1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግሪክ ወቅታዊ ሁኔታ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 14 2004

የህዝብ አስተያየት መመዘኛ እንደሚጠቁመው ባለፈው ምርጫ 16.78 ከመቶ ድምፅ ያገኘው የአሌክሲስ ሲፕራስ ፓርቲ በመጪው ምርጫ ጠንካራ ፓርቲ ሆኖ መውጣቱ አይቀርም ። እንደውም ፓርቲው የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ሥልጣን የመያዝ ጉጉት ነው ያለው ።

https://p.dw.com/p/150Fz
ምስል Reuters

የግሪክ የገንዘብ ቀውስና መፍትሄውዓለምን በተለይም የአውሮፓ ህብረት አባላትን አሁንም ማነጋገሩን ቀጥሏል ።ካለፈው የምክር ቤት ምርጫ በኋላም በግሪክ ሁኔታዎች በፍጥነት እየተለዋወጡ ነው ። የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን በግሪክን ወቅታዊ ሁኔታና በአውሮፓ ህብረት አቋም ላይ ያተኩራል ።
የግሪክ የገንዘብ ቀውስ በዓለም ዓቀፍ የገንዘብ አባዳሪ ተቋማትና በአውሮፓ ህብረት ብድርና እርዳታ ለጊዜውም ቢሆን መፍትሄ ያገኘ መሶሎ የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ሌሎች ችግሮች እየተከሰቱ ነው ። ከ 2 ሳምንት በፊት በተካሄደ የግሪክ ምክር ቤት ምርጫ የአውሮፓ ህብረትን የቁጠባ አሰራር የሚቃወሙ ፓርቲዎች ከፍተኛ ድምፅ ማግኘታቸው የአውሮፓ ህብረትና ግሪክ የተስማሙበትን የብድር ና የእርዳታ ውል ተግባራዊነት አጠያያቂ አድርጎታል ። የህዝቡን ስሜት ያንፀባረቀው የዚህ ምርጫ ውጤት ብዙ ለውጦችን አስከትሏል ። በግሪክ በተካሄደው የፓርላማ ምርጫ ፣ አዲስ ዲሞክራሲ የተሰኘው ወግ አጥባቂ ፓርቲና የሶሺያል ዲሞክራቱ ፓርቲ ፓሶክ ጥምረት፣ በሚያራምዱት የቁጠባ መርኀ ግብር ሳቢያ ህዝብ ድምጹን ነፍጓቸው መንግሥት ለማስተዳድር የሚያስችል በቂ ድምፅ አላገኙም ። የቁጠባ እርምጃ ተቃዋሚ የሆኑት የግራ ፅንፈኞች ህብረት እንዲሁም ኮሙዩኒስቶችና የቀኝ አካራሪ ኃይሎች ከዚህ በፊት ያላገኙትን ድምፅ ነበር ያፈሱት ። በዚህ ሰበብም አብላጫን ቁጥር ያገኘው ኒው ዲሞክራሲና ሶሻል ዲሞክራቱ ፓስኮ ከተቃዋሚዎች ጋራ ተጣምረው መንግሥት ለመመሥረት ቢሞክሩምም ሳይሳካ ቀርቶ 2ተኛ ዙር ምርጫ ለሰኔ 10 ፣ 2004 ዓም ተጠርቷል ። እስከዚያው ድረስም ግሪክ ፤ በፓናጊዮቲስ ፒክራሜኖስ የበላይ ነት በተመሰረተ የሽግግር መንግሥት ከ 5 ቀናት አንስቶ እየተመራች ነው ፤ ሚያዝያ 28 ቀን 2004 በተካሄደው የምክር ቤት ምርጫ ፤ መንበር ያገኙት የህዝብ እንደራሴዎችም ቃለመሃላ ፈፅመው ስራ ቢጀምሩም የምክር ቤት ቆይታቸውን የሚወስነው ከ3 ሳምንት በኋላ እንደገና የሚካሄደው አዲስ የፓርላማ ምርጫ ይሆናል ።
የመጪው ምርጫ ውጤት እንደ መጀመሪያው ተመሳሳይ ሆኖ አሁንም ሃገሪቱ የተደላደለ አስተዳደር መመስረት የሚችል መሪ እንዳታጣ የሚሰጉ አሉ ። የወግ አጥባቂዎች የፖለቲካ ጉዳዮች አጥኚ ማኖሊስ ኮታኪስ ይህ እንዳይደገም ፓርቲዎች መጠንቀቅ እንደሚገባቸው ያሳስባሉ ። እንደርሳቸው የግሪክ ፓርቲዎች በሃገሪቱ ወቅታዊ ችግሮች ላይ ግልፅ አቋም ሊኖራቸው ይገባል ፤ መፍትሄም ይዘው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል። « ባለፈው ጊዜ ዋናው ጥያቄ የታወቁት ና የተለመዱት ፓርቲዎች ለዛሬው የኤኮኖሚ ድቀት መቀጣት አለባቸው ወይስ የለባቸውም የሚል ነበር ። የሃገሪቱን ወቅታዊ ተጨባጭ ችግር በተመለከተ በርግጥ እስካሁን ተገቢ ክርክር አልተካሄደም ። መጪው ምርጫ የሚከናወነው የተለዩ ምልክቶች ይዞ ነው ። ፓርቲዎቹ በአሁኑ ጌዚ ግልፅ የሆነ አቋም በመያዝ በተጨባጭ ሁኔታ መፍትሄ እንደሚያገኙ ምልክት ማሳየት አለባቸው »
ታዋቂ የግሪክ የፖለቲካ ጋዜጠኛ ባቢስ ፓፓፓናዮቱ በቀጣዩ አዲስ ምርጫ እንዲሁ የተቃወሞ አካሄድና ማግለል ይንፀባረቃል ተብሎ አይጠበቅም ይላል ። ጋዜጠኛው አልፋ በተባለው የተሌቪቭን ጣቢያ እንደተናገሩት ዜጎች የተጠየቁት ሃገሪቱ በአውሮፓ ህብረት ውስጥ ስላላት የወደፊት መፃኤ እድል እንዲያረጋግጡ ነው ።
«በመጪው ምርጫ በግልፅ 2 የተለያዪ አካሄዶች መከሰታቸው የማይቀር ነው ለአውሮፓና ለዩሮ መቆም ወይም ደግሞ ሌላ መንገድ መከተል ። በበኩሌ በዚህም ላይ በታወቁት የቀኝ ማዕከል ወግ አጥባቂ ፓርቲዎችና ግራ ዘመም ፓርቲዎች ፊት ለፊት ገጥመው እንደሚከራከሩ እጠብቃለሁ ። ግር ዘመሞቹ በአሁኑ ጊዜ እንደተለመደው በሶሽያሊስቶች መመራታቸው ቀርቶ አክራሪ የግራ ፈልግ ተከታዩ ፓርቲ ሲሪዝያ ነው የሚያሾራቸው ። ስለሆነም ክርክሩ የተጋጋለ ነው የሚሆነው »
ባለፈው ምርጫ የግራ አክራሪዎቹ ፓርቲ መሪ አሌክሲስ ሲፕራስ 16.78 ከመቶ ድምፅ በማግኘት በፓርላማው 52 መናብርት ለመያዝ መብቃታቸው የሚታወስ ነው ።የህዝብ አስተያየት መመዘኛ እንደሚጠቁመው የርሳቸው ፓርቲ አሁንም ይህንኑ በመድገም ጠንካራ ፓርቲ ሆኖ መውጣቱ አይቀርም ። እንደውም ፓርቲው የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ሥልጣን የመያዝ ጉጉት ነው ያለው ። በምርጫ ዘመጫ ወቅት ግሪክ የዩሮ ተጠቃሚ አባል ሃገራት ማህበር አባል ሆና እንድትቀጥል ሆኖም የቁጠባ እርምጃውንና እዳዋን ላለመቀበል ነው ቃል የገቡት ። ይህን የመሰለውን የምርጫ ቃል በመግባት ነበር ሲፕራስ የተቆጡ መራጮችንና የምጣኔ ሃብት ቀውስ ሰለባዎች የሆኑትን መሳብ የቻሉት እነዚህ ሰዎችም በበኩላቸው ከእንግዲህ ምንም የምናጣው የለም የሚል አስተያየት ነው ያላቸው ። የምጣኔ ሃብቱ ምሁር ሚሻሊስ አርጊሩ እንደሚሉት እንዲያውም እነዚህ ሰዎች በግራ ፈለግ ተከታዮች አመራር የኑሪ ደረጃችን ከፍ ይላል ብለው የሚያስቡ ሰዎች ናቸው።
«የግራው ፓርቲ የምጣኔ ሃብት መርሃ ግብር በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አዲስ መመሪያ እንደሚኖር ነው የሚገልፀው ። ማንኛውም ነገር በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ይሆናል የተሃድሶ ለውጥ የሚባልም አይኖርም ። በተለይ እኝሂ ፖለቲከኛ ወጣትና ተአምር ሊሰሩ እንደሚችሉ የሚታሰቡ አንዳች አማራጭ ሃሳብ ሊቀርቡ አለመቻላቸው በርግጥ ያሳዝናል ። ከዚህ በፊት እንደነበረው በዛው መቀጠል ነው የሚሹት ። እጎአ በ 2009 ዓም ወደነበረው ሁኔታ በመመለስ አሁን ለደጋፊዎቻቸው ፍጹም ተግባራዊ ሊሆን የማይችለውን ነገር ተግባራዊ እናደርጋለን ነው የሚሉት ።»
ግራ አክራሪው አሌክሲስ ሲፕራስ ግሪክ ከዩሮ ማህበር ሳትወጣ የህዝቡን ኑሮ ካመሰቃቀለበት የቁጠባ እርምጃ ነፃ ለማውጣት ቃል ቢገቡም ይህ ግን እንዴት ተግባራዊ እንደሚያደርጉት ለማንም ግልፅ አይደለም ። ለማንኛውም በመጪው የምክር ቤት ምርጫ እንደገና በአሸናፊነት ብቅ ማለታቸው እንደማይቅር የሚጠበቀው ሲፕራስ በመላ ሃገሪቱ «ከዚህ በላይ አንከፍልም » የሚለውን መፈክራቸውን ደጋግመው ማሰማታቸውን ቀጥለዋል ። በተለይም ቁጠባው በጅርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ነው የተጫነብን የሚሉት ሲፕራስ እኔን ምረጡኝ እንጂ የአሁኑ ማስፈራራያ የትም አይደርስም ፣ እዳችንን ባንከፍል እንኳን የአውሮፓውያን እርዳታ አይቋረጥም ሲሉ ነው ህዝቡን የሚቀሰቅሱት ። በበዙዎች እምነት የርሳቸው ፓርቲ መፍትሄ የሚለውአንዳችም ነገር አልያዘም ። ይሁንና ህዝብ ድምፁን የሚሰጠው ሌላ አመራጭ ስለሌለው ሰኔ 10 ማድረግ የሚችለው አለመቀበልና መቃወም ብቻ መሁኑን ነው አስተያየት ሰጭዎች የሚናገሩት ። አውሮፓ ግን ህዝቡ ለቀደሙት በኢቫንገሎስ ቬኒዜሎስ ለሚመራው ለሶሻሊስቶቹ ና ለእንቶንዮስ ሳማራስ ፓርቲው ለወግ አጥባቂዎቹ ድምፅ እንዲሰጥ ነው የሚፈልገው ። ምክንያቱም እነዚህ ፓርቲዎች የብድሩን ስምምነትና ቅድመ ግዴታዎቹን ተቀብለዋልና ። አሁን ግን ለግሪኮች በቸኛው አማራጭ ሲፕራስ ሆነዋል ። የ38 ዓመቱ ሲፕራስ በግሪክን ፖለቲካ ውስጥ ረዥም ጊዜ ካስቆጠሩት የተለመዱት ፖለቲከኞች ጋር ሲነፃፀሩ ወጣት ናቸው ። በህዝብ ዘንድ ተመራጭ ያደረጋቸው የገቡት ቃል ብቻ አይደለም ። የኑሮ ሁኔታቸውም ጭምር እንጂ ። የፖለቲከኛው ሲፕራስ ገቢ በዓመት 48, 000 ዩሮ ወይም 61,000 ዶላር ነው ። ባለ ሞተር ሳይክል ሲሆኑ ቤታቸውም መካከለኛ የሚባል ነወ ። ከሌሎቹ የግሪክ ፖለቲከኞች ጋር ሲነፃፀር ድሃ የሚባሉ ዓይነት ናቸው ። በዚህና በሌሎችም ምክንያቶች የህዝብ ድጋፍ ያገኙት ሲፕራስ ህዝባቸውን በልዩ ልዩ ማማለያዎች ወደር ሳቸው ቢያስጠጉም እውነታው ግን ግሪክ የዩሮ አባል ሆኖ መቀጠል ከፈለገች ከዚህ ቀደም የተስማማችባቸውን ቅድመ ግዲታዎች መፈፀም አለባት ። ይህንንም የአውሮፓ መሪዎችና የአውሮፓ ህብረት ባለሥልጣናት ደጋግመው እያሳሰቡ ነው ። ከነዚህም አንዷ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ናቸው ። ሜርክል አርብና ቅዳሜ ከተካሄደው ከካምፕ ዴቪዱ የቡድን 8 ጉባኤ በኋላ በሰጡት መግለጫ ይህንኑ ጉዳይ አንስተውት ነበር ።

« በውይይቱ የተሳተፉት ሁሉም የቡድን 8 አባል ሃገራት ግሪክ የዩሮ ሸርፍ አባል ሃገራት ተጠቃሚ ማህበር ሆና እንድትቀጥል ይፈልግሉ ። ይሁን እንጂ ግሪክ በተደረገው አጠቃላይ ስምምነት የገባቻቸውን አጠቃላይ ግዴታዎች መፈጸም ይኖርባታል ። »
በሌላ በኩል የአውሮፓ ህብረት ይህን ሁሉ ውዝግብ ያስከተለችውን ግሪክን ከዩሮ ማህበር ሊያስወጣ ነው የሚል ወሬም ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ አካባቢ ሲናፈስ ነበር ። በተለይ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ብራሰልስ ውስጥ የመከሩት የገንዘብ ሚኒስትሮች ይህን ጉዳይ ማንሳታቸው ቢወራም ህብረቱ ግን በፍፁም ይህ አልሆነም ሲል አስተባብሏል ። አንዳንድ የህብረቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ግሪክ ዩሮን ለቃ እንደምትወጣ የሚያመለክቱ አስተያየቶች ሰጡ መባሉን የዩሮ ቀጣና አባል ሃገራት ማህበር የገንዘብ ሚኒስትሮች የበላይ ተጠሪ ጆን ክሎድ ዩንከር ውድቅ አድረገዋል ። ዩንከር ግሪክ ትወጣለች መባሉን ትርጉም የማይሰጥ ፕሮፖጋንዳ ሲሉ ነበር ያጣጣሉት ። እንደ ዩንከር የማህበራቸው ፍላጎት ከሚናፈሰው ወሪ የተለየ ነው
« የማይናጋው ፍላጎታችን ግሪክ የዩሮ ተጠቃሚዎች ማህበር አባል ሆና እንድትቆይ ነው ። ይህን ለማሳካት የተቻለውን ሁሉ እንደርጋለን ። የግሪክ ከዩሮ መውጣት መነጋገሪያችን አልነበረም ። »
ያም ሆኖ ዩንከር ባለፈው ሳምንቱ ጉባኤ ላይ ለግሪኩ የገንዘብ ሚኒስትር በግሪክ ጉዳይ ላይ ድምፅ ቢሰጥ ውጤቱ አሰቸጋሪ እንደሚሆን ከማስጠንቀቅ አልተቆጠቡም ።የአውሮፓ ህብረት የቁጠባ እርምጃዎች የተቀበሉት ፖርቱጋልና አየርላንድን የመሳሰሉት አገራትም በአቴንስ መንግሥት ላይ ከባድ ትችት መሰንዘራቸው ነው የተሰማው ። በነርሱ አባባል ህብረቱ ያሰቀመጣቸውን መመሪያዎች ተግባራዊ ለማድረግ እየታገሉ ግሪክ ግን በተደጋጋሚ የተሃድሶ እርምጃዎች መጣሷና ተቀባይነት የለውም ። እነዚህ ሃገራትና ሌሎችም ሚኒስትሮች ግሪክ በእሳት ላይ ቤንዚን ጨምራ በተደጋጋሚ በምታሳየው ቸልተኝነት ሌሎች የዩሮ ማህበር አባላትም በእሳቱ እንዲያያዙ በማድረግ ሃላፊነትዋን እየተወጣች አይደለም ሲሉ ወቅሰዋል ። ሆኖም የአውሮፓ ህብረት ግሪክም ሆነችም የተቀሩት የህብረቱ አባል ሃገራት ከዚህ ቀደም ለገቡት ቃል ተገዥ መሆናቸው ወሳኝነት እንዳለው ደጋግመው ማንሳታቸው አልቀረም የአውሮፓ ህብረት የምጣኔ ሃብት ኮሚሽነር ኦሊ ሪን የግሪክና የህዝቧ እጣ ፈንታ በግሪክ ፓለቲከኞች ጫንቃ ላይ ወድቋል ሲሉ የፖለቲከኞች ሚና ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ አውስተው ነበር ። ሬን እንደሚሉት ሃገሪቱ ከገባችበት ችግር እንድትወጣ የተደረሰበት ስምምነት የሚመለከተው ግሪክን ብቻ ሳይሆን የተቀሩትን የዩሮ ተጠቃሚ ሃገራትንም ጭምር ነው።
« ትብብሩ ባለ ሁለት መንገድ ነው ። 16ቱ የዩሮ ተጠቃሚ አባል ሃገራትና ግሪክ እንዲሁም መንግሥታቶቻቸው የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ ጥሪ የሚያደርግ ስምምነት ነው ። »
የህብረቱ ባለሥልጣናት ግሪክ ከዩሮ አትወጣም ሲሉ ደጋግመው ለማሳመን ቢሞክሩም አሁንም ጥርጣሪው አልተነሳም ። በ ቡድን 8 ጉባኤ ላይ የተሳተፉት የህብረቱ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆሴ ማኑዌል ባሮሶ ለግሪክ የተያዘ ሁለተኛ እቅድ ካለ ተብለው ሲጠየቁም አስተባብለዋል ።
« በሁለተኛ እቅድ ላይ አስተያየት አንሰጥም ። በአንደኛው እቅድ ላይ ነው። በመሥራት ላይ ያለነው መሠረታዊ መመሪያችን ይህን ነው ለአንደኛውና ለአንደኛው እቅድ ብቻ ነው የምንሰራው ። ይህም ግሪክ በዩሮ አባልነትዋ እንድትቆይና የገባችውን ግዴታ እንድትፈፅም ነው ።እርግጥ ሌሎች አባል መንግሥታትም ሁሉ ይህን የገባችውን ቃል እንዲያከብሩላት ነው ። »
የአውሮፓ ህብረት ባለሥልጣናት ማስተባበያ ከየአቅጣጫው በሚሰማበት በዚህ ወቅት ላይ ከዚህ ቀደም አይሆንም የተባለ ምርጫ ለግሪክ ህዝብ የማቅረብ ሃሳብ መኖሩም ተሰምቷል ። አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚሉት ከሆነ ጀርመን በግሪክ የዩሮ አባልነት መቀጠል አለመቀጠል ላይ ህዝበ ውሳኔ እንዲሰጥ ትፈልጋለች ።
ይህን ሃሳብ የቀድሞው የግሪክ ጠቅላይ ሚኒስትር ጊዮርጊዮስ ፓፓንድሪው አቅርበው ህብረቱ ሳይቀበላቸው ቀርቷል ። ህዝበ ውሳኔው አሁን እንደገና የተነሳው ህዝቡ ዩሮን ከተቀበለ የተቀመጡትን ቅድመ ግዴታዎችን መቀበሉን ያረጋግጣል ከሚል ሃሳብም የመነጨ መሆኑ ነው የተወሳው ። የዩሮ አባል ሃገራት ግን የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል አቀረቡት በተባለው በዚህ ጉዳይ ላይ በይፋ ያሉት ነገር የለም ። ጀርመንም ይህን አስተባብላለች ። የህዝበ ውሳኔውን ሃሳብ የጀረመን የገንዘብ ሚኒስትርም ማንሳታቸው ተዘግቧል ። ከግሪክ በኩል እንደተሰማው ግን ሜርክል ይህንኑ ሃሳብ ከጊዜያዊው ለጠቅላይ ሚኒስትር ፓናጊዮቲስ ፒክራሜኖስ አርብ ማታ በስልክ ባነጋገሩዋቸው ወቅት እንዳነሱላቸው ተረጋግጧል ። የግሪክ የወደፊት እጣ ፈንታ ወሳኙ ህዝበ ውሳኔው ውይስ መጪው ምርጫ ። ወደፊት የሚታይ ይሆናል ።

Griechenland Panagiotis Pikrammenos
ምስል Reuters
Parlament Athen Griechenland
ምስል dapd
SYMBOL Ein Mann schwenkt am Syntagma-Platz in Athen die griechische Flagge
ምስል dapd
Griechenland Parteien treffen sich mit Präsident Karolos Papoulias
ምስል dapd
PK in Paris Alexis Tsipras
ምስል dapd
Fitch Griechenland
ምስል AP

ሂሩት መለሰ
ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ