1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋዜጠኞች፤ የድረገጽ ጸሐፍትና ተማሪዎች መፈታት

ሐሙስ፣ ሐምሌ 2 2007

የኢትዮጵያ መንግሥት ዉጪ ከሚገኙ አሸባሪዎች ጋር አብራችሁ ሐገሪቱን ለማሸበር አቅዳችኋል በሚል ክስ አስሯቸዉ ከነበሩ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን መካካል አምስቱን መፍታቱ ተረግግጧል። ሶስቱ ጋዜጠኞችና ሁለቱ ጦማሪያን የተፈቱት አቃቤ ሕግ ክሱን በማቋረጡ እንደሆነ ጠበቃቸው ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/1Fvri
Addis Ababa (Äthiopien)
ምስል picture alliance/landov

[No title]


በተያያዘ ዜና በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ላይ በተደረገ ተቃውሞ ታስረዉ የነበሩ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች መካከል የተወሰኑት መፈታታቸው ተሰምቷል።

መጀመሪያ ከአዲስ አበባ ተነስቶ በማህበራዊ ድረ-ገጾች የተዛመተ ጭምጭምታ ነበር። በእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ መስርቶባቸው በእስር ላይ ይገኙ ከነበሩት ሶስት ጋዜጠኞች እና ስድስት የድረገጽ ጸሐፍት መካከል የተስፋለም ወልደየስ፤ አስማማው ሃይለጊዮርጊስ እና ዘላለም ክብረት መፈታት። ክሚያዝያ 2006 ጀምሮ የታሰሩት የድረገጽ ጸሐፍትና ጋዜጠኞችን መፈታት ለዶይቼ ቨሌ ያረጋገጡት የተከሳሾች ጠበቃ አምሐ መኮንን በቀሪዎቹ አራት ተከሳሾች ላይ ግን የተለየ ትዕዛዝ አለመኖሩን ተናግረዋል።

«አቃቤ ህግ በሕግ በተሰጠው ስልጣን መሰረት በእነዚህ አምስት ተከሳሾች ላይ ክሴን አቋርጫለሁ የሚል ማመልከቻ ለፍርድ ቤቱ ስላቀረበ ፍርድ ቤቱም በዚሁ መሰረት ተከሳሾቹ ለሚገኙበት ማረሚያ ቤቶች ተከሳሾቹ በሌላ ጉዳይ የማይፈለጉ ከሆነ ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ በመስጠቱ በዚህ ምክንያት ነው ተፈተው ያሉት። በሌሎቹ ተከሳሾች ላይ ግን እስካሁን የተለየ ነገር አልሰማንም። እነሱም እስካሁን አልተፈቱም።

Symbolbild Blog Blogging Internet
ምስል Fotolia/Claudia Paulussen

‘የሽብር ተግባርን ማቀድ ማሴር ማነሳሳትና መፈጸም’ እና ‘ህገ መንግሰታዊ ስርአቱን በሃይል መናድ‘ የሚሉ የህግ አንቀጾች ተጠቅሶባቸው በእስር እና የክስ ሂደት ላይ ከከረሙት ጦማሪያን መካከል አጥናፍ ብርሃኔ፤ ናትናኤል ፈለቀ፤አቤል ዋበላ እና በፍቃዱ ሃይሉ አሁንም በእስር ላይ ናቸው። ጠበቃ አምሐ መኮንን «ክሱ በግብረ አበርነት የተፈጸመ ነው ከተባለ ሁሉም ተከሳሾች ላይ ተመሳሳይ ውሳኔ መሰጠት ነበረበት የሚል እምነት አለን ።»ሲሉ ይሞግታሉ።

የጋዜጠኞቹ እና ጦማሪያኑ ዘመድ፤ ወዳጅና የሥራ ባልረቦች በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ደስታቸዉ እየገለጡ ነዉ።ሐገር ዉስጥም ዉጪም የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን የኢትዮጵያ መንግስት አሁንም በእስር ላይ የሚገኙትን ቀሪ ጦማሪያን እና የህሊና እስረኞች በሙሉ እንዲፈታ ውትወታቸውን ቀጥለዋል። የኢትዮጵያን መንግስት ውሳኔ በይሁንታ የተቀበለው በምህጻሩ (CPJ) በመባል የሚታወቀው የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅትም፤ አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ ተጨማሪ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል። በተመሳሳይ ክስ ማረሚያ ቤት የሚገኙት አራቱ ጦማሪያን ግን ሐምሌ 13/2007 ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ጠበቃ አምሐ መኮንን ተናግረዋል።

At Smybol
ምስል Fotolia/lichtmeister

በተያያዘ ዜና ከአንድ አመት በፊት የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ላይ በተነሳ ተቃውሞ ከታሰሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች መካከል ስድስቱ መፈታታቸውን አዲስ ስታንዳርድ የተሰኘ የኢትዮጵያ መጽሄት ዘግቧል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ጋር ያስተሳስራል የተባለው እቅድ ለህዝብ ይፋ ሲሆን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተነሳው ተቃውሞ አስራ አንድ ሰዎች መሞታቸውንና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ለእስር መዳረጋቸውን ዘገባው ጨምሮ ገልጿል።

ከጋዜጠኞቹና ከድረገጽ ጸሐፍቱ በተጨማሪ የአዲስ አበባን አዲስ ፕላን በመቃወማቸዉ ከታሰሩት መካከል ቢያስ ስድስቱ መፈታታቸዉ ተዘግቧል።ድንገተኛው የእስረኞች ፍቺ በበርካቶች ዘንድ የተለያየ ትርጉም የተሰጠው ሲሆን ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝት ጋር ያገናኙት በርካቶች ናቸዉ።

እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ