1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግሪክና የአበዳሪዎቿ ውዝግብና የህዝበ ውሳኔው ፋይዳ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 23 2007

ግሪክ ከአበዳሪዎቿ የምትጠብቀው ገንዘብ ሊለቀቅ የሚችልበት የመጨረሻው ቀን ሊያበቃ ጥቂት ሰዓታት ቀርተዋል ። ግሪክን ለመታገድ ተግባራዊ በሆነው የብድርና እርዳታ መርሃ ግብር መሠረት ሃገሪቱ ከወሰደችው ገንዘብ የተወሰነውን እዳዋን መክፈያው ቀነ ገደብም እንዲሁ።

https://p.dw.com/p/1Fqsc
Griechenland Athen Schuldenkrise
ምስል picture-alliance/AP Photo/P. Giannakouris

የግሪክና የአበዳሪዎቿ ውዝግብና የህዝበ ውሳኔው ፋይዳ

አበዳሪዎች በመርሃ ግብሩ መሠረት ሊሰጧት ያቀዱትን ቀሪ 7.2 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 8.1 ሚሊዮን ዶላር በከለከሏት በግሪክ የገንዘብ ቀውስ ተባብሶ ባንኮች ከትናንት አንስቶ ለአንድ ሳምንት ተዘግተዋል ። ከባንክ ውጭ ገንዘብ የሚወጣባቸው የATM ማሽኖችም እንዲሁ ከ60 ዩሮ በላይ እንዳይሰጡ ተደርጓል ። በርሊን ነዋሪ የሆኑት የኤኮኖሚ እድገት መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የኤኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ ዶክተር ፈቃዱ በቀለ መንግሥት እርምጃውን የወሰደው በሃገሪቱ በተከከሰተው የገንዘብ እጥረት ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ ። ዶክተር ፈቃደ እንደሚሉት ባንኮች ቢዘጉም በሃገሪቱ ገንዘብ የሚተላለፍባቸው ሌሎች መንገዶች አሉ ።
አበዳሪዎች የግሪክ መንግሥት ተግባራዊ እንዲያደርግ አጥብቀው በሚሞግቱት የቁጠባ እርምጃዎች ላይ ህዝቡ ድምጽ እንዲሰጥ ለፊታችን እሁድ ተጠርቷል ። ይህ ያልተጠበቀ የግሪክ መንግሥት እርምጃ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራትን በተለይም የዩሮ ተጠቃሚዎችን አደናግጧል ። ግሪክ የተጣለባትን አስገዳጅ የቁጠባ መርሃ ግብር አስቀራለሁ ሲል ቃል ገብቶ ባለፈው ጥር ሥልጣን ላይ የወጣው ግራ ዘመሙ የግሪክ ፓርቲ ሲሪዛ ህዝቡ አበዳሪዎች በጠየቋቸው የተሃድሶ እርምጃዎች እንዳይስማማ እየሳሰበ ነው ። የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ ግሪካውያን አበዳሪዎች ያቀረቧቸውን የማሻሻያ ሃሳቦች በመደገፍ ድምፁን በመስጠት ሃገሪቱ ከዩሮ ማህበር ጋር እንድትቀጥል ያደርጉ ዘንድ ተማፅኗል ። ከወዲሁ እንደሚታየው ግን የግሪክ ህዝብ ፍላጎት አንድ አይመስልም ይላሉ ዶክተር ፈቃደ ።የግሪክ ህዝብ አበዳሪዎች ተግባራዊ ይሁን የሚሉትን የቁጠባ እርምጃ መቀበል አለመቀበሉ በመጪው እሁድ ህዝበ ውሳኔ ይታወቃል ። ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ግን አስቸጋሪ ሆኖ ነው የተገኘው ።ያም ሆኖ ምናልባት የህዝበ ውሳኔው ውጤት እሺታ ቢሆን ምን ሊከተል ይችል ይሆን ?
በአንፃሩ ውጤቱ እምቢታ ቢሆንስ ?
ግሪክ ከዩሮ አባልነት ብትወጣም በሌሎቹ የማህበሩ አባላት ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ እንደማይኖር ነው የሚነገረው ። ይሁንና የግሪክን ችግር መፍታት አለመቻል ለመላው አውሮፓ አደጋ የመሆኑ ስጋት አለ ። ለግሪክ ብዙ ብድር ከሰጡት ሃገራት አንዷ የሆነችው የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ለግሪክ ችግር አግባባቢ መፍትሄ ከጠፋ ለአውሮፓ ውድቀት ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል ። ዶክተር ፈቃደ ስጋቱና ማስጠንቀቂያው መሠረታዊ ምክንያት አለው ይላሉ ።
ግሪክን መርዳት ከተፈለገ አሁን ከተጀመረው መንገድ የተለየ አማራጭ መፍትሄ ማግኘቱ አይገድም እንደ ዶክተር ፈቃደ ። በርሳቸው አስተያየት ባንኮችን እስከማዘጋት ለደረሰው ለግሪክ የገንዘብ ችግር ጀርመንና ፈረንሳይ ከመሳሰሉ ጠንካራ ኤኮኖሚ ካላቸው የዩሮ ተጠቃሚ ሃገራት በኩል ችግሩን ሊያቃልል የሚችልመፍትሄ ሊገኝ ይችላል ።
የግሪክና የአበዳሪዎቿ ውዝግብ መፍትሄ ባያገኝም ዶክተር ፈቃደ እንደሚሉት ግሪክ ምናልባት ከዩሮ ማህበር ለቃ የምትወጣ ቢሆን እንኳን በሌላ መንገድ እርዳታ የምታገኝበት መንገድ እየተጠና ነው ።

Griechenland Athen Schuldenkrise Vorbereitungen Referendum
ምስል picture-alliance/dpa/S. Pantzartzi
Griechenland Athen Schuldenkrise Drachme
ምስል picture-alliance/dpa/F. Gambarini

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ