1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር የአፍሪቃ ጉብኝት

ቅዳሜ፣ የካቲት 14 2007

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር የአፍሪቃ ጉብኝታቸውን ቀጥለው ዛሬ ወደ ሩዋንዳ አቅንተዋል። ሚንሥትሩ ከሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ጋር ዛሬ በመዲናዪቱ ኪጋሊ ተገኝተው ንግግር አሠምተዋል።

https://p.dw.com/p/1EfVY
Steinmeier in Goma
ምስል DW / Claus Stäcker

እጎአ በ1994 የሩዋንዳ የእርስ በእርስ የዘር ፍጅት ለተጨፈጨፉ ሰዎች የቆመውን የመታሠቢያ ማዕከልም ጎብኝተዋል። ጀርመን ከአፍሪቃ ጋር ያላትን ግንኙነት የምታጠናክረው በአህጉሪቱ የምጣኔ ሀብት ዕድሎች ስላሉ ብቻ ሳይሆን አፍሪቃን በተመለከተ ኃላፊነት ስለሚሰማት ጭምር እንደሆነ ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ተናግረዋል። የሩዋንዳ ጎረቤት በሆነችው ዲሞክራሲያዊ ኮንጎ ሪፐብሊክ ውስጥ የተሰማራውን የተመድ ሠላም አስከባሪ ለማገዝ ጀርመን በየዓመቱ ከ100 ሚሊዮን ዩሮ በላይ እንደምትረዳ ይታወቃል። የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር እጅግ ከፍተኛ ግፍ እና በደል በሚፈጸምበት የዲሞክራሲያዊ ኮንጎ ሪፐብሊክ ምሥራቃዊ ክፍል ፤ ጎማ ትናንት በመገኘት የሚከተለውን ተናግረዋል።

«ቦታው ካለፉት 20 ዓመታት አንስቶ በአካባቢው በተፈራረቁ የጦር አበጋዞች የተነሳ ሊታመን በማይችል ግፍ ለተሰቃዩ ሰዎች የተስፋ ቦታ ነው። በተመሳሳይ መልኩ፤ መደበኛ ሕይወት የሚቀጥልበት፣ በደልና ግፉ የሚያከትምበት፣ የምጣኔ ሀብት እድገት የሚመጣበት እና የሰብዓዊ ርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ርዳታው የሚደርስበት የተስፋ ቦታም ነው።»

Kongo Steinmeier Joseph Kabila Kabange
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር እና የዲሞክራሲያዊ ኮንጎ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ ካባንጌምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ሰሜን ኪቩ አውራጃ ውስጥ የአውሮፕላን ማስፋፊያ ግንባታን በጎበኙበት ወቅት ንግግራቸውን ሲያሰሙ የሀገሪቱ የመጓጓዣ አገልግሎት ሚንሥትርም ተገኝተው ነበር። ጀርመን በሰሜን ኪቩ አውራጃ የሚገኘውን 500 ሜትር ርዝመት ያለው የአውሮፕላን መንደርደሪያ ማስፋፊያ በገንዘብ ትደግፋለች።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ልደት አበበ