1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋምቤላ ታጋቾች በከፊል ተመለሱ

ረቡዕ፣ ሰኔ 8 2008

ታጣቂዎቹ ያን ያሕል ሕዝብ ሲግድሉ፤ሲዘርፉና ሲያግቱ ድንበርን የማስከበር፤ የሐገር ፀጥታና የሕዝብ ደሕንነትን የማስከበር ሐላፊነት ያለበት የኢትዮጵያ ጦር የት-ምንስ ያደርግ ነበር ብሎ ጥያቄ-ብዙዎች ብዙ ጊዜ ጠየቁ።መልስ የለም።የኢትዮጵያ መንግሥት ለጥያቄዉ መልስ ከመስጠት ይልቅ ያደረገዉ ወደ የደቡብ ሱዳን ግዛት ጦር ማዝመት ነበር።

https://p.dw.com/p/1J6uj

[No title]

ሙርሌ የተሰኘዉ የደቡብ ሱዳን ጎሳ ታጣቂዎች ባለፈዉ ሚያዚያ ከጋምቤላ መስተዳድር አግተዉ ከወሰዷቸዉ ልጆች መካከል ከሥልሳ የሚበልጡ መመለሳቸዉ ተነገረ።አኝዋክ ሰርቫይቫል የተሰኘዉ የመብት ተሟጋች ድርጅት እንዳስታወቀዉ ታግተዉ ከተወሰዱት 110 ሰዎች መካከል 63ቱ ተመልሰዋል።መንበሩን ለንደን-ብሪታንያ ያደረገዉ ድርጅት እንደሚለዉ ታጋቾቹ በከፊልም ቢሆን የተመለሱት በሐገር ሽማግሌዎች ጥረትና በድርድር ነዉ።የድርጅቱ ሐላፊ አቶ ንዪካዉ ኦቻላ እንደሚሉት ባሁኑ ወቅት ባካባቢዉ ያለዉ አለመረጋጋት እና የሚጥለዉ ዝናብ ቀሪዎቹን ለማፈላለግ እና ለመመለስ የሚደረገዉን ጥረት ሳያዉከዉ አይቀርም።ነጋሽ መሐመድ ተከታዩን ዘገባ አጠናቅሮታል።

ዉሐ፤የግጦሽ መሬት፤ ጎሳ-ዘር ምክንያት ሆኖ የድንበር ላይ ግጭት-ቁርቁስ፤ግድያ-ዘረፋዉ በርግጥ የዓመት ከዓመት ክስተት ነዉ።ዘንድሮ ሚያዚያ የደረሰዉ ግን፤ የአካባቢዉ ተወላጆች እንደሚሉት በብዙ ዘመን ታሪክ ደርሶ አያዉቅም።ዘመናይ ጦር መሳሪያ የታጠቁት የደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ አባላት የጋምቤላ መንደሮችን ወርረዉ ከሁለት መቶ በላይ ሰዉ ሲገድሉ፤ በርካታ አቁስለዉ ከአንድ መቶ የሚበልጡ ሕፃናት፤ ልጆች፤ ሴቶችን እና በርካታ ከብቶችን አግበስብሰዉ ተሰወሩ።

ታጣቂዎቹ ያን ያሕል ሕዝብ ሲግድሉ፤ሲዘርፉና ሲያግቱ ድንበርን የማስከበር፤ የሐገር ፀጥታና የሕዝብ ደሕንነትን የማስከበር ሐላፊነት ያለበት የኢትዮጵያ ጦር የት-ምንስ ያደርግ ነበር ብሎ ጥያቄ-ብዙዎች ብዙ ጊዜ ጠየቁ።መልስ የለም።ሁለተኛ ወሩ።የኢትዮጵያ መንግሥት ለጥያቄዉ መልስ ከመስጠት ይልቅ ያኔ ያደረገዉ አጋች-ታጋቾቹ ሰፍረዉበታል ወደተባለዉ የደቡብ ሱዳን ግዛት ጦር ማዝመት ነበር።

Südsudanesische Flüchtlinge in Gambella
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

አኝዋክ ሰርቫይቫል የተሰኘዉ የመብት ተሟጋች ድርጅት የበላይ ንዪካዉ ኦቻላ የኢትዮጵያ መንግሥትን የ«ሰዶ-ማሳደድ» አይነት እርምጃን ያኔም አሁንም አይቀበሉትም።

ታግተዉ ከነበሩ ኢትዮጵያዉያን 63ቱ መመለሳቸዉን አቶ ንዪካዉ አረጋግጠዋል።ታጋቾቹን ያስለቀዉ ግን የዘመተዉ ጦር አልነበረም።የሐገር ሽማግሌዎች ማግባባት፤ የፖለቲከኞች ፍቃድና ድርድርና እንጂ።ለሟቾች የደም ካሳ ሥለመጠየቅ-አለመጠየቁ የሚታወቅ ነገር የለም።ገዳይ-አጋቾችን ለፍርድ የማቅረብ ሙከራ የለም።ሌላ ቀርቶ እስካሁን ያልተመለሱት፤ ሕፃናት፤ ልጆችና ሴቶች ያሉበት ስፍራ፤ለማስመለስ የሚደረገዉ ጥረት የደረሰበት ደረጃም ግልፅ አይደለም።የኢትዮጵያ የፌደራል እና የጋምቤላ መስተዳድር ባለሥልጣናትን በስልክ ለማግኘት ያደረግነዉ ሙከራ ፤ባለሥልጣናቱ ትናንት ሙሉ ቀን «ስሰብ ላይ ናቸዉ» በመባሉ በሙከራ ነዉ የቀረዉ።

Sudanesische Flüchtlinge in Äthopien
ምስል DW/Coletta Wanjoyi

አቶ ንዪካዉ እንደሚሉት ግን ቀሪዎቹን የማስለቀቁ ፍላጎት እና ጥረት ቢኖር እንኳ ወቅቱ አመቺ አይደለም።ለዘመናት የኖረዉ ግን ሚያዚያ ላይ የከፋዉ ግድያ፤ዘረፋና እገታ ለወደፊቱ የመገታቱ ምልክት እንቅስቃሴም አይታይም።አቶ ንዪካዉ እንደሚሉት ችግሩ በዘላቂዉ የሚወገደዉ ከድንበር ማዶ ለማዶ የሚገኘዉy ከብት አርቢ ሕዝብ አኗኗር፤ አስተሳሰብ፤አመለካከቱን ሲቀይር ነዉ።ላሁኑ ግን የርብቶ አደሩን ኑሮ መለወጥ አይደለም ሕይወቱንም ያዳነዉ የለም።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ