1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋና ፕሬዝደንት ድንገተኛ ሞት

ረቡዕ፣ ሐምሌ 18 2004

የጋናዉ ፕሬዝደንት ድንገት ከዚህ ዓለም በሞት መለያታቸዉ የተሰማዉ ትናንት ማምሻዉን ነዉ። ፕሬዝደንት ጆን አታ ሚልስን ሳይታሰብ ለህልፈት ያበቃቸዉ ምክንያት በይፋ ባይገለፅም፤ በቅርቡ የተለመደ የህክምና ምርመራ ለማድረግ ወደዩናይትድ ስቴትስ ተጉዘዉ እንደነበር ግን ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/15ecm
ጆን ድራማኒ ማሐማምስል Reuters
Ghana Präsident Atta Mills gestorben
አታ ሚልስምስል Reuters

 የሀገር ዉስጥ የመገናኛ ብዙሃን ግን የጉሮሮ ካንሰር ሲያሰቃያቸዉ እንደቆየ ዘግበዋል። የእሳቸዉ ሞት በተረጋጋ የፖለቲካ ይዞታዋ የምትታወቀዉን ሀገር ወዴት ሊወስዳት እንደሚችል ከወዲሁ ማነጋገር ሲጀምር፤ ህልፈተ ህይወታቸዉ በተሰማ በሰዓታት ዉስጥ ምክትላቸዉ ሥፍራዉን መያዛቸዉ ነዉ የተሰማዉ። ጆን ኢቫንስ አታ ሚልስ ህይወታቸዉ ባለፈባት በሐምሌ ወር በጎርጎሮሳዊዉ የዘመን ቀመር በ21ኛዉ ቀን 1944ዓ,ም ነዉ በጋራ ምዕራባዊ ግዛት ታርዋካ በተባለች ስፍራ የተወለዱት። ቅዳሜ ዕለት 68ኛ ዓመታቸዉን ያከበሩት አታ ሚልስ በያዙት የፕሬዝደንትነት ስልጣን ለመቀጠል ታህሳስ ላይ በሚካሄደዉ ምርጫ ዳግም ለመወዳደር ተዘጋጅተዉ ነበር።

ብዙም ሳይሰማላቸዉ በዝምታ ሲያስታምሙት የከረሙት ህመም ግን ለዚህ ቀጠሮ አለበቃቸዉም፤ ከአምስት ወራት አስቀድሞ ነጠቃቸዉ እንጂ። ሞታቸዉ ጋናዎችን አስደንግጧል፤

«በጣም አዝኛለሁ፤ አዘዉትሬ እከታተላቸዉ ነበር፤ ሆኖም በጣም ጥሩ ሰዉ ነበሩ።»

ጋናዊቱ የፕሬዝደንቱን ሞት ሲሰሙ፤

«አሳዛኝ ዜና ነዉ፤ ታዉቃለህ ሰዉየዉ ትሁት ሰዉ ነበሩ፤ ጥሩ ሰብዕና ያላቸዉ ሰዉ ነበሩ፤ ሁሉም ያደንቃቸዋል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ደግሞ የተሻለዉን ያዉቃል፤ እኛ ልናደርግ የምንችለዉ ነገር አይኖርም።»

 መልካም ሰብዕናቸዉን እኝህ ብቻም አይደሉ የገለፁላቸዉ፤ እኝህም ይህን ነዉ ያሉት፤

«በትሁት ሰብዕናቸዉ አስታዉሳቸዋለሁ፤ በህግ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ቢኖራቸዉም አይኮሩም ነበር፤ እንዲህ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ምናልባት አለሁ አለሁ ሊሉ ይችላሉ፤ እሳቸዉ ግን ሁልጊዜ ትህትና የተላበሱ ነበሩ፤ የሚከበሩ ሰዉ ናቸዉ።»

ጋናዉያን ድንገት በሞት ስላጧቸዉ ፕሬዝደንት ጆን አታ ሚልስ የሰጡት አስተያየት ነዉ።

 «በጣም ነዉ ያዘንኩት፤ በጣም ጥሩ ሰዉ ነዉ ያጣነዉ፤ በእርግጥ በጣም ጥሩ ሰዉ።»

Ghana John Atta Mills Präsident
ምስል picture alliance / dpa

ጋና ዛሬ ላለፉት አራት ዓመታት በፕሬዝደንትነት ለመሯት ሚልስ ስትተክዝ ስታነባ አርፍዳለች። በህገ መንግስቱ መሠረት ፕሬዝደንቱ በሞት ሲለይ ወዲያዉ ምክትሉ ኃላፊነቱን ይረከባል። ትናንት የፕሬዝደንት ጆን አታ ሚልስ ህልፈተ ህይወት በተሰማ በሰዓታት ዉስጥ ምክር ቤቱ ተሰበሰበ። ምክትላቸዉ የነበሩት ጆን ማሃማ ቃለመሃላ ፈፅሙና መንበሩን ተረከቡ። እስከ መጪዉ ምርጫ ድረስ በፕሬዝደንትነት የሚቆዩት ማሃማ በሞት የተለዩትን ፕሬዝደንት አባት፤ አርአያ አሏቸዉ፤

«ያጣሁት አባቴን ነዉ፤ ጓደኛዬን ነዉ፤ ምሳሌዬን ነዉ ያጣሁት፤ ከፍተኛ ጓድ ነዉ ያጣሁት፤ ፕሬዝደንት አታ ሚልስ ህይወታቸዉን ሙሉ ለዉድ ሀገራችን የሰጡ፤ በአሁኑ ወቅት በመጨረሻ የምናወሳዉ ለሀገራችን አንድነትና መረጋጋት ያደረጉትን አስተዋፅኦ ነዉ።»

ከተረጋጋ ፖለቲካዋ፤ ሌላ በዴሞክራሲያዊ ሂደት በምታካሂደዉ የስልጣን ሽግግር የምትታወቀዉ ጋና፤ የፕሬዝደንቷ ድንገተኛ ሞት እንደመሰል የአፍሪቃ ሀገሮች ዉጥንቅጥ ሳያሳያት እስከምርጫዉ የሚመራ ፕሬዝደንት መሰየሙ ተሳክቶላታል። የ53 ዓመቱ የታሪክ ምሁር ማሃም የሀገሪቱን ኤኮኖሚ በተረጋጋ መንገድ እንዲቀጥል ይረዳሉ የሚል ተስፋ ተጥሎባቸዋል። ዋናዉ ጥያቄ ግን ለቀጣዩ ምርጫ በአታሚልስ እግር በእጩነት ማን ይተካል የሚለዉ ነዉ። 

ፓርቲያቸዉ ብሄራዊ ዴሞክራሲ ተተኪዉን ይመርጣል ቢባልም፤ ብዙዎች ከማሃም አያልፍም ባይናቸዉ። ከዚህ በመነሳትም ምናልባት የታህሳሱ ምርጫ ጋና ዉስጥ አለመረጋጋት ሊያስከትል ያደግሞ አሁን ባለበት ደረጃ እጅግ የወረደዉ የሀገሪቱ የገንዘብ አቅም ሊባባስ ይችላል የሚል ስጋት አለ። አክራ የሚገኘዉ የጀርመኑ ፍሬድሪሽ ኤበርት ተቋም ባልደረባ ዳንኤላ ኩሱ በእሳቸዉና በምክትላቸዉ መካከል ጥብቅ ትስስር ስለነበር የፕሬዝደንት አታ ሚልስ ድንገት ማረፍ የጋናን ፖለቲካዊ ሁኔታ አይቀይረዉም ባይ ናቸዉ፤

«በመሠረቱ በጣም ግሩም ጉድኝት ያላቸዉ የሥራ ባልደረቦች ነበሩ። ሚልስ አዘዉትረዉ በሚያደርጉት የስራ ጉዞ ምክንያት በቦታቸዉ ተክተዋቸዉ የሚሠሩት ማሃማ ነበሩ። እንደዉም አንዳንዶች ተጠባባቂ ፕሬዝደንት ነበር የሚሏቸዉ። በተሠማሩበትም በርካታ ጥሩ ነገሮችን ሠርተዋል፤ ስለዚህ በደንብ የታዩና የታወቁ ምክትል ፕሬዝደንት ነበሩ።»

Ghana John Atta Mills und Jerry Rawlings
አታ ሚልስ ከጄሪ ሮዉለንስ ጋምስል Getty Images

በጄሪ ሮዉሊንግስ ዘመነ ሥልጣን ከጎርጎሮሳዉያኑ 1997 እስከ 2001ዓ,ም ድረስ በምክትል ፕሬዝደንትነት ጋናን ያገለገሉት አታ ሚልስ፤ አልቀናቸዉም እንጂ በ2000 እና በ2004ዓ,ም ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ምክር ቤት ለሚባለዉ ፓርቲ ፕሬዝደንታዊ እጩ ሆነዉ ቀርበዋል። በዚሁ የዘመን ቀመር 2008 መገባደጃ ላይ ግን ቀናቸዉ እና በ2009ዓ,ም ጥር ወር በትረ ስልጣኑን ጨበጡ። እንደእሳቸዉ ቢሆን በመጪዉ ታህሳስ ወር በሚካሄደዉ ምርጫ ለመፎካከርና ከተሳካም ስልጣን ላይ ለመቆየት አቅደዉ ነበር። ሞት ግን ቀደማቸዉ ሳይታሰብ፤ ሰኞ አመመኝ አሉ፤ አክራ የሚገኘዉ 37ኛ ወራደራዊ ሃኪም ቤት ገቡ፤ ማክሰኞ ህልፈታቸዉ ተሰማ። ጆን አታ ሚልስ ጋና ዉስጥ እስካሁን ከስልጣን መንበራቸዉ ሳይሻሩ ሞት የወሰዳቸዉ ፕሬዝደንት ናቸዉ።  

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ