1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግብፁ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለምክክር አዲስ አበባ ይገባሉ

እሑድ፣ ታኅሣሥ 15 2010

የግብፁ ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ሳሜሕ ሽኩሪ ከኢትዮጵያው አቻቸው ዶ/ር ወርቅነሕ ገበየሁ ጋር በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ላይ ለመምከር በሚቀጥለው ሳምንት ወደ አዲስ አበባ እንደሚያቀኑ የመስሪያ ቤታቸው ቃል-አቀባይ አረጋገጠ። የውጭ ጉዳይ ምኒስትሩ ጉብኝት ወደ ፊት መራመድ ለተሳነው የግድቡ ግንባታ ድርድር መፍትሔ ለማበጀት ነው ተብሏል።

https://p.dw.com/p/2ptxI
Ägypten Außenminister Sameh Shoukry
ምስል Getty Images/AFP/A. Schmidt

ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ በውሐ አቅርቦት ላይ ጫና ያሳድራል የሚል ሥጋት እንዳላት በተደጋጋሚ ገልጣለች።  ኢትዮጵያ በበኩሏ ታላቁ የኅዳሴ ግድብ በግብፅ ላይ የከፋ ተፅዕኖ አያሳድርም የሚል አቋም አላት። ግብፅ ፖለቲካዊ ጡንቻዋን ተጠቅማ ለሌሎች የኃይል ማመንጫ ግንባታዎች የገንዘብ ድጋፍ እንዳታገኝ የማከላከል ሥራ ሰርታለች ስትል ኢትዮጵያ ትከሳለች።

ባለፈው ጥቅምት ወር በፈረንሳይ ኩባንያ የተሰራውን የግድቡን አካባቢያዊ እና ኤኮኖሚያዊ ተፅዕኖ የሚገመግም ጥናት ለማፅደቅ የግብፅ፣ የሱዳን እና የኢትዮጵያ ልዑካን ተገናኝተው በመጀመሪያው ሪፖርት ላይ ሳይስማሙ ተለያይተዋል። የሱዳኑ የመስኖ ሚኒሥትር ሞዓታዝ ሙሳ እንደሚሉት አገራቸው እና ኢትዮጵያ በመጀመሪያው ሪፖርት ላይ ሊደረግ ይገባል ያሉትን ማሻሻያዎች ግብፅ ለመቀበል ፈቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች።

ኢትዮጵያ እና ሱዳን በበርካታ ጉዳዮች ላይ በተለይም ግድቡ የሚያስከትለውን ተጽእኖ ለሚመዝነው ጥናት መነሻ ይሁን ተብሎ በቀረበው ሐሳብ ላይ ያላቸውን ቅሬታ መግለጣቸውን ሚኒሥትሩ አክለው ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በውሐ ፍሰት ላይ የሚደረገው ድርድር ሳይቋጭ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ ያላት ፍላጎት ሌላው ያልተስማሙበት ጉዳይ ነው።

የአረብ የውሐ ምክር ቤት ሊቀ-መንበር እና የቀድሞው የግብፅ የመስኖ ሚኒሥትር ማሕሙድ አቡ ዛይድ ኢትዮጵያውያኑ "በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ውይይት እየተደረገ ሳለ ግድቡን ውሐ መሙላት እና ግንባታውን ማጠናቀቅ ሳይፈልጉ አይቀርም ብለን እናምናለን" ሲሉ ጥርጣሬያቸውን ገልጠዋል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴር ቃል-አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ባለፈው ወር የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ "ማንም ወገን ሊያስቆመው የሚችል ፕሮጀክት አይደለም" ብለው ነበር። 

እሸቴ በቀለ

ተስፋለም ወልደየስ