1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጅቡቲ ምርጫ፤ ዉጤትና ትችቱ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 3 2008

ባለፈዉ ሳምንት ዓርብ በአፍሪቃ ቀንድ ስልታዊ ጠቀሜታ ባላት በጅቡቲ የተካሄደዉ ምርጫ ላይ ግድፈት ቢታይበትም ምርጫዉ ነፃ፣ ግልፅና ተዓማኒ እንደነበር የአፍሪቃ ኅብረትና የአዉሮጳዉ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎች ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/1ITKz
Dschibuti Präsidentenwahl Ismail Omar Guelleh
ምስል picture alliance/abaca

ምርጫዉ ሃገሪቱን ለ17 ዓመታት የመሩት ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ የምርጫዉ ዉጤት ይፋ እንደሆነ «ነገውኑ ወደ ሥራ እገባለሁ» ማለታቸዉ ተዘግቦላቸዋል። በተቃራኒዉ የሀገሪቱ የተቃዉሞ ፖለቲከኞች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ምርጫው ፖለቲካዊ አፈና እና መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በተንሰራፋበት ሁኔታ የተካሄደ፤ ሚዲያዎች በነፃነት በማይሠሩባት ሃገር የተከናወነ ነው በማለት ትችት እያሰሙ ነዉ። በኢትዮጵያ የዉጭ ግንኙነትና ስትራቴጂክ ተቋም ጥናት ተመራማሪ አቶ አበበ ዓይነቴ በጅቡቲ ብሎም በኢትዮጵያና ጅቡቲ ግንኙነት ላይ ጥናት አድርገዋል። እሳቸዉ እንደሚሉት በአፍሪቃ ቀንድ በምትገኘዉ ጅቡቲ ሰላማዊ ምርጫ ተካሂዷል፤ ምናልባት ቅሬታዉ ያለዉ ዉጤቱ ላይ ነዉ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና ተቃዋሚዎች የፕረስ ነፃነት በሌለበት ነፃ ምርጫ አልነበረም ሲሉ ነዉ የሚከሱት።
ፕሬዝዳንቱ ለምርጫ የቀረቡት ከተዳከሙ እና ከተበታተኑ ተቃዋሚዎች ጋር የነበረ በመሆኑ ለአራተኛ የሥልጣን ዘመን እንደሚያሸንፉ ተገምቶ ነበር። ከአጠቃላይ የጅቡቲ ዜጎች መምረጥ የሚችሉት 187,000 ያክሉ መሆናቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል። በአጠቃላይ በምርጫዉ ሂደትም ሆነ በምርጫዉ ዉጤት ላይ ቅሪታዎች መምጣቱ አይቀሪ ነዉ የጉሌህ መመረጥ ግን በቀጠናዉ መረጋጋት አስተዋፅኦ አለዉ ሲሉ አቶ አበበ ተናግረዋል።

Dschibuti Präsidentenwahl Ismail Omar Guelleh
ምስል Getty Images/AFP/H.-I. Hersi


ፕሬዝዳንት ኢስማዔል ኦማር ጉሌህ ምርጫውን እንደሚያሸንፉ እርግጠኛ እንደነበሩ መናገራቸዉ ተዘግቦአል። የ68 ዓመቱ ጉሌህ ጅቡቲ ከፈረንሳይ ነፃነቷን ካገኘችበት ከጎርጎሮሳዊው 1977 ወዲህ ሃገሪቱን የመሩ ሁለተኛው ፕሬዝዳንት ናቸው ። የመጀመሪያው የጅቡቲ ፕሬዝዳንት ሃሰን ጉሌድ ኦፕቲዶን የጉሌህ አጎት ናቸው።


አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ