዎቻቸዉን ለመቃወም አደባባይ ለመዉጣት ተዘጋጅተዉ ነበር። ፕሬዝዳንቱ ግን አይሆንም አሉ።ፕሬዝዳንቱ ፖለቲካዊ መልክና ባሕሪ የተላበሰዉን ቁጣና ተቃዉሞ ለማቀዝቀዝ ትናንት ከዳኞቹ ጋር ተነጋግረዉ ነበር።አልተስማሙም።
ዉይይቱ ያለ ዉጤት ማብቃቱ እንደተሰማ የአደባባይ ሠልፍ፥ተቃዉሞዉ እየጠነከረ ሔደ።ትናንት አደባባይ የወጣዉ ተቃዋሚ ወደ ሰወስት መቶ ሺሕ ተገምቷል። ተቃዋሚዎችን የሚቃወሙት ወይም ፕሬዝዳንቱን የሚደግፉት ወገኖችም አደባባይ አይዉጡ እጅ ቁጣ ንዴታቸዉ እያየለ መሆኑን አልሸሸጉም።እና በሳቸዉ ቋንቋ ግብፅ ለሁለት ተገመሰች።
«ገሚሱ ከሙርሲ ጎን ቆሟል። የተቀሩት ገሚሶቹ እሳቸዉን ይቃወማሉ።እንግዲሕ ማን እንደሚያሸንፍ እናያለን።ፍትሕ ያሸንፋል።»
በፊት እንደታሰበዉ ቢሆን ኖሮ ዛሬ አዲሱ ሕገ-መንግሥት ተረርቅቆ የሚያበቃበት ዕለት በሆነ ነበር።አልሆነም።የዉዝግብ፥ ንትርክ ቀን እንጂ። ዉዝግቡ ባስከተለዉ ግጭት እስካሁን ሰወስት ሰዎች ተገድለዋል።ዉዝግቡም እንደቀጠለ ነዉ።
ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ