1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግብፅ ሕዝባዊ አብዮትና ሙርሲ

ሰኞ፣ ጥቅምት 5 2005

የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ፕሬዝዳቱን የሚሞግቱ የሕግ ባለሙያ፥ የሕግ በላይነትን አክብረዉ ዉሳኔያቸዉን የሚሽሩ ፕሬዝዳት፥ ፕሬዝዳንቱን የሚተቹ መገናኛ ዘዴዎች፥ የፕሬዝዳንቱን አዋጅ የሚጠራጠሩ የመብት ተሟጋቾች እንደ አሸን ፈልተዉባታል።

https://p.dw.com/p/16QVS
zu: Bringt Mursi den Ägyptern Gerechtigkeit? Egypt's President Mohamed Mursi attends a meeting at the presidential palace in Cairo October 8, 2012, a day after Mursi's "Al Nhada (Renaissance) project. The project is primarily a economic and social programme comprising of promises the president vowed to fulfil within 100 days of taking office. Mursi has won grudging respect from detractors in his first 100 days by sending the army back to barracks faster than anyone expected and raising Egypt's international profile in several newsmaking visits abroad. Yet his political fortunes and those of the Muslim Brotherhood which propelled him to power may well depend on his delivering on more mundane issues such as easing traffic congestion and bread and fuel shortages by Oct. 7 as promised. REUTERS/Amr Abdallah Dalsh (EGYPT - Tags: POLITICS)
ሙርሲምስል Getty Images

የግብፅ ሕዝብ አዲሱ ፕሬዝዳቱ ሥልጣን የያዙበትን አንድ መቶኛ ቀን ገሚሱ፦ በአደባባይ በመደባደብ ሌላዉ በክርክር አከበረ።የክፍፍል ድብድቡ ሠበብ ምክንያት የታላቁን ሕዝባዊ አብዮት ሒደት ዉጤት እንዴትነት ዳግም አነጋጋሪ፥ አደናጋሪም አድርጎታል።የአብዮቱ ዉጤት አነጋጋሪ-አደናጋሪነቱ አስተንትኖ ሳያበቃ፥ ፕሬዝዳት መሐመድ ሙርሲይ ከሐገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ-ሕግ ጋር የገጠሙት እሰጥ አገባ በጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ድል መደምደሙ ተነገረ።የሙርሲይ መርሕ መነሻ፥ የግብፅ ሕዝባዊ አብዮት ሒደትና ዉጤት ማጣቀሻ፥ ጥቅል አስተምሕሮቱ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

የግብፅ አስመራጭ ኮሚሽን ሐላፊ።ግንቦት ሃያ-አራት፥ ሁለት ሺሕ አስራ-ሁለት (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።ግብፅ በዕልፈ-ዓዕላፋት ታሪኳ ለመጀመሪያጊዜ በሕዝቧ ድምፅ መሪ ተሰየመባት።መሐመድ ሙርሲይ።ተሕሪር አደባባይ በዳግም ድል ቦረቀ።

የግብፅ ሕዝባዊ አብዮት የሐገሪቱን አምባ ገነናዊ አገዛዝ ለማስወገድ ድል፥ መሐመድ ሙርሲን ለማስመረጥ ዉጤት የበቃዉ በሺ የሚቆጠሩ አብዮተኞችን ሕይወት፥ አካል፥ ደም አስገብሮ ነበር። የዩኒቨርስቲ መምሕርና ሙዚቀኛ አሕመድ ባሶዩኒ ባደባባይ ተቃዉሞዉ መሐል በፕሬዝዳት ሆስኒ ሙባረክ ታማኝ ታጣቂዎች ከተገደሉት አንዱ ነዉ።የሰላሳ-አንድ ዓመት ወጣት ነበር።


ፕሬዝዳት መሐመድ ሙርሲ የፕሬዝዳትነቱን ሥልጣን የያዙበት መቶኛ ዓመት ባለፈዉ ሳምንት ሰኞ ሲከበር የወጣቱ መምሕርና ሙዚቀኛ የቀድሞ ተማሪዎች መሕራቸዉን ሟቹ በሚወደዉ ሙዚቃ ግን በሐዘን ሥልት ዘከሩት።

የአንጋፋዉን የግብፅ የፖለቲካ ማሕበር የሙስሊም ወንድማማቾች አባል የሆነዉ የነፃነትና የፍትሕ ፓርቲ መሪ የመሐመድ ሙርሲይ ፕሬዝዳንትነት፤ እነ መምሕር አሕመድ ባሲዩኒ መስዋዕት የሆኑለት አብዮት ዉጤት መሆናቸዉ የተጠራጠረ የለም።ፕሬዝዳቱም ከተመረጡበት ጊዜ ጀምሮ የአብዮቱን ዉጤት ለመጠበቅ፥የአብዮተኞችን ዓላማ ለማሳካት፥የአብዛኛ ሕዝባቸዉን ፍላጎት ለማሟላት እንደሚጥሩ ቃል ያልገቡበት ጊዜ የለም።

«እንደ ፕሬዝዳት የሕዝብ አገልጋይና የሕዝብ ተገዢ ነኝ።ከነበላይ ይሁንና እኔ ካገኘሁት ድምፅ በላይ ድምፅ ያገኙት አብዮቱና ሌሎቹ ፕሬዝዳንታዊ ተፎካካሪዎች ከጎኔ እንዲቆሙና እንዲተባበሩኝ እጠይቃለሁ።በዘመነ-ሥልጣኔ ሁሉም የፖለቲካ ቡድናትና ማሕበራት፥ ወንዶች፥ ሴቶችና ወጣቶች በሙሉ ይወከላሉ።»

መሐመድ ሙርሲ ።ሙርሲ ሥልጣን የያዙበት መቶኛ ቀን ሲከበር ግን ያ የሆስኒ ሙባረክን አገዛዝ ለማስወገድ ባንድ አብሮ ተሕሪር አደባባይን ሲያጨናንቅ የከረመዉ ሕዝብ የሙርሲ ደጋፊና ተቃዋሚ በሚል ለሁለት ተገምሶ ነበር።

ግራ ፖለቲካ የሚያቀነቅ ነዉ፥ ለዘብተኛ የሚባለዉና በሙርሲ የመቶ ቀን ሥራ-መርሕ ያልተደሰተዉ ወገን የሙርሲይ መንግሥት እስላማዊ አስተምሕሮትና ደንቦችን ይከተላል፥የሐገሪቱ ሕግ ለማድረግም ይጥራል ባዮች ናቸዉ።በሙርሲ መርሕ አለመርካታቸዉን ወይም ተቃዉሟቸዉን ለማሳየት ባለፈዉ አርብ አደባባይ ወጡ።

የሙርሲ ደጋፊና ለእስልምና ሐይማኖት ያዳላሉ የሚባሉት ደግሞ የፕሬዳንቱን ተቃዋሚዎች በመቃወም እዚያዉ ተሕሪር አደባባይ ይሰለፋሉ።ሁለቱ ተቀናቃኝ ሰልፈኞች ያን የሰላማዊ ትግል አብነት፥ የሕዝባዊ አብዮት መታደሚያ አደባባይን የመቧቀሻ መድረክ፥ የመፈነካከቺያ ሜዳ አደረጉት።

የግብፅ ጤና ጥበቃ ሚንስቴር እንዳስታወቀዉ በግጭቱ አንድ መቶ አርስ ሰዎች በመጠኑ ቆስለዋል።አዉቶቡስ ተቃጥሏል፥ መስተዋት ተሰባብሯል።ሌላ ንብረትም ጠፍቷል።

ሙርሲይ የምሕንድስና ፕሮፌሰር የነበሩትን ያክል፥ የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ አባል፥ ባለሥልጣንም ናቸዉ።

ከግብፅ ሕዝብ የመረጣቸዉ እንዳለ ሁሉ ያልመረጠ የሚቃወማቸዉም፦ የሚደግፋቸዉ እንዳለ ሁሉ የሚቃወማቸዉ መኖሩ አያጠያይቅም።ተቃዉሞ ድጋፍን መግለፅ ደግሞ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ወግ፥ ሰዉ የመሆን ባሕሪ ነዉ።ድብድብን ምን አመጣዉ?።መልስ ያጣ ጥያቄ።

የፕሬዝዳት ሆስኒ ሙባረክን አገዛዝ በመቃወም አደባይ እንደወጣ የሙባረክ ታማኞች የጥይት ራት ሆኖ በዚያዉ የቀረዉ የመምሕርና የሙዚቀኛ አሕመድ ባሶዩኒ የቀድሞ ተማሪዎች መምሕራቸዉን የዘከሩት ከአደባባዩ ሰልፍ፥ ከግጭት፥ዉዝግቡ ገለል፥ ቀለል ባለ አደራሽ ነበር።

ተማሪዎቹ በዚያ አዳራሽ በአዘጋጁት ትርዒት የመምሕራቸዉን ማንነት፥ አለማ፥ ገድሎቹን የሚያስረዱ መግለጫዎችንና የሙዚቃ ሥራዎቹን ለተመልካች አቅርበዋል።ጎብኚዎቹ የሟቹን ወጣት መምሕር ታሪክ፣ አላማ የማድነቅ፥ በወጣት እድሜዉ በመሰዋቱ የማዘን መተከዛቸዉን ያክል የሞተለት ሕዝባዊ አብዮት ሥለ ደረሰበት ደረጃ ማዉሳታቸዉም አልቀረም።

እሳቸዉ ትርዒቱን ከጎበኙት አንዷ ናቸዉ።የምዕራብ መገናኛ ዘዴዎች ለዘብተኛ እና አክራሪ፥ ወይም ግራ እና ቀኝ ፖለቲከኛ እያሉ ከሚከፍሏቸዉ አንዷ መሆን አለመሆናቸዉ ግን ግልፅ አይደለም።ቢያንስ ያሉትን ባለበት ወቀት ተሕሪር አደባባይ አልነበሩም።አዲሱን ፕሬዝዳት ግን ይቃወማሉ።
«ሙርሲ የአብዮቱ ፕሬዝዳት አይደሉም።አዳዲስ ችግሮች ተፈጥረዋል።መብራት ይቋረጣል።ሌሎችም ከዚሕ በፊት ያልነበሩ ችግሮች አሉ።»

አምር ሶብሐኒም እንደ ወይዘሮዋ ሁሉ ለዚያ ወጣት መሕምሕር የተዘጋጀዉን ትርዒት ጎብኝተዋል። የሕዝባዊ አብዮቱን ሒደት ዉጤትም ያዉቁታል።የአዲሱ ፕሬዝዳት መርሕ፥ ጅምር ሥራን ይደግፋሉ።

«ገቢር ለማድረግ ቃል ከተገባዉ 64 ጉዳይ አራቱ ተከናዉኗል።ከተቀረዉ ሃያ አራቱን ገቢር ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።»

ሌላዉ ጎብኚ ግን የሶብሐኒን አስተያየት አይቀበሉትም።እንደ ወይዘሮዋ ሙርሲን ይቃወማሉ። ምክንያታቸዉ ግን ከወይዘሮዋ ጠንከር ያለ ነዉ።«ሙርሲና ሙስሊም ወንድማማቾች የሙባረክን ሥርዓት እንዳለ ከመተካት ባለፍ የተከሩት ነገር የለም።የአብዮቱን ዓለማ ለማሳከት ያደረጉትን ምንም አላየሁም።ከቀድሞዉ ሥርዓት ተጠያቂ የሆኑ አሉ ማለት ይከብዳል።እንዲያዉም ጦር ሐይሉ እየተወደሰ ነዉ።»

ሆስኒ ሙባረክ ከስልጣን ሲወገዱ የሐገሪቱን የመሪነት ሥልጣን የያዘዉ የጦር ሐይሎች ምክር ቤት ፈርሷል።በሙባረክ ዘመን ለረጅም ጊዜ የመከላከያ ሚንስትርና የጦር ሐይሎቹ ምክር ቤት ሊቀመንበር የነበሩት ፊልድ ማርሻል መሐመድ ሁሴይን ተንታዊና ሌሎች የሙባረክ ታማኝ የጦር ጄኔራሎች በጡረታ ተገልለዋል።

አስተያየት ሰጪዉ ግን ሙርሲ ከዚሕ በላይ ማድረግ ነበረባቸዉ ባይ ናቸዉ።ሌላዉ የትርዒቱ ጎብኚ ግን ስልሳ ዘመን የተጠራቀመ ችግርን ለማቃለል አዲሱ ፕሬዝዳንት በዚሕ ጊዜ ከዚሕ በላይ ምን ያድርጉ ባይ ናቸዉ።

«በምጣኔ ሐብቱና በአገልግሎቱ መስክ፥ ለምሳሌ የማብሰያ ጋስ፥ የኤሌክትሪክ ሐይልን እጥረትና የትራፊክ መጨናነቅ ካለፈዉ ብሷል።ይሁንና ማንም ፕሬዝዳት ስልሳ ዓመት የተመሰቃቀለን ችግር በመቶ ቀናት ማቃለል አይችልም።»

አዲሱ ፕሬዝዳት ሥልጣን የያዙበት መቶኛ ቀን በተከበረ በአራተኛዉ ቀን፥ ደጋፊ ተቃዋሚዎቻቸዉ ተሕሪር አደባባይ የተደባደቡ ዕለት ሆስኒ ሙባረክ በጠቅላይ አቃቢ ሕግነት ሾመዋቸዉ የነበሩትን የሕግ ባለሙያ በቫቲካን የግብፅ አምባሳደር አድርገዉ ሾሟቸዉ።

ሙርሲ ጠቅላይ አቃቤ ሕጉን በአምባሳደርነት የመሾማቸዉ አላማ የሙባረክ ዘመን ባለሥልጣናትን ለማስወገድ የገቡትን ቃል ገቢር የማድረግ ጥረታቸዉ አካል መሆኑ አላነጋገረም።ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አብዱል መጂድ ማሕሙድ ግን ሞቼ ነዉ-ቆሜ አሉ።

«ፕሬዝዳንቱ አሁን በሥራ ላይ ባለዉ ሕገ መንግሥት መሠረት እኔን ከስልጣን ሊያስወግዱ አይችሉም።የፍትሕ ሥርዓቱን ነፃነት ለማስከበር እታገለለሁ።ሐላፊነቴንም አልለቅም።ፕሬዝዳንቱ እኔን ማባረር የሚችሉት ሲያስገድሉኝ ብቻ ነዉ።»

የግብፅ ምክትል ፕሬዝዳትና የሙርሲ የሕግ አማካሪ መሐመድ መኪ እንደሚሉት ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ በአምባሳደርነት ተሾሙ እንጂ ከስልጣን አልተሸሩም።ያም ሆኖ ጠቅላይ አቃቤ-ሕጉ በጠቅላይ አቃቤ ሕግነት የተሾሙበት ዘመን ሳያበቃ በሌላ ሹመት መቀየራቸዉን ሕጉ ሥለማይፈቅድና እሳቸዉም በመቃወማቸዉ አዲሱ ፕሬዝዳት ዉሳኔያቸዉን ሻሩ።

አል-አሕራም የተሰኘዉ የግብፅ መንግሥት የሚቆጣጠረዉ እዉቅ ጋዜጣ የሹም ሽር ዉዝግብ ፍፃሜዉን «የሕግ ሥርዓቱ በፕሬዝዳቱ ላይ የተቀዳጀዉ ድል» በማለት ዘገበ።ሌሎችም እንዲሁ።

ከሁለት ዓመት በፊት ቢሆን ኖሮ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እንዲሕ ባደባባይ ፕሬዝዳቱን ሊሞግቱ፥ መንግሥት የሚቆጣጠረዉ ጋዜጣ እንዲሕ በይፋ ሊዘግብ ቀርቶ፥ ለመሞገት፥ መዘገብ ያስባሉ ብሎ ማሰብ ሕልም በሆነ ነበር።የመገኛ ዘዴዎች ነፃነት ከተነሳ አንድ እንጨምር።

የባሕል መድሐኒት አዋቂ ነኝ ያሉ ግለሰብ የግብፅ መንግሥት ከሚቆጣጠረዉ ቴሌቪዥን ፊት ቀርበዉ የግመል ሽንት መጠጣት ለብዙ በሽታ መድሐኒት ነዉ ብለዉ ተናገሩ።ይሕን ያዩ አንድ ሐኪም የባሕል መድሐኒተኛዉን ተችተዉ ሲያበቁ፥ «አሁንስ የሙባረክ ዘመኑ ቴሌቪዥን ሳይሻል አይቀርም» አሉ።

ፕሬዝዳት ሙርሲ ሥልጣን የያዙበት መቶኛ ቀን ሲከበር ሕዝባዊ አብዮትን በመደገፍ አደባባይ በመዉጣታቸዉ፥ በአብዮቱ ወቅት ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር በመጋጨታቸዉ፥ ወይም የጦር ሐይሎች ምክር ቤትን በመቃወምና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች የታሰሩ በሙሉ በነፃ እንዲለቀቁ የምሕረት አዋጅ አዉጀዋል።

የካይሮ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም ባልደረባ መሐመድ ዛራዕ እንደሚሉት አዋጁ ለፍትሕ አንድ እመርታ ነዉ።

«ይሕ አዋጅ ወደ ፍትሐዊ ሥርዓት ለሚደረገዉ ጉዞ ጥሩ እርምጃ ነዉ።ይሁንና አሁን ማለት የምችለዉ ለመገምገም ጊዜዉ ገና ነዉ።ጥሩ ጅምር ነዉ።ለመገምገም ግን ገቢራዊነቱን ማየት እንሻለን።»

ሁሉም ሆኖ ግብፅ ባለፈዉ ሁለት ዓመት ሁሉም እንዳላት አስመሰከረች።አምባገነን ገዢን በመቃወም ጠመንጃ ከታጠቀ ጦር ጋር ለመጋፈጥ የወሰነ ቆራጥ ሕዝብ፥ ለሕባዊዉ አላማ ስኬት መስዋዕት ለመሆን የወሰኑ ጀግና ሙሕራን እና ወጣቶች እንዳሏት አሳይታለች።ፕሬዝዳንቱን በመቃወምና በመደገፍ እንደ ሥርዓተ አልበኛ ባደባባይ የሚደባደብ፥ እንደ ጨዋ በሥርዓት የሚከራከር ዜጋም አላት።ፅንፈኛ ሐይማኖተኛና ገለልተኛ፥ አክራሪ እና ለዘብተኛ ፖለቲከኛ።

የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ፕሬዝዳቱን የሚሞግቱ የሕግ ባለሙያ፥ የሕግ በላይነትን አክብረዉ ዉሳኔያቸዉን የሚሽሩ ፕሬዝዳት፥ ፕሬዝዳንቱን የሚተቹ መገናኛ ዘዴዎች፥ የፕሬዝዳንቱን አዋጅ የሚጠራጠሩ የመብት ተሟጋቾች እንደ አሸን ፈልተዉባታል።

እንደ ግብፅ የሺ ዓመታት ነፃነት እንዳላቸዉ የሚነገርላቸዉ ግን በዲሞክራሲያዉ ሥርዓት እጦት ግራ ቀኝ የሚላጉ ሐገራት ሙሑር-ልሒቃን ብዙ መናገር፥ መፃፍ፥ መተቸታቸዉ አልቀረም።ከግብፆች ተምረዉ እንደ ግብፆች መጀገን፥ መቁረጣቸዉ እሲኪታይ ግን ያዉ ይጠየቃል።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ






















Egypt's General Prosecutor Abdel Maguid Mahmoud speaks to reporters in his office in the High Court in Cairo October 13, 2012. Egypt's President Mohamed Mursi said on Thursday he was removing Mahmoud from his post, but Mahmoud has denounced the move and told Egyptian media he would stay on. Mursi had made the move to appease demonstrators who accused Mahmoud of presenting weak evidence in a case against Mubarak-era officials accused of planning attacks on protesters last year. REUTERS/Amr Abdallah Dalsh (EGYPT - Tags: POLITICS CIVIL UNREST)
አቃቤ ሕግ ማሕሙድምስል Reuters
Source News Feed: EMEA Picture Service ,Germany Picture Service An anti-Muslim Brotherhood demonstrator prepares to throw stones during clashes with supporters of the Muslim Brotherhood and Egyptian President Mohamed Mursi at Tahrir Square, the focal point of the Egyptian uprising, in Cairo October 12, 2012. Supporters and opponents of Mursi threw stones and bottles at each other, showing feelings still run high between rival groups trying to shape the new Egypt after decades of autocracy. REUTERS/ Mohamed Abd El Ghany (EGYPT - Tags: POLITICS CIVIL UNREST)
የሙርሲ ተቃዋሚምስል Reuters
Protesters try to stop the stone throwing after scuffles broke out between groups of several hundred protesters in Tahrir square when chants against the new Islamist president angered some in the crowd in Cairo, Egypt, Oct. 12, 2012. The scuffles between supporters and opponents of President Mohammed Morsi reflect deep political divisions among the country’s 82 million people, more than a year after the popular uprising that toppled Hosni Mubarak. (Foto:Khalil Hamra/AP/dapd)
የሙርሲ ደጋፊምስል AP
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ